ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች በቤታቸው እንዲቆዩ ተወሰነ

Views: 60

የኦሮሚያ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዳይስፋፋ በሚል የተወሰኑ የመንግስት ሰራተኞች ከዛሬ ጀምሮ በቤታቸው እንዲቆዩ ወሰነ፡፡

ውሳኔው በስራ ቦታና ትራንስፖርት ላይ በሚፈጠር መጨናነቅ ምክንያት የቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋ የተወሰደ እንደሆነ የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ዛሬ ለሸገር ተናግረዋል፡፡

ሕፃናት ልጆች ያሏቸውና ነፍሰ ጡር እናቶች እንዲሁም ስኳርና ደም ግፊት ያሉ ህመሞች ያሉባቸው ሰራተኞች በቤታቸው ከሚቆዩት መካከል እንደሆኑ ሰምተናል፡፡

እድሜያቸው ለጡረታ የተቃረበ ሰራተኞችም በቤታቸው እንዲቆዩ መወሰኑን አቶ ጌታቸው አብራርተዋል፡፡

በስራ ገበታቸው ላይ የሚገኙ ሰራተኞች ደግሞ በቤታቸው እንዲቆዩ የተወሰኑ ባልደረቦቻቸውን ስራ እንዲሸፍኑ ትዕዛዝ ተላልፏል ብለዋል፡፡

በተለይ ደግሞ በአገልግሎት መስጠት ተግባር የተሰማሩ ሰራተኞች ሀላፊነታቸውን በተጠናከረ መልኩ እንዲወጡ ትዕዛዝ እንደተላለፈ ነግረውናል፡፡

እነዚህ ዜጎች በዚህ ወቅት የሚያከናውኑት ተግባር እንደ ዜግነት ግዴታ የሚቆጠር ነውም ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ወደ ግማሽ ሚሊየን የሚጠጉ የመንግስት ሰራተኞች እንዳሉ የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል ክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል 7 ንዑሳን ኮሚቴዎችን አደራጅቶ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ጌታቸው አብራርተዋል፡፡

እነዚህ ኮሚቴዎች ዝግ ሆነው እንዲቆዩ የተወሰኑና እንደ ምሽት ቤቶች ያሉ ተቋማት ስለመዘጋታቸው እንደሚከታተሉ እንዲሁም አጋጣሚውን በመጠቀም በምርቶች ላይ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን እንደሚቆጣጠሩ ገልጸዋል፡፡

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com