ዜና

ኮሮና እና የማዳጋስካር ፀሐይ …

Views: 21932
 • ዳግም ለኢኳቶሪያ ጊኒ!

ሀ/ የማዳጋስካር ዕፀ-መድኃኒት፤

አፍሪቃዊቷ ትልቋ ደሴት- ማዳጋስካር፣ ባለፈው ሳምንት ለኮሮና ቫይረስ ወይም ኮቪድ 19 ከዕፀዋት ውጤት “መድኃኒት አግኝተናል” ብላለች፡፡ ስሙም ኮቪድ ኦርጋኒክ  (Covid Organics /CVO/  ) ይባላል፡፡ ማጣቀሻ አንድ

የማላጋሲው ፕረዚዳንት አንድሪ ራጆሊና በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ኮቪድ ኦርጋኒክ  ማግኘታቸውን እና ይህም የእስከ ዛሬን የመድኃኒት የጉዞ ታሪክ የሚቀይር ነው በማለት የምስራች አበሰሩ፡፡ ቀጥለውም አጠቃቀሙ መድኃኒቱ በፈላ ውሃ ተዘፍዝፎ ቆይቶ (concoction) እንደ ሻይ የሚጠጣ ከኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ለመከላከል እና ለማዳን የሚሆን ዕፀ-መድኃኒት  መሆኑን በይፋ አረጋግጠዋል፡፡ መድኃኒቱም የተሠራ ወይም ለተባለው በሽታ ይበልጥ ምርመራ ያደረገው በማላጋሲ ኢንስቲቲዩት ኦፍ አፕላይድ ሪሰርች መሆኑም ተነግሯል፡፡

አንድሪ ራጆሊና በመጠጥነት የተዘጋጀውን መድኃኒት መግዛት ለማይችሉት ችግረኞች በነፃ በቀጥታ እንዲከፋፈል እና መግዛት ለሚችሉት በዝቅተኛ ዋጋ እንዲሸጥ ሲሉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡

ይህ ጉዳይ “እውነት ነው” ብለን ከተቀበልን፤ እንዴት ያለች የፈካች ፀሐይ ለማዳጋስካር ቀድማ ወጣች?! ብለን እንደነቃለን፡፡ የዓለም ህዝብ በዚህ በሽታ ይህ ሁሉ ሐፍረት እና መከራ ሲደርስብን፤ በማዳጋስካር የሆነው ነገር እንዴት ነው? ይህ የሆነላቸው መድኃኒት እንከን አይንካባቸው፣ ይሳካላቸው፣ ለአዛውንቱም፣ ለሴቶቹም፣ ለወጣቱም፣ ለልጆችም ይሁንላቸው እንላለን፡፡

ለ/ ለኢኳቶሪያል ጊኒ ተሰጠ

ይህንኑ የኮሮና በሽታን ያድናል የተባለለትን የመድኃኒታማ ዕፅ ውጤት ግኝት ባለፈው ሳምንት በአካባቢው መገናኛ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ፤ በመሐከለኛው አፍሪካ የምትገኘው የኢኳቶሪያል ጊኒ የጤና ሚኒስተር ዴኤታው  ሚቶሃ ኦንዶኦ አዬካባ “ማየት ማመን ነው”  በማለት  መጭ ብለው  ማዳጋስካር ጎራ አሉ፡፡ ደርሰውም “ተሠራ የተባለውን ዕፀ መድኃኒት ለአገሬ ህዝብ እፈልጋለሁ?  ሲሉ ጠየቁ፡፡ ማጣቀሻ ሁለት

የእህት አገር ማዳጋስካሩ ፕሬዚደንት ጥያቄውን በደስታ ተቀበሏቸው፡፡ በመሆኑም በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ሚያዝያ 2ዐ ቀን 2ዐ12 ዓ.ም ማዳጋስኮር መድኃኒቱን ለኢኳቶሪያል ጊኒ ማበርከቷን አበሰረች፡፡

ክብደቱ 1.5 ቶን የሆነ፣ በ11 5ዐዐ (አሥራ አንድ ሺ አምስት መቶ) ፓኮዎች የተዘጋጀ፣ እንደ መዓዛማ ሻይ የሚጠጣውን፣  ኮቪድ ኦርጋኒክ  Covid Organics (CVO)  የተባለ መድኃኒት ለኢኳቶሪያል ጊኒ ስትልክ፣ ሚኒስቴር ዴኤታው ተረክበው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ከተላኩትም የመድኃኒት ፓኮዎች ውስጥ 1 5ዐዐ ፓኮው ለታመሙት ማዳኛ  እና 1ዐ ዐዐዐ ፓኮው ያህሉ ደግሞ ለመከላከያ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ኢኳቶሪያል ጊኒ ለዚህ በማዳጋስካር ተመራማሪዎች ለተገኘው የኮሮና ዕፀ መድኃኒት  ከሁሉ ቀድማ ዕውቅና የሰጠች እንዲሁም ተጠቃሚ አገር ሆናለች፡፡፡ ላ ቨርቴ የተባለው ጋዜጣ፣ የኢኳቶሪያል ጊኒ የጤና ሚኒስተር ዴኤታ፣ የሆኑትን  ሚቶሃ ኦንዶኦ አዬካባ  “በሁለቱ አገራት መሐከል ያለው የጤና ትብብር ወደፊትም እንደሚጠናከር ተስፋ እናደርጋለን ”  ብለዋል  ሲል ገልጿል፡፡

ኢኳቶሪያል ጊኒ በሰሜን ከካሜሩን፣ በምስራቅ እና በደቡብ ከጋቦን፣ እና በምዕራብ በአትላንቲክ ውቅያኖስ የተከበበች ትንሽ የአፍሪካ አገር ናት፡፡

በዩኤስ አሜሪካ የሚገኘው ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ እንዳጠናቀረው ከ1.3 ሚሊዮን ህዝቧ ውስጥ እስከ ዛሬ (ሚያዝያ 2ዐ ቀን 2ዐ12 ዓ.ም ማለት ነው) 315 ሰዎች በኮቪድ 19 መጠቃታቸው፣  ከነዚህም አንድ ሰው መሞቱ እና ዘጠኙ ማገገማቸውን ገልጿል፡፡

ሐ/ የሌሎችም ደጅ ጥናት

የማዳጋስካር ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት ጨምረው እንደገለፁት ሌሎች 3 የአፍሪካ አገራት ማለትም ሴኔጋል፣ ዲሞክሪቲክ ሪፕብሊክ ኮንጎ እና ጊኒ ቢሳው መድኃኒቱን ለማግኝት ፍላጎት አሳይተዋል ብለዋል፡፡ (ይህ ዜና የተገኘው ማጣቀሻ አንድ እና ሁለት ላይ ካለው ድረ ገፅ ነው፡፡ ለተጨማሪ ገለፃ ብታነቡት መልካም ነው፡፡)

መ/ የውይይት ጉዳዮች

 • የማዳጋስካሩ ፕሬዚደንት፣ በዚህ ፍጥነት እንዲዘጋጅ አስደርገው ህዝቡን እንዲጠጣ ማዘዛቸው፡ እና አንደ ሺ ወታደር በዋና ከተማዋ ታናናሪቮ አሰልፈው ማስጠጣታቸው፣ ለሌሎች ምን ተሞክሮ ይሆናል፤
 • መድኃኒቱን የቅርብ ጎረቤት የሆኑት ሞሪሸስ፣ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ አፍሪካ አገራት ትኩረት ሳይሰጡ፣ በሩቅ ያለችው ኢኳቶሪያል ጊኒ ቀድማ መውሰዷ፣
 • ተገኘ የተባለውን ዕፀ-መድኃኒት በኬንያ በብዙ ምርምር ሲደረግበት እና ምርቱም የተሻለ እንዳላቸው ይገመታል፡፡ ነገር ግን እስከ ዛሬ ትንፍሽ አለማለታቸው፣ ሙያ በልብ ነው በማለት ይሆን ወይ፤
 • ዕፀ-መድኃኒቱን በምን ያህል መሬት ቢያለሙት ነው፣ እንደዚህ ለሌሎች የሚቸሩት፣
 • በግምት አንዱ ፓኮ መጠኑ 13ዐ ግራም ይሆናል፡፡ ይህ ለአንድ ሰው ለስንት ጊዜ ይበቃ ይሆን? ወይስ አንዱ ለአንድ ቤተሰብ ይበቃ ይሆን?
 • አሁን ይህ መድኃኒት ዕውነትም ባለዋጋ ከሆነ አንድሪ ራጆሊና ለሌሎችም ብዙ ጎረቤት የአፍሪካ አገራት እንዲህ በነፃ ያበረክቱ ይሆን?
 • ኢትዮጵያስ “ራጆሊና ወንድማችን እኛም አስራ አንድ ሺ ሳይሆን አንድ ሺ ፓኮዎች ብቻ ከፍለን ማግኘት እንፈልጋለን” ብላ ብትጠይቅ ራጆሊና ምን ይሆን መልሳቸው?
 • የነገር መሠረቱ ዕፅ በእኛም አገር ከፊሉም ቢሆን ቢገኝ እንኳን (ባለፈው ሳምንት እንደቀረበው ) “ለኮሮና ቫይረስ ዕፀ-መድኃኒት ኢትዮጵያ አገኘች” ቢባል  . . . . ከዚያስ ፤ የሚለውን ወይም https://www.youtube.com/watch?v=ho4NJyYloxE   በዚህ ላይ እንደተነገረው፤   አሁንስ ተነስተን ምርምር እንጀምር ብንል ጉዳዩ ብዙ ንትርክ ይጠይቅ ይሆን?
 • ማዳጋስካር ለዚህ ዝግጅት ተጠቀምኩ ያለችው አንዱ ከላይ በምስሉ ላይ ያለው  የቻይና ጭቁኝ (Artemisia Annua አርቲሚሲያ አኑዋ) እና ሌሎች በአገሯ የሚገኙ ተክሎችን፣ መጥና ሲሆን እነዚህን ተክሎች በአገራቸው የሚያገኙ ተመራማሪዎች በዚህ ላይ ምርምር ቢጀምሩ እንዴት ነው ነገሩ?
 • በእኛ አገር ይህ አርቲሚሲያ ለብዙ በሽታ ብዙ ጥቅም እየሰጠ ይገኛል፡፡ በተለይም ፀረ ወባ፣ ፀረ ኤች አይ ቪ፣ እንዲሁም ለጉንፋን፣ ለአስም፣ ለሳል ወዘተ የተመሰገነ መሆኑን በ (ሕክምና በቤታችን) ላይ አንብቡ፡፡ (ማጣቀሻ ሶስት)
 • አርቲሚሲያ አኑዋን ወደ ኢትዮጵያ ያስመጡት እና ያላመዱትን እጅግ እናመሰግናለን፡፡ ቀጥሎም ስለ ልማቱ እና አጠቃቀሙ የተዘጋጀ መጽሐፍ አንብቡ፡፡ (ማጣቀሻ አራት)

ሠ/  ለወደፊቱም እንደ ማሳሰቢያ

 • ከዚህ ጉዳይ መማር የምንችለው ብዙ ነገር አለ፡፡ እንደ አገር በየደረጃው፡ በየመሥሪያ ቤቱ፣ የሚገኙ ባለሙያተኞች እና ነባር ዕውቀት ያላቸው የባሕል ሐኪሞች በወጉ ባለመደማመጥ፣ ባለመተማመን፣ በአንድ ነገር መርህ ሳይዘጋጅ፣ እንዲሁ የዓለም መጨረሻ ስንሆን ይቆጫል፡፡ ዛሬ እንኳን! በዚህ በፈተና ቀን እንኳን!

አርቲሚሲያ የኢትዮጵያ አሪቲ (ነጭ ሪያን)፣ የዱር ጭቁኝን ወዘተን ጨምሮ ሌሎችም  ብዙ ዝርያዎች በአፍሪካ፣ በአውሮፓ እና በኤሽያ አሉት፡፡ ለአጥኚዎችም፣ ለአልሚዎች መረጃ ይሆን ዘንድ ከዚህ ቀጣይ በሆነ ጽሑፍ ላይ ይቀርባል፡፡  ቸር ሠንብቱ፡፡

                                                                

ማጣቀሻዎች፡-

ማጣቀሻ አንድ// https://www.aa.com.tr/en/africa/madagascar-donates-anti-covid-19-drug-to-eq-guinea/1825645             Madagascar  Donetes AntipCOVID-19 drug to Eq.Guines

ማጣቀሻ ሁለት// http://savannanews.com/equatorial-guinea-orders-madagascars-covid-organics-herbal-medicine/         EQUATORIAL Guinea is seeking COVID 19 herbal medicine

ማጣቀሻ ሶስት// በቀለች ቶላ፣ ሕክምና በቤታችን የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና በተፈጥሮ መድኃኒት፣ 6ኛ እትም፣ 2ዐዐ9 ዓ.ም አልፋ አታሚዎች፣ አዲስ አበባ፡

ማጣቀሻ አራት//  ሐንሰ ማርቲን ኸርት (ዶ/ር) እና ኪት ሊንድሴይ  (ዶ/ር)፤ የካቲት 1999 ዓ.ም፤ የተፈጥሮ መድሐኒት ሕክምና በምድር ወገብ ሞቃታማ አካባቢ፤ አናሜድ  ትርጉም ተሾመ ነጋሽ ካሳዬ፤ አዲስ አበባ፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *