ቤተ-ክርስቲያን ወደ ምዕመኗ በማምራት የማዕጠንት አገልግሎት በመስጠት ላይ ናት

Views: 62
  • ከ 5 መቶ ሺህ በላይ ቀሳውስትና ካህናት በአገልግሎት ላይ ናቸው!
  • ሰዎች በመንፈስ ሳይናወጹ ራሳቸውንና ወገናቸውን ይጠብቁ!

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የኮሮና (ኮቪድ 19) ቫይረስ ወረርሺኝ ሥርጭት ለመግታት በሚደረገው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ላይ፣ ንቁ ተሳታፊ መሆኗን አመላከተች፡፡

በዚህ መንፈሳዊና ሀገራዊ አገልግሎት፣ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሚያገለግሉ ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ቀሳውስት፣ ካህናትና ዲያቆናት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰዎችን መንፈስ፣ አእምሮ እና አካል የሚያጠናክሩና በጤንነት የሚጠብቁ መንፈሳዊ ምክሮችን ትለግሳለች፤ አካባቢን ደግሞ በጸሎትና በማዕጠንት የማወድ አገልግሎት እየሰጠች ፈጣሪን ትማልዳለች ሲሉ በአገልግሎት ላይ ያሉ ካህን ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጸዋል፡፡

ከደንበል እስከ ጎተራ ባለው አካባቢ በልዩ-ልዩ የካህን፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት ስብስብ እየተንቀሳቀሱ መንፈሳዊ የማዕጠንት አገልግሎት ሲሰጡ ያገኘናቸው መንፈሳዊ አባቶች ሳይታክቱ አገልግሎት ሲሰጡና፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ ሰውነታቸውን፣ ልብሶቻቸውንና አካባቢያቸውን (የሥራ/የንግድ ሥፍራቸውን) እንዲያጥኑላቸው ሲጋብዙ ተመልክተናል፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ፣ ከኢትዮጵያ ሃይማኖት የጋራ ጉባዔ፣ ከመንግሥት፣ ከሚመለከታቸው የጤና ተቋማት እና ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን የሰውን ልጅ አካል፣ አእምሮ እና መንፈስ እያወከ የሚገኘውን ተዛማች ወረርሺኝ ለመቆጣጠር እየሰራች ነው ሲሉ በሥፍራው ለነበረው ዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚያገለግሉ ሃይማኖቶች (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ጉባዔ (መጅሊስ)፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ሕብረት) በጋራ በመሠረቱት የኢትዮጵያ የሃይማኖት የጋራ ጉባዔ ላይ በተደረሰበት የጋራ ስምምነት መሠረት፣ ለአገልግሎት እንደሚንቀሳቀሱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህም መሠረት፣ የሀገሪቱ መንግሥት የጤና ሚንስትርና የሕክምና ባለሟሎች በሚሰጡት ሙያዊ ምክር መሠረት፣ ሰዎች የግልና የአካባቢያቸውን ንጽህና በመጠበቅ ጤናቸውንና አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ፣ በአንፀሩም ዝም ብለው በመላ ምት ሽብር እንዳይደናገጡና በመንፈስ እንዳይናወጹ መንፈሳቸውን የማጽናናትና የማጠናከር አገልግሎት በመለገስ ላይ መሆኗን ገልፃለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ በአሜሪካን አገር በተለያዩ ግዛቶች እየተደረገ ባለው የፀረ ኮሮና ቫይረስ ዘመቻ መንፈሳዊ የጸሎትና የማዕጠንት አገልግሎት መስጠቷ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የእርስዎ ጥንቃቄ ለወገንኦት ሁሉ መድህን ነው፤ እጅኦን በሚገባ በሳሙና ይታጠቡ፤ ሳልና ማስነጠስ ሲኖር በማህረብ ወይም በሶፍት ወረቀት አሊያም በክርንኦ አፍና አፍንጫዎን ይከልሉ፤ ሌሎችም ይህንኑ እንዲያደርጉ ይምከሩ፤ በሚንቀሳቀሱበት ሁሉ ማኅበራዊ እርቀት (ፈቀቅ- ይበሉ!) ይጠብቁ፤ ተራርቀው ይቀመጡ፤ ተራርቀው ይሰለፉ፤ ሰዎች ከሚበዙበት ቦታ ራቅ ይበሉ፤ የሰው ልጅ ቀደም ሲል እንዲህ ዓይነት መከራዎችን ተጋፍጦ አልፏል፤ ዛሬም በእርስኦ ጥንቃቄና ትብብር የኮሮና (ኮቪድ 19) ቫይረስ ሥርጭት ተቆጣጥረን እንወጣዋለን፤ እናም በሕይወት እንኖራለን፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com