‹‹የምርጫው መራዘም ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝ ፈጥሯል››

Views: 614

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት፣ የምርጫ መራዘምን ተከትሎ የገጠመንን ሕገ መንግስታዊ አጣብቂኝ ለመፍታት፤ በፍጥነት መፍትሔ መፈለግ አለብን ሲል ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አስታወቀ፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት ጥናት ሲያደርግ የቆየ መሆኑን የገለጸው ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ፣ በሕገ መንግስቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የስራ ዘመን በተመለከተ (አንቀጽ 58/3) ላይ ማሻሻያ ማድረግ የተሻለው አማራጭ ነው የሚል መደምደሚ ላይ መድረሱን ለኢትዮ-ኦንላይን በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁሟል፡፡

በአሁኑ ጊዜ፣ ቀጣዩ ምርጫ መቼ እና እንዴት ይካሄዳል? በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የስልጣን ዘመኑ ሲጠናቀቅ ሀገር እንዴት ትተዳደራለች? የሚሉ እና ተያያዥ ጥያቄዎች በስፋት እየቀረቡ ይገኛል ብሏል፡፡

እንደ ሀገር ለአጋጠመን ሕገ መንግስታዊ አጣብቂኝ፣ ተገቢ መፍትሔ በጊዜ መፈለግ ያስፈልጋል ሲል ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ  አሳስቧል፡፡

በዚሁ መሠረት፣ በአንቀጽ 58(3)፡ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፤ የስራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል” በሚለው ላይ ማሻሻያ በማድረግ ምርጫው ሊራዘም የሚችልበትን ሕጋዊ መሰረት መፍጠር ያስፈልጋል ሲል ገልጿል፡፡

ይህንን ማሻሻያ ማድረግ ከሌሎች አማራጮች በተሻለ እንደ ሀገር የገጠመንን አጣብቂኝ በቀላሉ አልፈን፣ ሙሉ አቅማችንን ወረርሽኙን ለመከላከል እንድንጠቀም ብሎም አላስፈላጊ የፖለቲካ ቀውሶችን ለማስወገድ ይረዳናል ሲል ምክር ሃሳብ አቅርቧል፡፡

የዓለማችንና የሀገራችን የወቅቱ ዋነኛ የጤና ተግዳሮት በሆነው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት፣ በዚህ ዓመት ይካሄድ የነበረውን ጠቅላላ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጹ ይታወሳል፡፡

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com