‹‹ሩቅ የጠቆምነው ለእኛም አይቀርም››

Views: 73

የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን በስፋት መከሰቱን ተከትሎ የአለም መንግስታት ‹‹ጎመን በጤና›› እንዲሉ የተለያዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቀነሱ አስፈላጊ ከሆነም እንዲገቱ በማሳሰብ ድንገት የመጣብንን ዱብዳ ለመከላከል ትኩረታቸውን አፈርጥመዋል፡፡

ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ድንገት አለምን እያሽመደመዱ ከሚገኙ ነገሮች ሰሞነኛና ዋነኛ ሆኗል፣ የሰዎች ህይወት ለህልፈት እየተዳረገ ነው ፣ ሀያላን ተብለው የተሰየሙት ሀገራት ሳይቀሩ በፍርሀት ውስጥ ይገኛሉ፡፡

በሀገራችንም ይህ አስከፊ በሽታ ለመከላከል ይቻል ዘንድ የመንግስት ሰራተኞችን ቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ መደረጉን ጨምሮ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲዘጉ ተወስኗል፡፡

መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ በማለት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ በማድረግ ላይ ይገኛል ፣ ከተቋማቱም መካከል አንዱ የሆነው በሀገራችን  አንጋፋው የትምህርት ተቋም ‹ አዲስ አበባ›  ዩንቨርሲቲ ቀዳሚው ነው፡፡

የዩንቨርሲቲው ተማሪዎች ከመጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ቤተሰቦቻቸው በመትመም ላይ ናቸው፡፡

እውቀትን ለመገብየት ሩቅ ተጉዘው የመጡ ተማሪዎች ፣ የመመረቂያ ጊዜያቸውን የሚጠባበቁ ሁሉ ከትምህርት ገበታቸው ለመገታት ተገደዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በዩንቨርሲቲው ሰፊ የእውቀት ማዕድን የሆኑ ቤተ-መፅሀፍት ተከርችመዋል፣ የሀገር ታሪክ የያዙ ቤተ-መዘክሮች ተዘክተዋል፣ ስንት የተከበሩና እውቅ ፕሮፌሰሮችና መምህራን ከስራቸው ተስተጓጉለው በቤታቸውም ተቀምጠዋል ፣ በልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫዎች  ኑሮን ለማሸነፍ የሚተጉ ሰራተኞች  ቤታቸው ቁጭ እንዲሉ ተደርገዋል ፣እነዚያ ምሁራን የሚመካከሩባቸው  አዳራሾች  ኦና ሆነዋል፡፡

በዩንቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ በቀስታ ከሚሰሙ የሰዎች   ድምፆች በስተቀር የአእዋፍትና የዛፎች መወዛወዝ ነው የሚደመጠው፡፡ ይህን ስፍራ ያለ ተማሪና ያለ መምህራን ማሰብ ይከብዳል ሆኖም ነገሩ የህይወት ጉዳይ ነውና ግድ ሆኗል፡፡

 

አሁን አብዝተው ሲቀነቀኑ የከረሙ የብሔርተኝነት ፣ የአመፀኝነት፣ የፖለቲካ መዝሙሮች ረገብ ብለው አለም አንድ የስጋት ቋንቋ አንደበቷን ይዟታል ‹‹ኮሮና›› የተባለ አዲስ ቋንቋ፡፡ ይህ ቫይረስ ሃይማኖት ፣ ዜግነት፣ ብሔር፣ አካባቢ፣ እድሜ ፣ ፆታ አይመርጥም፡፡

ስለዚህ ቫይረስ ሁላችንም ልንባንን ይገባል ፤ ብዙዎች በለዘብተኝነት ህይወታቸውን አጥተዋል በጣሊያን በአንድ ቀን የሆነውን ሳንሰማ አልቀረንም ፡፡

እናም የሀገሬ ልጆች ‹‹ ሳይቃጠል በቅጠል ›› እንዲሉ መሰረታዊ ጥንቃቄዎች እናድርግ!! በየሚድያው  ዕለት ተዕለት የሚለፈፈውን እንደ ቀልድ አንቁጠር፣ የንፅህና አጠባበቃችንን እንፈትሽ !!

በሀገራችን የሚታየው የበሽታው ስርጭት በግዜ  አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገ የጣልያንና የእስፔን እጣ ፈንታ መጎንጨታችን አያጠራጥርም ፣ ሩቅ የጠቆምነው ለኛም አይቀርም ፡፡ ይህ ገሀድ ያፈጠጠ ሀቅ ነው!!!

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com