ዜና

ከነገ ጀምሮ አገር አቋራጭ አቡቶቡሶች የህዝብ ማጓጓዝ አገልግሎት ሊያቆሙ ነው

Views: 154

– ሆኖም፣ ተማሪዎችና የመከላከያ አባላት ለመጓጓዝ ልዩ ፈቃድ አላቸው!
– እገዳው ለሕገ-ወጥ የምሽት መጓጓዣ አገልግሎት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል!

የገዳዩን ቫይረስ ኮሮና (ኮቪደ 19) በፍጥነት መዛመት ለመግታት፣ ክልሎች ለሕዝብ ማመላለሻ ሀገር አቋራጭ አቡቶቡሶች ድንበሮቻቸውን ዝግ ማድረጋቸውን ቢገልጹም፣ ‹‹የኛ ባስ›› ዛሬ ማምሻውን ከትግራይ ክልል ተሳፋሪዎችን ይዞ አዲስ አበባ መግባቱን ከሥፍራው ለማረጋገጥ ችለናል፡፡

ኢትዮ-ኦንላይን ባደረገው ማጣራት፣ ‹‹ሰላም ባስ›› ዛሬ ወደ መቀሌ ጉዞ አለማድረጉን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ ከመቀሌ ተጓዦችን ይዞ ማምሻውን አዲስ አበባ መግባቱን ግን ለመመልከት ችለናል፡፡

በአገር አቋራጭ የሕዝብ ማጓጓዣ አቡቶቡስ ቢሮዎች ዞረን ባደረግነው ቅኝት፣ ከነገ ጀምሮ በልዩ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደማይሰጡ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ለመከላከያ አባላት ብቻ አገልግሎት እንድንሰጠ ልዩ ፈቃድ አለን ሲሉ ለኢትዮ ኦንላይን ዘጋቢ ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአገር አቋራጭ አቡቶቡሶች ጉዞ በድንገት መገታቱ፣ ለሕገ-ወጥ የምሽት መጓጓዣ አገልግሎት ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን ከሥፍራው ለመታዘብ ችለናል፡፡

በሚኒ-ባስ በተለምዶ ‹‹አባዱላ›› በተሰኙ መኪኖች ምሽት (ለሊት) ለመጓጓዝ ለሚፈልጉ ግለሰቦች፣ ደላሎች የጉዞ ሂደቱን ሲያመቻቹ ለመመልከት ችለናል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በሀገራችን መታየት መጀመሩ ከተረጋገጠ በኋላ፣ የፌዴራል መንግሥት ወረርሺኙ በቁጥጥር ሥር እስኪውል፣ ዜጎች በተቻላቸው መጠን በቤት ውስጥ እንዲቀመጡ ለማበረታታት የመንግሥት ሠራተኞች ከቤታቸው ሆነው የሚሰሩበትን እድል ማመቻቸቱ ይታወቃል፡፡

በዚህ የተነሳም፣ ከከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች፣ ከሕክምና ባለሟሎችና ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ውጪ፣ ወደ ክልሎች ለመጓዝ የአቡቶቡስ ትኬት የቆረጡ ዜጎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት መቸገራቸውን ገልጸውልናል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com