ዜና

ገዢ፣ ሻጪ እና ጎረቤታሞች

Views: 1077

ቤቴ ውስጥ ተቀምጫአለሁ፤ ቴሌቪዥን ከፍቼ ስለኮሮና ቫይረስ የሚባለውን እከታተላለሁ፤ ድንገት ጎረቤታችን ተጣራችና ወጣሁ፡፡ ሳፋ ውስጥ ያሉትን በርካታ ድንቾች ታጥባለች፤ ለምን እንደተጣራች አልገባኝም፤ በራፍ ላይ ቆምኩ፤ አየችኝ፡፡

“ምን ተባለ?

“ስለምን”

“ስለ በሽታው ነዋ! ቁጥሩ

“አልጨመረም”

“ስንት ደርሰ”

“ትናንት እንደነገርኩሽ”

“ሂድ ምን ዓይነት ነው አስደነገጠኝ “ኮ”

ተቀመጠች

“ለመሆኑ የሚባለውን ትሰሚያለሽ?”

“ምን ተባለ?”

“ስለ ጥንቃቄው ነው ያልኩሽ”

“ያው ከሰው ነዋ፤ ታውቅ የለ እኔኮ

በቴሌቭዥን ወሬ መስማት ይደብረኛል፡፡

ከሳምንት በፊት አትክልት ተራ ነበረች፡፡ ይዘጋል የሚል ወሬ ስለነገሯት የምትፈልገውን ሸምታ ተመልሳለች፡፡ መራራቁን ብትሰማም፣ እዚያ ስትሄድ ትተዋለች፡፡

እሷ ብቻ አልነበረችም የገዢው ብዛት፣ የደላላው ዓይነት የሻጩ ጩኸት ከድሮው የተለየ ነገር አይታይበትም፡፡ ከአካባቢው እየተሯሯጠ የሚደባለቀው ግርግሩ መሐል የሚገዛውን የሚመርጠው ሁሉ እንዳሻው ተገፋፍቶ እንደተመቸው ተደጋግፎ ታይቷል፡፡

“ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እየተጠጋ ነው የሚያስፈልጋችሁን ገዝታችሁ ግቡ” የተባለ እንጂ፣ መግባቱ የሚታወቅ አይመስልም ነበር፡፡

እነዚህ ሰዎች ማኀበራዊ ርቀትን በምን መንገድ እንደሰሙት ማመን ይከብዳል፡፡

ለምንድነው የሚገዙት? እንዴት ሆነው? መቼ ሊጠቀሙበት? የተነገራችሁን ችላ ካላችሁ የከፋ ጉዳት ላይ ትወድቃላችሁ ከተባሉ በኋላ መድፈራቸው ለምን?

ጐረቤታችንን ተመለከትኳት

“ይሄ ሁሉ ድንች ለምንድነው?”

“ለቤት ነዋ!”

“ድግስ አለብሽ?”

“አንተ ደሞ እየቀለድክ ነው?”

“እንዴት?”

“ከቤት አትውጡ ቢባልስ!”

ሳቅሁ፡፡

“ምን ያስቅሃል?

“የተባለውን ሳትሰሚ ላልተባለው መጨነቅሽ ገርሞኝ ነው”

“ምኑ ነው ያልሰማሁት?”

“እንዴት እንደገዛሽ ታውቂዋለሽ?”

“አሃ አንተ ደሞ እና ባዶ ቤት እንሙት?!”

መቀጠል አልፈለግኩም ልገባ እንደሆነ ነገርኳት፤ አቀርቅራ እያንጐራጐረች ድንች ማጠቡን ቀጠለች፡፡

ቤት ገብቼ ቴሌቭዥን ላይ አፈጠጥኩ፡፡ ተከታትለው የሚቀረቡት ማስታወቂያዎች ነበሩ፡፡

ብዙዎቻችን በዝግጅት ተጠምደን ያሳለፍናቸው ጊዜያትን አስታውሳለሁ፡፡ ወሬው ከየት እንደመጣ አይታወቅም ተናጋሪውም ተብሏል፡፡ ከማለት በስተቀር የሚናገረው የለም፡፡ በትንንሾቹ ለምደን ወደ ትልልቆቹ ተሻግረናል ቀስ በቀስ “ሊጠፋ ይችላል” በሚል ፍርሃት የጀመርነው ተጋፍቶ የመግዛት፣ ገዝቶ የማከማቸት ልምዳችን ዛሬ ሕይወታችንን አሳልፈን ለመስጠት አስገድዶናል፡፡

የተወሰነ ጉዳዮችን ጠይቀው ሌላውን ዘንግተው ለወደፊቱ የሚጨነቁ ጥቂት አይመስሉኝም፡፡ አንዷ ጐረቤታችን ናት

“ስንት ሰው ሞተ?”

“ምንም”

“በጣም የታመሙ አሉ?”

“የማላውቀውን አልጠቁማትም”

“የእኛዎቹ ብዙ ናቸው”

ቁጥሩን እነግራታለሁ፡፡

“የሚጨመር ይመስልሃል”

“አለመጠንቀቅ በእዚሁ ከቀጠለ፡፡”

“ምን ይሻለናል?”

ይደክመኛል፤ በእዚህ ጊዜ እንደ እሷ ቴሌቪዥን ከፍተው የሚመለከቱ የሬዲዮ ጣቢያ መርጠው የሚያዳምጡ ጋዜጣ ገዝተው የሚያነቡ የሚፈልጉትን ብቻ ነው፡፡

ሌላውን እንደቀልድ ከሰው እየጠየቁ ይውላሉ፤ ከሰው እየሰሙ እፎይ ብለው ያድራሉ፡፡ ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ሊገዟቸው የተመ˜ቸውን ፍለጋ ይሯሯጣሉ፡፡

ሰልፉን ሳይሆን፣ መጠጋጋቱን ሳይሆን የሚገዙትን እያሰቡ ይቆያሉ፡፡ የበሽታውን ስጋት ተረድተው ሊገዟቸው የመጡትን ይሸሻሉ፤ ጥሪ የሰማሁ መሰለኝ፡፡ የቴሌቪዥን ድምፅ ቀነስኩ፤ የወንድ ድምፅ ስሜን ተጣራ፡፡

ወጣሁ የግቢያችን ሰው ነው፤ ጐረቤታችን አጠገብ ቆሟል፡፡ በርቀት ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ በእጁ ወደ አንጠለጠለው ጥቁር ፌስታል እያሳየኝ መግዛቴን ጠየቀኝ፤ ውስጡ ምን እንዳለ አላወቅሁም ግራ መጋባቴን ጎረቤታችን አይታለች፡፡

“አልኮሉን ማለቱ ነው”  ገባኝ፡፡

“አመሰግናለሁ ገዝቻለሁ”

“እንግዲህ እንደተባልነው መጠቀም ነው”

“እውነት ብለሃል”

“እዚያማ ጉድ ኮ ነው አይቼ የመጣሁት”

“ምን አየህ?” ጎረቤታችን ጣልቃ ገባች

ቀና ብላ የሚለውን ጠበቀች፡፡

“ሰዎች የሚገዙት ነዋ!”

“እኮ ምን?” የሆነውን ለመስማት የጓጓች ትመስላለች፤

“አንዳንዱ የገዛው ብዛቱ

“ታዲያ ይሄ ምን ይገርማል?!”

ተናዳዳች፡፡

“እንዴት?”

“ቢያልቅስ?

“አሃ አንቺ ምን ሆነሻል ለእነሱ ወይስ ላላገኘው

ነው ንግግርሽ”

“ለእነሱ ነው እንጂ ቤት ተቀመጡ

ቢባል ከየት ያገኛሉ?”

“የለም! የለም! በእዚህ ሰዓትማ መደጋገፉ ነው

የሚበጀው መቼም እንደንግግራቸው ከሆነ ሰዎችን

ለመርዳት ብለው የገዙት አይመሰለኝም”

የሰውዬውን  ባህሪይ ሁላችንም እናውቀዋለን የማይሆን ክርክር አይወድም፤ ይናደዳል፤ ንዴቱ ሲብስ ለዱላ ይጋበዛል፡፡

ጣልቃ ገባሁ፣

የደከመህ ትመስላለህ?”

“ትንሽ”

ከንፈሩን ሲነክስ አየሁት፡፡

ለምን ጐራ አትልም?

“የለም ወደ ቤት ብሄድ ይሻላል”

ገልመጥ አድርጓት አለፈ፤ ወደ ውስጥ ገባሁ፡፡ ከቴሌቭዥኑ ፊት ለፊት ብቀመጥም የማስበው ስለ ሰዎቹ ነበር፡፡

በእዚህ ቀን ሁሉን ረስተው ተሰብስበው ስለሚሸጡት ተገፋፍተው ስለሚሸምቱት፡፡

ሁሉን ረስተው ለሁሉም እንዲዳረስ ከሚከፋፈለው በብዛት ገዝተው ስለሚሸጡት፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com