በአማራ ክልል የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ከ126 ሺህ ኩንታል በላይ እህል ለተጠቃሚው እየቀረበ ነው

Views: 67

ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ከ126 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እያቀረበ መሆኑን የአማራ ክልል ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኃይለልዑል ተስፋ እንዳሉት ‹‹እህሉ እየቀረበ ያለው በ43 ዩኒየኖች አማካኝነትም ለመንግስት ሰራተኞች፣ ማረሚያ ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ለሌሎች ተጠቃሚዎችም ነው።››

እየቀረበ ካለው እህል ውስጥም   ጤፍ፣ በቆሎ ፣የምግብ ዘይት፣ በርበሬ፣ የዳቦ  ዱቄት፣ ስንዴና የጥራጥሬ ሰብል  ይገኙበታል።

ጤፉ በገበያ ላይ ካለው ዋጋ የ300 ብር የዋጋ ቅናሽ እንዳለውና ሌሎችም የእህል ዓይነቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ንረቱን ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል።

“አቅርቦት እጥረት እንዳይኖርም በምርት ዘመኑ በዩኒየኖችና ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት 2 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የሰብል ምርት ግዥ እየተፈጸመ ነው “ብለዋል።

አቅርቦቱ ሳይቋረጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ኤጀንሲው ከክልሉ ንግድ ቢሮ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በሽምብጥ ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር የንብረትና ሽያጭ ሰራተኛ ወይዘሮ እማዋይሽ አለነ በበኩላቸው በተያዘው ወር 100 ኩንታል ጤፍ ቀርቦ  3 ሺህ 430 ብር በሆነ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ማህበሩ ምስር፣ ክክ፣ ሩዝ፣ ፓስታና ማካሮኒ  በማቅረብም ለአባሉና አባል ላልሆኑ ተጠቃማዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸጡ መሆኑን አስረድተዋል።

የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ባልደረባ  ወይዘሮ ጥሩየ አንለይ በሰጡት አስተያየት አሁን በነጋዴው በኩል እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ጭማሪ ችግር እንደሆነባቸው  ተናግረዋል።

እሳቸው በመስሪያ ቤታቸው አማካኝነት ከጊዮን ዩኒየን ጋር በተፈጠረ ትስስር ከደመወዛቸው በ3 ወር ተከፍሎ የሚያልቅ አንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ በ3 ሺህ 450 ብር መግዛታቸውን ገልጸዋል።

“ህብረት ስራ ማህበራት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡት ያለው የጤፍ ምርት አነስተኛ ደመወዝ ተከፋይ የሆንን የመንግስት ሰራተኞች ታድጎናል ” ያሉት ደግሞ አቶ ውድይሁን ፈንታሁን ናቸው።

ህብረት ስራ ማህበራቱ ከጤፍ ምርት በተጨማሪ ሌሎች የፋብሪካ ውጤቶችንም በተመጣጣኝ ዋጋ ቢያቀርቡ ህብረተሰቡን ከስግብግብ ነጋዴዎች መታደግ እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በክልሉ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ከአንድ ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላር እርምጃ ተወስዷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com