በእስራኤል የቻይናው አምባሳደር በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሞተው ተገኙ

Views: 265

የ58 ዓመቱ አምባሳደር ዱ ዌ አልጋቸው ላይ ሕይወታቸው አልፎ የተገኘ ሲሆን ለሞታቸው ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

በቅርቡ የካቲት ወር ላይ የተሾሙት አምባሳደሩ ከዚህ በፊት ዩክሬን ውስጥ የቻይና ልኡክ ሆነው ሲሰሩ ነበር።

አምባሳደሩ የአንድ ልጅ አባት ሲሆኑ ባለቤታቸውም ሆነ ልጃቸው በአገር ውስጥ እንዳልነበሩ ተገልጿል።

አምባሰደር ዱ በቴልአቪቭ ሄርዚሊያ በምትባል አካባቢ ነዋሪ ነበሩ።

የእስራኤል ፖሊስ ቃለ አቀባይ ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት ፖሊስ የሞቱበት ስፍራ ደርሶ ሁኔታውን እያየ መሆኑን ነው።

የእስራሌል ቴሌቪዥን ጣቢያ ስሙ ካልተጠቀሰ የህክምና ምንጭ አገኘሁት ባለው መረጃ የመጀመሪያ ምርመራ እንደሚጠቁመው አምባሳደሩ በእንቅልፍ ላይ እንዳሉ በተፈጥሯዊ ሞት መሞታቸውን ነው።

አምበሳደሩ ገና በእስራኤል በተሾሙበት ወቅት “በአለም ሁለተኛ ኢኮኖሚ ያላት ሃገር ቻይናና ገና ጀማሪዋ እስራኤል” ያላቸውን ግንኙነት ማድነቃቸውን በኤምባሲው ድረገፅ የወጣው ፅሁፍ አትቷል።

በዚህ ሳምንት አርብም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ በእስራኤል ጉብኝታቸው ቻይና ወረርሽኙን የተቆጣጠረችበትን መንገድ መተቸታቸውን ተከትሎ ኤምባሲያቸው የሰላ አፀፋዊ ምላሽ ሰጥቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ጀሩሳሌም ፖስት ባወጣው ፅሁፍ ላይ ቻይናና ወረርሽኙን ሸፋፍናለች የሚለውን ውንጀላ ኤምባሲው ማውገዙንም ተጠቅሷል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com