የእኛ ነገር

Views: 68

(አጭር የጉዞ ማስታወሻ)

ካዛንቺስ ከጓደኛዬ ጋር ቀጠሮ ነበረኝ፤ ጠዋት ላይ አረፋፍጄ ስነሳ ጎረቤቴ እንደልማዷ የምን ተባለ ጥያቄዋን አነሳችልኝ፤ በእኛ ግቢ ይህ የተለመደ ይመስላል፡፡

በግቢው አብዛኛው ነዋሪ ማታ ላይ የውጭ ሀገር ተከታታይ ፊልሞችን እያየ ያመሻል፡፡ ጠዋት ላይ ስለወረርሽኙ ኮሮና ቫይረስ ይጠይቃል፤ ይነገረዋል፡፡ እንደነገሩ ይሰማና ላልሰማው ጨማምሮ ይነግረዋል፡፡

ምሽት ላይ በውጭ ሀገር ፊልም እየተዝናና ያመሻል፤ ሲነጋ ስለቫይረሱ በሰማው ወሬ ትንሽ ይቆዝማል፡፡
ለጎረቤቴ የተባለውን ነገርኳት፤ በተለይ ስብስብ ብሎ መገኘቱ በቀላሉ ለጉዳት እንደሚያጋልጥ አጫወትኳት፡፡ ፈገግ አለች፤ ለምን ፈገግ እንዳለች አልገባኝም፤ ጠየቅኋት፡፡

ስለወረርሽኙ ምንነት ትክክለኛ መረጃ ማግኘት እንዳልቻለች ነገረችኝ፤ ግራ ተጋባሁ፡፡ ከሰዎች የተለያዩ ወሬዎች እንደምትቀበል ገመትሁ፤ ከምታወራው ያወቅሁት እሱኑ ነበር፡፡

ጠዋት ላይ አንዱ በአየር ላይ ሳይሆን፣ በንኪኪ የሚተላለፍ ነው ሲላት፤ ከሰዓት በኋላ ሌላው በአየር ላይ ቆይቶ ይሰራጫል አሉ ይላታል፡፡ ሌላው በዕድሜ የገፉትን እንጂ ወጣቶችን አይነካም ሲላት፣ ከእሱ በኋላ ያገኘችው ትልልቆቹ መትረፋቸውን እንደሰማ ይነግራታል፡፡

ወሬዋን ስትጨርስ አትኩሬ አየኋት፤ የፈራች ትመስላለች፡፡ ትክክለኛውን መረጃ ከየት እንደምታገኝ ልጠቁማት ስጀምር፣ ቀዝቀዝ ያለ ፈገግታ አሳይታኝ ጥላኝ ሄች፡፡

ሰሜን ሆቴል አካባቢ ካለው ግቢያችን ወጥቼ ቁልቁል ወደ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ማዝገም ጀመርኩ፤ ማታ ላይ የተነገረው አካላዊ ፈቀቅታ (በተወሰነ እርቀት መቆም፣ በተወሰነ እርቀት መቀመጥ) ሲነጋ ሰሚ ያገኘ አይመስልም፡፡

ምናልባት እንደ እኛ ግቢ ሰዎች ምሽት ላይ ፊልም አይተው ዘና ብለው የተኙ ይሆናል ብዬ ገመትሁ፡፡ ጥቂት ተራምጄ ደግሞ ፊልም የሚታይባቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተመልካቾቻቸውን ዕድሜ ለማራዘም ከፊልሞች በፊት መግለጫዎች የሚተላለፍበት መንገድ ቢያዘጋጁስ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡

ቁልቁለቱን ጨርሼ ወደ ግራ በመታጠፍ ወደ ፒያሳ የሚወስደውን መንገድ ያዝኩ፤ ከትናንሽ የጫት መሸጫ ቤቶች በራፍ ላይ ደንብ አስከባሪዎች ቆመዋል፡፡
ከእነሱ ራቅ ብለው ከቆሙት ወጣቶች አጠገብ ደረስኩ፤ አንዱ ሌላው ትከሻ ላይ ክንዱን እንዳስደገፊ ያወራሉ፡፡

“የማታውን ሰምተው ነው”
“ማታ ምን ተባለ?
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጫት ቤት ዝጉ ብሎ”
“እና ጫት ከየት ልንገዛ?
“ከእዚሁ ነዋ መቸ አትግዙ አለ?
“እና?
“ጫት ቤት ተሰብስባችሁ አትቃሙ ነው ያለው
“ታዲያ ምን ችግር አለው ቦታ መለወጥ ነው”

ከእነሱ አለፍ እንዳልኩ ሰልፍ ተመለከትኩ፤ መጠየቅ አላስፈለገኝም፡፡ ቫይረሱን ለመከላከል በሸማቾች ማኀበራት አማካኝነት ለሽያጭ የቀረቡትን ለመግዛት የተሰለፉ ነበሩ፡፡
ያ ሁሉ ሰልፈኛ ማታ የተባለውን ያልሰማ ነው ለማለት አልደፈርኩም፡፡ ከወረርሽኙ አስከፊነት ይበልጥ መጠኑን ጠብቀን ተራርቀን መቆም እንዳቃተን አመንኩ፡፡

በተወሰነው ልክ ተራርቆ ማውራት፤ በተወሰነው ልክ ተራርቆ መብላት፤ ተጋፍቶ ከመግባት፣ በአንዴ በተወሰነው ልክ መሰለፍን ቶሎ መልመድ የተቸገርን መሰለኝ፡፡
አቅራቢዎቹም ሲጠየቁ “የመጣውን በአግባቡ ሸጥን ከማለት ባለፈ፣ ገዢውን በአግባቡ ለማስተናገድ አማራጭ አጥተው ይሆን? ወይስ እነሱም መገለጫውን አልሰሙ ይሆን ብዬ አሰብኩ፡፡
አቡነ ጴጥሮስ ሐውልትጋ ስደርስ በስተግራ ታጥፌ ሽቅብ ወደ ላይ ተራመድኩ፤ ዳግማዊ ምኒልክ ሀውልትጋ ስደርስ ዙሪያውን መቃኘት ተያያዝኩ፡፡

አልፎ አልፎ ውሃ የያዙ አነስተኛ በርሜሎች ከላያቸው ወይም ከጐናቸው ሳሙናዎች ተቀምጠውባቸው በየካፌው፣ በየሆቴሉ፣ በየሥጋ ቤቱ በራፎች ላይ ይታያሉ፡፡
ስብስብ ብለው ጋዜጦች ከሚያነቡትና ስብስብ ብለው ከሚያወሩት ሌላ እጆቻቸውን በሳሙና በደንብ ታጥበው ስብስብ ብለው የሚበሉትንም ተመለከትኩ፡፡

የቀጠሮዬ ሰዓት እየደረሰ ነበር፡፡ የካዛንችስ ታክሲ ለመያዝ ቁልቁል ወደ ደጐል አደባባይ መራመድ ጀመርኩ፡፡ ደንብ አስከባሪዎች እየሸሹ ድንገት ብቅ በሚሉ ልብስ ሻጮች መካከለ በክር የተሰሩ የእጅ ጓንቶች የሚሸጡ ነጋዴች ድምፃቸውን ቀንሰው ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ የሚሆን ጓንት በቅናሽ እንደሚሸጡ ይናገራሉ፡፡ አለፍ ስል ሁለት መንገደኞች ስለጓንቱ እያወሩ ነበር፡፡

“ትናንት መግዛቴ በጀኝ አየህ ዛሬ ዋጋውን ጨምረውታል”
“ፋርማሲ ውስጥ የሚሸጡት አይሻልህም ነበር?
“አይ እሱን እንኳን አላምነውም”
“እንዴት?”
“ስስ ነዋ! በእዛ ላይ ሲያደርጉት ይጨንቃል አሉ”
“ ግን ኮ የሹራቡ ጓንት ብዙ ቀዳዳዎች አሉት
“አይ! ያስ ቢሆን የሆነ ነገር ቢያገኘው መበሳቱ ይቀራል?!
ከዚህ በኋላ ያሉትን አልሰማሁም፡፡ ተረኛ ከሆነው የካዛንቺስ ታክሲ ውስጥ ገባሁ፡፡ ስሳፈር መሐል ላይ ካለው ወንበር ሁለት ተሳፋሪዎች ተቀምጠዋል፡፡ ሶስት- ሶስት ሰዎች የሚጭን ነበር፡፡ ዳር ላይ ያለው ተሳፈሪ ከመሐል እንድቀመጥ በምልከት አሳየኝ፡፡ ገባሁ፡፡

ወደ መቀራረቡ ተቀላቀልኩ፡፡ ደክሞኛል የቀጠሮ ሰዓቴ ደረሷል ወይም ሰበቤ ይሆናል፡፡ እኔስ ማን ነኝ? ስንሰለፍ በቀይ ቀለም አስፋልቱ ላይ ተራርቀን እንድንቆም የተሰመረውን ምልክት አይቼ ነበር፡፡ ስንገባ ተራርቀን የምንቀመጥበት ቦታ አላገኘንም፡፡
ታክሲው ጉዞ ጀመረ፡፡ በውስጡ ፀጥታ ሰፍኗል፤ እንደ ቀድሞው ሙዚቃ ማስጮህ ለም፤ የተቀመጡትን ለማየት ሞከርኩ፡፡ አንዳንዶች ተኮሳትረዋል፡፡ የተጠራጠሩ ይመስላሉ፡፡ አጠገቤ ውጭ ውጩን የሚያዩ በእድሜ ገፋ ያሉ ወይዘሮ ተቀምጠዋል፡፡ ይቅርታ ስጠይቃቸው ዞሩ፡፡

“መስኮቱን ብንከፍተው አይሻልም?”
“አስቤው ነበር ግን ንፋስ ሲመታኛ ያስለኛል”
ገባኝ ላስጨንቃቸው አልፈለግኩም፤ ድንገት ከኋላችን ያለው ተሳፋሪ ወፍራም ድምፁን አሰማ፡፡
“መስኮቱን ክፈቱት እንጂ፣ ልታሰጨርሱን ነው!”
ወይዘሮዋ ፈጥነው ከፈቱት፡፡
ብዙም አልተጓዝንም ወይዘሮዋ ማስነጠስ ጀመሩ፤ ተሳፋሪዎች ተቁነጠነጡ፡፡ አንዳንዶቹ አፋቸውን ለመሸፈን ሲሞክሩ አየሁ፡፡ ከእሳቸው ፊት ለፊት የተቀመጠችው እድሜዋ አርባ መጀመሪያ ላይ እንደሆነ የገመትኳት ወይዘሮ እንዴት ተነስታ እንደተቀመጠች ስመለከት ደነገጥኩ፡፡ ካዛንቺስ ደርሻለሁ፤ ወርጄ ጓደኛዬ ወደ አለበት እየተጓዝኩ፣ የሆነውን ሁሉ ሳስታውስ’
ከመንግስት የሚወጡ መግለጫዎች የሚተላለፉበት ሰዓት’ የሚተላፉበት መንገድ ሕብረተሰቡ በየጊዜው እንዴት መጠበቅ እንዳለበት ማዘጋጀት ‘ ስለቫይረሱ በበጎ ፍቃደኞች አማካኝነት ህዝብ ወደተሰበሰበበት ሥፍራ በመገኘት ከጥንቃቄ ጀምሮ ተሰብስቦ መቆም ይሁን መቀመጥ የከፋ አደጋ እንደሚያስከትል መናገር :: የስብሰባው እገዳ በመንግስት ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ሕብረተሰቡ ዝቅ ብሎ መከልከል’ ይህም ዓዋጅ ከማወጅ አልፎ፣ መቆጣጠሩ ቢኖር ብዬ አሰብኩ፡፡ የነገው ሰማይ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com