ቅምሻ -ከወዲያ ማዶ # ከሰመመን ሲነቃ ፈረንሳይኛን አቀላጥፎ መናገር የቻለው የማንችስተር ተጫዋች

Views: 379

የሮሪ ከርትስ ጉዳይ ትንግርት ካልተባለ ምን ሊባል ይችላል?

ታሪኩን በአንድ አንቀጽ የሚከተለውን ይመስላል።

ሮሪ በ22 ዓመቱ ዘግናኝ የመኪና አደጋ ደረሰበት። ከሳምንታት በኋላ ከሰመመን ነቃ። በቅጡ ተናግሮት የማያውቀውን ፈረንሳይኛ እንደ ልሳን ያንበለብለው ጀመር።

ሮሪ ለማንችስተር ታዳጊ ቡድን ተጫዋች ነበር። በሕይወቱ ከኳስ ሌላ ሕልም አልነበረውም።

በአንድ ክፉ አጋጣሚ መኪናውን በእንግሊዝ አውራ ጎዳና በፍጥነት ሲያሽከረክር ተገለበጠ። ያን ቀትር ዶፍ እየዘነበ ነበር። መንገዱ ያንሸራትት ነበር። እሱ ከከባድ መኪና ጋር ሲጋጭ ከኋላው በፍጥነት እየተነዱ የነበሩ ስድስት ሌሎች የቤት መኪናዎች ተገጫጭተው እላዩ ላይ ወጡበት። የእርሱ መኪና ጭምድድድ. . . አለች፤ እንደ ካርቶን።

እንኳን ሰው ዝንብ ከዚያ አደጋ ይተርፋል ያለ ማንም አልነበረም። ሮሪ ግን ሲፈጥረው በቀላሉ አትሙት ተብሏል መሰለኝ. . .፡፡ ራሱን ሳተ እንጂ ነፍሱ አልወጣችም ነበር።

አምቡላንስ መጣ፤ ሆስፒታል ተወሰደ። ለሳምንታት አልነቃም።

ሐኪሞቹ የዚህ ወጣት ነፍስ የመትረፍ ዕድሏ የተመናመነ እንደሆነ ለቤተሰቦቹ በይፋ ተናገሩ። ኾኖም ግን አንድ በሙከራ ላይ ያለ መድኃኒት እንዳለና ፍቃዳቸው ከሆነ እሱን መድኃኒት ሊወጉት እንደሚችሉ ጠየቁ።

የሮሪ ወላጆች ተስማሙ። አዲሱን መድኃኒት ተወጋ። ሆኖም ከሰመመኑ አልተመለሰም። በግማሽ ሞት፣ በግማሽ ሕይወት መሀል ሆኖ ለሳምንታት ራሱን እንደሳተ ቆየ።

ሁሉም ነገር ተስፋ አስቆራጭ በሚመስልበት በዚያ ሰዓት አንድ ማለዳ ሮሪ ዓይኑን ገለጠ።

እሱ ሲነቃ አጠገቡ አንዲት ጥቁር ነርስ ነበረች። አንዳች ነገር ማጉረምረም ጀመረ። ቀጥሎ የሆነው ግን ለሳይንስም ግራ ነው የሆነው።

ፈረንሳይኛ ቋንቋን ያንበለብለው ነበር። በአጋጣሚ አጠገቡ የነበረችው ጥቁር ነርስ ፈረንሳያዊት ስለነበረች ልጁ የፈረንሳይ ዜጋ እንደሆነ እርግጠኛ ነበረች። ኋላ ላይ አባትየውን ፈረንሳይ የት አካባቢ እንደሚኖሩ የጠየቀቻቸውም ለዚሁ ነበር።

እርሳቸው ግን “ኧረ እኛ ከእግሊዝ ነን፤ የምን ፈረንሳይ አመጣሽብኝ?” አሉ።

“ታዲያ እንዴት ልጆዎ ፈረንሳያዊ ሊሆን ቻለ? በእናቱ ወገን ይሆን?” ነርሷ ጠየቀች። በፍጹም ጥርጣሬ አልገባትም ነበር።

ሆኖም ሮሪ አይሪሽ እንጂ ፍሬንች አልነበረም።

እርግጥ ልጅ እያለ ድሮ በትምህርት ቤት መጠነኛ ፈረንሳይኛ ተምሯል። አለ አይደል? ለመግባባት ያህል የምትሆን ፈረንሳይኛ።

ያን ከመማሩ ውጪ በዚህ ደረጃ ቋንቋውን አቀላጥፎ ተናግሮት አያውቅም። አይችልምም።

እንዲያውም ልጅ እያለ ከተማረው በኋላ ቋንቋውን ተናግሮ ስለማያውቅ ጭራሽ ፈረንሳይኛን እንደማያስታውሰው ነበር የሚታወቀው።

ነገር ግን ከሰመመን ሲነቃ ፈረንሳይኛውን አንበለበለው።

ይህ ትንግርት ነበር፤ ለሐኪሞቹም፣ ለወላጆቹም፣ ለሳይንስም።

የራሱን ማንነት የረሳው የማንችስተር ተጫዋች

ሮሪ ከሳምንታት ሰመመን ሲነቃ ፈረንሳይኛ ይናገር እንጂ ማን እንደነበረ በጭራሽ አያውቅም ነበር።

ለማንችስተር ታዳጊ ቡድን ይጫወት እንደነበረ ቢነገረው ሊገባው አልቻለም። ኳስ ይወድ እንደነበረ እንኳ ረስቷል። ስላለፈ ሕይወቱ በጭራሽ የሚያስታውሰው ነገር የለም። አንዳችም ነገር!

ለምሳሌ ምን ሆኖ ወደ ሆስፒታል እደገባ፣ ጭኑ አካባቢ እንደተሰነጠቀ፣ ክርኑ እንደተሰበረ፣ ጭንቅላቱ እንደተፈለጠ ሁሉ አያውቅም። ፈረንሳይኛ ብቻ ያውቃል።

ፈረንሳይኛው እንደ ልሳን. . . እንደ ማር. . . ከአፉ ጠብ ይል ነበር። ሆኖም ብዙ አልዘለቀም። በድንገት ዝም አለ።

ፈረንሳይኛው በድንገት እንደ ጉም በነነ። በቃ አቃተው። ተናገር ሲባል ኧረ እኔ ፈረንሳይኛ አልችልም ነበር ያለው። እንዴት ይህ ሊሆን ቻለ?

ቅደም አያቶቹ ከፈረንሳይ መሆናቸው ይሆን?

“አባቴ ነገሩ አስገርሞት መመራመር ያዘ። የደረሰበት ነገር ቢኖር የእርሱ ቅድመ አያቶች ከሰሜን ምዕራብ ፈረንሳይ ኖርማንዲ ግዛት የሚመዘዙ መሆናቸው ነበር” ይላል ሮሪ።

ይህ ዘመን ግን በ1800 አካባቢ መሆኑ ነው። ይህ ታዲያ እንዴት ከሮሪ ፈረንሳይኛ መናገር ጋር ሊገናኝ ይችላል?

ቋንቋ እንደ ስኳርና ደም ግፊት በደም አይተላለፍ ነገር! ይተላለፍ ይሆን እንዴ?

ሮሪ በእርሱ ላይ የደረሰው ትንግርት እንዴት ዓለምን ሲያነጋግር እንደቆየ ለቢቢሲ ሲናገር “ዩቲዩብ ላይ ስሜን ጉግል ብታደርገው ከእኔ መላምቶች ጋር በተያያዘ ብዙ ቪደዮዎችን ታገኛለህ። አንዳንዱ ቋንቋ በትምህርት ብቻ ሳይሆን በዘር የሚተላለፍና አእምሯችን ጓዳ ሊቀበር እንደሚችል የሚገልጽ ነው” ይላል።

ሮሪ የሆሊውድ ተዋናይ መሆኑን ነበር የሚያውቀው

ሮሪ ላይ ይህ አደጋ የደረሰው በ2012 ላይ ነበር። ያን ጊዜ ሮሪ 22 ዓመቱ ነበር። ዛሬ 30 ዓመት ደፍኗል።

ሮሪ ያን ጊዜ ለማንችስተር ዩናይትድ ታዳጊ ቡደን እየተጫወተ በትርፍ ሰዓቱ ለአንድ ተቋራጭ ኩባንያ በተላላኪነት ይሰራ ነበር።

የሚገርመው ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ዛሬም ድረስ ያ አደጋ እንዴት እንደተፈጠረ ምንም ትዝ አይለውም። ያ አሰቃቂ የመኪና አደጋ ከትዝታ ቋቱ የተፋቀ ጉዳይ ነው።

ሆኖም የዓይን እማኞች እንደተናገሩት ሮሪ በዚያ ዝናብ በከፍተኛ ፍጥነት እየነዳ በፍጥነት መስመር ሲቀይር ነበር ከፊት ለፊቱ ከሚገኝ ከባድ ተሸከርካሪ ጋር ሄዶ የተላተመው። ከዚያም ከኋላው የነበሩ መኪናዎች እላዩ ላይ ወጡበት።

የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች ሮሪን ከተጫኑት ስድስት መኪናዎች ውስጥ ፈልፍለው ለማውጣት ከግማሽ ሰዓት በላይ ወስዶባቸዋል።

ያን ጊዜ ትንፋሽ አልነበረውም። ሆኖም አምቡላንስ ውስጥ የመተንፈሻ መሣሪያዎች ተገጥመውለት በርሚንግሀም ወደሚገኘው ቅድስት ኤልዛቤጥ ሆስፒታል ተወሰደ።

ሐኪሞች ምን አሉ?

ሮሪ የኋላ ታሪኩ ሲጠና 7 ዓመቱ ላይ ሳለ የማጅራት ገትር የመሰለ ሕመም ታሞ እንደነበር ታውቋል። ያን ጊዜም ቢሆን የመትረፍ እድሉ 50 በመቶ ብቻ ነበር።

ለ6 ሳምንት በበርሚንግሀም የሕጻናት ሆስፒታል ውስጥ ክትትል ተደረገለት። ከዚያ በኋላ በተወነ ደረጃ ዕይታው ስለተጋረደ መነጽር ማድረግ ጀምሮ ነበር።

“ያን ጊዜ ሆስፒታል ከነበርነው ሕጻናት እኔ ብቻ ነኝ የልጅነት ልምሻ ያልያዘኝ። ያለምንም ጉዳት ድኜ ስወጣ ሰው ሁሉ ገርሞት ነበር” ይላል።

ይኸው ነው ቅድመ ታሪኩ። ሮሪ ከዚህ በኋላ ምንም የጤና እክል አላጋጠመውም። እንዲያውም ንቁና ቀልጣፋ በመሆኑ እግር ኳስ አካዳሚ ተመዘገበ።

ቤተሰቡ የለየለት የበርሚንግሀም ቀንደኛ ደጋፊዎች ናቸው።

በ11 ዓመቱ ለበርሚንግሀም የታዳጊ ቡድን እንዲጫወት ተፈቅዶለት ነበር። በ13 ዓመቱ ለሴንትራል አያክስ ቡድን አጥቂ ቦታ ሲጫወት የማንችስተር ዩናይትድ መልማዮች አይተውት ወደዱት፤ ወሰዱት።

ከዚህ በኋላ ነበር አሰቃቂው አደጋ የደረሰበት።

ከሰመመን ሲነቃ ፈረንሳይኛ መናገሩ ብቻ አይደለም የሮሪ አስገራሚው ነገር።

እድሜውንም ረስቶ ነበር። ያኔ 22 ዓመቱ የነበረ ቢሆንም እርሱ ግን የ10 ዓመት ልጅ እንደሆነ ነበር የሚያውቀው።

“ውሻዬ የት ሄዳ ነው?” ይላል። “እማዬ ውሻዬን አምጪልኝ” ይለኝ ነበር ትላለች እናቱ። ውሻዋ እኮ ድሮ እሱ ልጅ እያለ ነው እኮ የሞተችው። እርሱ ግን ረስቶታል።

ሮሪ በበኩሉ “ቀስ እያልኩ እድሜዬ 10 ሳይሆን 12 እንደነበር ትዝ አለኝ” ይላል።

የሚደንቀው ይህ አይደለም።

ከሰመመን ከነቃ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሮሪ ራሱን የሆሊውድ ዝነኛ ተዋናይ ማቲው መካነሄይ እንደሆነ ነበር የሚያስበው። ቅዠት ሳይሆን በእውን እርሱ የሆሊውዱ ማቲው ማካነሄይ እንደሆነ በትክክል ያምን ነበር።

መጀመርያ እንዲያ ያስብ የነበረው ሆስፒታል አልጋ ላይ ሳለ ነበር። ያስጨንቀው የነበረውም ቶሎ ተነስቶ ቀጣዩን ዝነኛ ፊልሙን መቅረጽ ነበር።

እርሱ የኦስካር አሸናፊ ማቲው መካነሄይ እንደነበረ እቺን ታህል ጥርጣሬ አልበረውም።

“ክንዴና ጭኔ አካባቢ ተሰብሬ ስለነበር እናቴ ነበረች ሽንት ቤት የምታደርሰኝ። የመጀመሪያ ከሰመመን ነቅቼ ሽንት ቤት ሳለሁ በመስታወት የማየው ልጅ ማን ነው? ስል ግራ ተጋባሁ። አላውቀውም ነበር። ራሴን አላውቀውም። የራሴን መልክ አላውቀውም። እኔ የማውቀው ማቲው መካነሄይን መሆኔን ነበር” ይላል ሮሪ።

ምናልባት ሮሪ ያን ጊዜ መስታወቱ የዋሸው ያህል ሳይሰማው አልቀረም። እሱ ቆሞ እንዴት የሌላ ሰው ፊት ያሳየዋል?

ሮሪ በየ15 ደቂቃው ይረሳ ጀመር

ሮሪ በኅዳር 2012 ከሆስፒታል ሲወጣ አብዛኛውን ነገር ዘንግቶ ነበር። እንኳንስ የድሮውን ይቅርና ከ15 ደቂቃዎች በፊት ያደረገውን ይረሳል።

ስለዚህ ማስታወሻ ደብተር ተገዛለት። ምሳ ሲበላ ምሳ በልቻለሁ ብሎ ይጽፋል። ገላውን ታጥቦ እንደወጣ ገላዬን ታጥቢያለሁ ብሎ ይጽፋል።

“በዚህ መንገድ የጨረስኩት የማስታወሻ ደብተር ብዛቱ!” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሮሪ በዚህ መንገድ ማንነቱን መልሶ ለማግኘት ብርቱ ጥረት አደረገ። በመጨረሻም አንድ ዓመት ካገገመ በኋላ ራሱ ልብሱን መቀየር ቻለ። ከዚያ ሙሉ በሙሉ ድኖ ወደሚወደው እግር ኳስ ለመመለስ ሞከረ።

ከስድስት ዓመት በፊት ለስቶርፖርት ክለብ መጫወት ጀመረ። ሐኪሞች ማመን አቃታቸው። እንዴት በዚያ ደረጃ የተጎዳ ልጅ ድኖ ኳስ ሊጫወት እንደሚችል ትንግርት ሆነባቸው።

“በእርግጥ መገረም ብቻ ሳይሆን እንዳልጫወት መክረውኛል። ምክንያቱም በጭንቅላቴ ኳስ መግጨት ስለማይኖርብኝ ነው። ጭንቅላቴ በአደጋው ተጎድቶ ነበር” ይላል።

ምናልባት ሮሪ ቋንቋ ማስታወስ የቻለው የጭንቅላቱ የቋንቋ ቋት በድንገት በሩ ተከፍቶ ይሆን? አንዳንዶች ጭንቅላታችን ከተወለድን ጀምሮ የሚሰማውንና የሚያየውን ነገር ሁሉ ይመዘግባል። እኛ ማስታወስ ስላቃተን ባዶ ይመስለናል እንጂ አእምሮ እጅግ ውስብስብ ተፈጥሮ ነው ይላሉ።

ምናልባት ሮሪ ፈረንሳይኛው ከጭንቅላቱ የቋንቋ ቋት ተዘርግፎበት ቢሆንስ?

ሮሪና አዲሱ መድኃኒት

ሮሪ የመኪና አደጋው ከደረሰበት በኋላ በሙከራ ላይ የነበረ የሆርሞን መድኃኒት ወስዷል።

ያ መድኃኒት የሰው ልጅ ላይ ሲሞከር ሮሪ በዓለም ሁለተኛው ሰው ነበር። መድኃኒቱ ጭንቅላታቸው አካባቢ ከፍተኛ አደጋ ደርሶባቸው ለተጎዱ ሰዎች እንዲያገግሙ የሚረዳ ነበር።

በአሜሪካ ሐኪሞች የተመራው ይህ የመድኃኒት ሙከራ ሲናፕሴ (Synapse) ይባላል። በከፊል ፕሮግሬስትሮን የተሰኘ የሴቶችን ሆርሞን ነበር የተወጋው።

ሐኪሞቹ በየሦስት ወራት ሮሪን ይመለከቱት ነበር። ቤተሰቡ ለእሱ በተአምር መትረፍ ይህ መድኃኒት ዋናው እንደሆነ ያስባል።

እሱን ይከታተሉት ከነበሩት ሀኪሞች አንዱ የሆኑት ኒውሮሎጂስቱ ዶ/ር አንቶኒ ቤሊ ግን መድኃኒቱ ለእርሱ እንዳልሰራለት ነው የሚናገሩት። ከዚያ ይልቅ የልጁ ጥንካሬና ዘረመሉ ሊሆን ይችላል ለተአምሩ መፈጠር ምክንያት የሆነው።

ሮሪ ሙሉ በሙሉ ይዳን እንጂ አሁንም ድረስ ራሱን አግንኖ የማየት ነገር አለበት። “ፍጹም ነኝ ብዬ የማመን ስሜት ይሰማኛል” ይላል።

ሮሪ በእግር ኳሱ ብዙ ተስፋ እንደሌለው ሲያስብ ወደ አስተማሪነት ከዚያም ወደ ጸጉር አስተካካይነት ገባ።

“እናቴ 6 እህቶች አሏት። ሁሉም አስተማሪዎች ናቸው። እኔም ለምን በጸጉር ሙያ አስተማሪነት አልሞክርም ብዬ ተነሳሁ። አባቴ ዘርማንዘሮቹ ሁሉ ጸጉር አስተካካዮች ነበሩ። ለምን እሱን አልሞክረውም አልኩኝ” ይላል።

የአባቱ ድርጅት ቻርሊ ፓርከር ጸጉር ቤት ይባላል። ከ1980ዎቹ ጀምሮ ቤተሰቤ በጸጉር ሥራ ነው ሲተዳደር የኖረው። “ስለዚህ ከእናቴ ቤተሰቦች አስተማሪነትን ከአባቴ ደግሞ ጸጉር አስተካካይነትን ወሰድኩ።”

ሮሪ በኋላ ላይ ተምሮ ከተመረቀ በኋላ በበርሚንግሀም ሳውዝ ኤንድ ሲቲ ኮሌጅ ሌክቸረር ሆኖ ተቀጠረ። ጥቂት እንደሰራ ግን የልቡ አልደርስ አለ።

ስለዚህ ለምን የራሴን ጸጉር ቤት አልከፍትም ብሎ “ቻርሊ ፓርከርስ ከት ትሮት ኤንድ ኮፊ” የሚባል የውበት ሳሎን ባለፈው ዓመት ከፈተ።

መጀመርያ በ11 ዓመቱ፣ በኋላ ደግሞ በ22 ዓመቱ ሞትን በቆረጣ ጎብኝቶ የመጣው ሮሪ ጭንቅላቱ ላይ በደረሰው አደጋ የዓለም መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። እሱ ደግሞ ከጭንቅላት በላይ በሚበቅል ጸጉር መተዳደር ጀምሯል።

ስለመጪው እሱም፣ ሐኪሞቹም የሚያውቁት ነገር የለም። እንኳን ስለመጪው ስላለፈውስ መቼ በቅጡ አወቁና. . .

ቢቢሲ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com