ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በአንድ ወር ውስጥ የኮሮና ቫይረስን አራግፋ ትጥላለች አሉ

Views: 241

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ እስከ ፈረንጆቹ ፋሲካ ድረስ ኮሮናን አራግፋ ጥላ ከቫይረሱ ነጻ ትሆናለች አሉ፡፡

ፕሬዝዳንቱ ይህ ተስፋቸውን ቢናገሩም የኒዮርኩ አገረ ገዢ ግን ወረርሽኙ በግዛታቸው “እንደ ፈጣን ባቡር በፍጥነት እየተምዘገዘገ” መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንቱ በዋይት ሐውስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት የሚቀጥለው ወር መጀመሪያ “መልካም ጊዜ” ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ የፕሬዝዳንቱ ተስፋ የተሞላበት ንግግር የተሰማው የዓለም ጤና ድርጅት አሜሪካ ቀጣይዋ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማዕከል ትሆናለች ብሎ ስጋቱን ካስቀመጠ በኋላ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለፎክስ ዜና ተቋም ማክሰኞ ዕለት እንደተናገሩት ከ20 ቀናት በኋላ፤ ለፈረንጆቹ ፋሲካ ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ ብለዋል።

“በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተዘጉ ተቋማት እከፈታሉ፣ ለፋሲካ ሁሉ ነገር ተከፍቶ የሚታይባት አገር እንድትኖረኝ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

በዚሁ ቃለ ምልልስ ወቅት እንደተናገሩት “ፋሲካ ለእኔ ልዩ ቀኔ ነው። በመላ አገሪቱ ቤተክርስቲያናት በሰዎች ተሞልተው ይታያሉ” ሲሉ ተስፋቸውን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ አገራቸው ዳግም የተዘጉ የንግድ ተቋማት ተከፍተው ወደ ሥራ ካልገባች “ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ድቀት ወይንም ውድቀት ይገጥማታል” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ በመቀጠልም “በርካታ ሰዎችን ልናጣ፣ በርካታ ሺህ ሰዎች ራሳቸውን ሊያጠፉ ይችላሉ። ሁሉም ነገር ሊከሰት ይችላል። አለመረጋጋት ሊከሰት ይችላል” ብለዋል።

በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ወቅትም “ከዋሻው መውጫ ላይ ብርሃን ይታየኛል” ሲሉ ተስፋቸውን ገልፀዋል።

ከዚያም “ውሳኔያችን በጠንካራ እውነታ ላይና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ይሆናል” ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር የኮሮናቫይረስ ግብረ ኃይል አባል የሆኑት ዶ/ር አንቶኒ ፋኡቺ ግን “በኒውዮርክ የሚሆነውን ነገር የሚያይ ሰው ጉዳዩን ቀለል አድርጎ ሊገምት አይችልም ” ሲሉ ተናግረዋል።

አሜሪካ እስካሁን ድረስ 55 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 800 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

በዓለማችን ላይ በአጠቃላይ 420 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 19 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com