የትጥቅ ትግሉን ትታችሁ ኮሮና ቫይረስን በጋራ እንዋጋ

Views: 52
  • መንግሥት እና ኦነግ ሸኔ በትጥቅ ትግል ላይ መሆናቸው ይታወሳል!

በዓለም ዙሪያ ያሉ ሁሉም የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ ወገኖች የትጥቅ ትግላቸውን አቁመው የጋራ ጠላት የሆነውን ኮሮና ቫይረስ እንዲዋጉ የመንግሥታቱ ድርጅት ጥሪ አቀረበ፡፡

በዓለም ዙሪያ ሁሉም የትጥቅ ትግል የሚያደርጉ አካላት በፍጥነት ተኩስ አቁመው የጋራ ጠላት የሆነውን ኮሮና ቫይረስ መዋጋት ላይ እንዲያተኩሩ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

“ቫይረሱ ዜግነት፣ ብሔር፣ ሃይማኖት የማይለይ በመሆኑ ተባብረን በጋራ ልንዋጋ ይገባል” ብለዋል ዋና ጸሐፊው፡፡

ትጥቅ ትግል የሚካሄድባቸው አገራት ውስጥ የጤና ሥርዓቱ ጠንካራ አለመሆኑንና የጤና ባለሞያዎች ቁጥርም ዝቅተኛ መሆኑን ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡

የትጥቅ ትግል አድራጊዎች ከሚገኙባት አገራት መካከል ኢትዮጵያም አንዷ ነች፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ሸምቆ በሚገኘው በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሸኔ እና በሀገሪቱ መንግስት መካከል የሚደረገው የተኩስ ልውውጥ ነው፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት ‹‹የትጥቅ ትግሉን ትታችሁ ኮሮና ቫይረስን በጋራ እንዋጋ›› ማለቱን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ እነዚህ የትጥቅ ታጋዮች ተኩስ አቁመው ብሔር፣ ጾታ፣ ቋንቋ እና ሀይማኖት የማይለየውን የኮሮና ቫይረስን ከህዝቡ ጋር በጋራ እንዲዋጉ የማንቂያ ደውል ነው ተብሏል፡፡

ቫይረሱ ወደ ሀገራችን መግባቱና መሠራጨቱ ከታወቀበት ጊዜ ጅምሮ፣ ኦነግን ጨምሮ የተለያዩ አካላት በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ በተፈጠረው ግጭት የኢንተርኔት አገልግሎት ለረጅም ጊዜ በመቋረጡ ምክንያት ለአካባቢው ማህበረሰብ በቂ መረጃ እየደረሰ እንዳልሆነ በመግለጽ የኢንተርኔት አገልግሎቱን እንዲለቅ ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን በገባበት ሳምንት፣ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ በፋኖ የወጣቶች ትግል አደረጃጀት እና በመንግሥት መካከል የተኩስ ልውውጦች ተደርገው የፋኖ ሦስት ካምፖች ተደምስሰው የሰዎች ህይወት መጥፋቱና አካባቢው ላይ ሥጋት መስፈኑ የሚታወስ ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com