ለኮርኖ ቫይረስ ፍርሃት መፍትሔ አይሆንም! ይልቅ አማራጭ ሕክምናን በየቤታችሁ ፈልጉ፤ ታገኙማላችሁ! (ክፍል ፩)

Views: 473
 • የእፅዋት እንፋሎት መታጠን (1) የሰንሰን (ስሚዛ) ቅጠል ቀቅሎ መታጠን፣ 
 • የእፅዋት እንፋሎት መታጠን (2) የዳማከሴ ቅጠል፣ የሐረግሬሳ ቅጠል፣ የጽድ እርጥብ ቅጠል፣ የባሕር ዛፍ ቅጠል፣ የጋሜ ቅጠል፣ የግራዋ ሥር፣ ወይም ሌላ ተስማሚ ተክል ቀቅሎ እንፋሎቱን መታጠን …

መነሻ ጉዳይ፡-

ኮሮና ቫይረስ (COVID-19 virus) የተባለ ጉንፋን መሰል በሽታ እንዲህ አስፈሪ በሆነበት ቀን፣ ዝም ብሎ ከመቀመጥ ጥቂት መላ መፈለግ ያሻል፡፡ አያድርሰው እና ቢደርስብን ምን እናደርጋለን? የኮሮና ቫይረስ ስጋት ካለባቸው የውጪ አገራት የመጣ ዘመድ፣ ጓደኛ፣ ቤተሰብ፣ የቢሮ ባልደረባ እስከ ሁለት ሳምንት ተለይቶ ይቆይ ይሆናል፡፡ በዚህ ወቅት ምን ዓይነት ጥንቃቄ ያስፈልጋል? ለመሆኑ ይህ በሽታ ከምን ጋር ተቀራራቢ ነው? እስከ አሁን በበሽታው ይበልጥ የተጎዱት ሰዎች በእድሜ፣ በኑሮ፣ በጤና ሁኔታ፣ በልማድ ምን ይመስላሉ? እስከ አሁን ታመው የዳኑት ሰዎችስ በእድሜ፣ በኑሮ፣ በጤና ሁኔታ፣ በልማድ ምን ይመስላሉ?

ከበሽታው በላይ ፍራቻው ጉዳት አድርሷል፤ ብዙ የተመሳቀሉ የዓለም ክስተቶች ታይተዋል፡፡ በእኛም አገር ብዙ ክስተቶች ሆነዋል፡፡ የፍራቻው መንፈስ የሰውን አዕምሮ ተቆጣጥሮታል፡፡ ፍራቻው ከመጎልበቱ የተነሳ መባል የሌለባቸው ጉዳዮች ተራግበዋል፡፡  አሁን እንደገና ከወር በፊት ያልናቸውን ነገሮች ወይም የተባሉት ነገሮችን ዞር ብለን ስናስበው “ይገርማል” በማለት እራሳችንን ሳንታዝብ አንቀርም፡፡ በዕውነት ግን ፍራቻው ከባድ ነው፡፡ ፍራቻው መኖሩ ለጥንቃቄ ያበረታን እንደሆን መልካም ነው፡፡ በፍራቻው መርበትበት ግን መፍትሔ አያመጣም፡፡

ለኮሮናም ሆነ ለሌሎች ጉንፋን ወይም ኢንፉሌንዛ መሰል በሽታዎች በቤታችን የምናደርገው የመከላከያ ወይም የመታከሚያ ዘዴዎች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በዚህ ሰሞን የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች በአገራችን መገኘታቸውን አስመልክቶ፤ በመንግሥት ሕክምና ተቋማት፣ በለይቶ ማከሚያ (ለይቶ ማቆያ) ቦታዎች የሚደረጉ እርዳታዎች እንዳሉ ሆነው፣ እስከዛሬ ስለ ኮሮና ቫይረስ የተነገሩን የመከላከያ ዘዴዎች እንዳሉ ሆነው፤ በተጨማሪ ሁሉም ሰው በየቤቱ ሊያደርጋቸው የሚችሉ አማራጭ ሕክምናዎች ብዙ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ዛሬ ኮሮና የተባለ ጉንፍን መሰለ እና አደገኛ በሽታ በዓለም ላይ ስለተከሰተ አዲስ እና ተአምራዊ ዘዴ መንገር አይቻልም፡፡ ነገር ግን፣ ቀደም ሲል ለጉንፋን፣ ለኢንፉሌንዛ፣ ለሳል፣ ለአስም፣ ለችኩንጉንያ ወዘተ የነበረንን ብልሃት እንደ አግባቡ መልሰን ልንጠቀም ግድ ይለናል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ፣

 • ከልክ የበዛ ፍራቻ እና መርበትበትን ትተን፣ በአንክሮ ስለ ጥንቃቄው ማሰብ እንዳለብን ለመንገር፤
 • በሌሎች ተደጋግመው ያልተነገሩ የምክር ጉዳዮች እንዳይረሱ ለማድረግ፣
 • በሽታው ቢከሰት እንኳን ከህክምና ተቋማት በተጨማሪ እኛም እራሳችንን ማከም ወይም ማስታመም እንደሚገባን ለማሳየት ነው፡፡

ሀ/ የኮሮና ቫይረስ እና የቻይና የባሕል ህክምና

የበሽታው ተከሰተ በተባለበት ቻይና ውስጥ፡ ባለፈው ታኅሳስ ወር ላይ ለኮሮና በሽታ የተፈጥሮ ባሕላዊ ሕክምና ከዘመናዊ መድኃኒት ጋር በእኩል መጠን ተጠቅመው ጥሩ ውጤት እንደተገኘ አብስረዋል፡፡ ሁቢ ግዛት የጤና ኮሚሽኑ ዋንግ ሄሸንግ እንዳሉት “ውሃን ሆስፒታል ውስጥ የምዕራባውያን መድኃኒት እና የቻይና የባህል መድኃኒትን ያካተተ የህክምና ዘዴ ሥራ ላይ ውሏል”  ያሉት በብሎምበርግ የዜና ወኪል ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ቀጥሎም ሄሸንግ  “ጥረታችን ጥሩ ውጤት አሳይቷል፡፡ ታዋቂ የቻይና የባህል ህክምና ኤክስፐርቶች ምርምር ሊያደርጉ  እና ህክምና ሊሰጡ ወደ ሁቢ ግዛት ተልከዋል”” ሲሉ፤ በመቀጠልም  ፌብሩዋሪ 15 ፕረስ ኮንፍረንስ ላይ ሄሸንግ  “የቻይና የባህል ህክምና በበሽታው ከተጎዱት ውስጥ ለግማሽ ያህሎቹ (5ዐ%) ጠቀሜታ ላይ ውሏል፡፡” ብለዋል፡፡  ለተጨማሪ ገለፃ በዚህ ሊንክ https://www.pharmaceutical-technology.com/news/covid-19-china-traditional-medicine/    ላይ አንብቡ፡፡

በቻይና ውስጥ የባሕል ህክምና ተጠቅመው ውጤት ማግኘታቸው እኛም ስለ አገር በቀል መድኃኒት እንድናስብ መነሻ ይሰጠናል፡፡

ለ/ የኮሮና ቫይረስ በሽታ ምልክቶች   የመረጃ ምንጭ (https://www.who.int/health-topics/coronavirus)

ዋና ዋና ምልክቶች

 1. የመተንፈሻ ሥርዓት መታመም (መለከፍ)፣
 2. ትኩሳት
 3. የጉንፋን ሳል
 4. ትንፋሽ እጥረት እና ለመተንፈስ መቸገር፣ እና ከዚህም በላይ በሽታው ከፀና የሳንባ ምች፣ የኩላሊት ድክመት እና ለሞት ሊያደርስ ይችላል፡፡

በተያያዥ ሌሎች የሚከሰቱ የበሽታው ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ለምሳሌ

 • የምግብ በሆድ ውስጥ አለመፈጨት
 • ማስመለስ
 • ተቅማጥ
 • ለምግብ ፍላጎት ማጣት
 • የነርቭ ህመም
 • የራስ ህመም
 • የማየት ችግር
 • የዓይን መለብለብ ችግር

በሽታው በእድሜ በገፉ አረጋውያን እና በሌሎች በሽታዎች በተጎዱት ላይ ይበረታልም ተብሏል፡፡

 የበሽታውን ምልክቶች ተከትለን የሚያሽሉ ነገሮችን ስለመጠቀም፡፡

1. ለመተንፈሻ ሥርዓት መለከፍ እና ለጉንፋን ሳል

1.1 የመድኃኒት እፅዋት በውሃ እየቀቀሉ እንፋሎቱን በቀን 4 ጊዜ ወይም የበለጠ ጊዜ መታጠን፣

 • የእፅዋት እንፋሎት መታጠን (1) የሰንሰን (ስሚዛ) ቅጠል ቀቅሎ መታጠን፣  ስለሂደቱ በዚህ ሊንክ https://ethio-online.com/archives/7470  ላይ አንብቡ፡፡
 • የእፅዋት እንፋሎት መታጠን (2) የዳማከሴ ቅጠል፣ የሐረግሬሳ ቅጠል፣ የጽድ እርጥብ ቅጠል፣ የባሕርዛፍ ቅጠል፣ የጋሜ ቅጠል፣ የግራዋ ሥር፣ ወይም ሌላ ተስማሚ ተክል ቀቅሎ እንፋሎቱን መታጠን፡፡

ማሳሳቢያ፣

 • እነዚህንም ሆነ ሌሎች ተክሎች ለመታጠን በተቻለ መጠን መቀቀያው ዕቃ ሸክላ መሆን አለበት፣ በተለይ ሐረግሬሳ በብረት መቀቀል የለበትም፡፡
 • መፍላት ከጀመረ ከ1ዐ ደቂቃ በኋላ ማውረድ፣ ከላይ ፎጣ ወይም ጋቢ ተሸፋፍኖ እንፍሎቱን በአፍ እና አፍንጫ ለ1ዐ ደቂቃ ያህል ወይም የቻሉትን ያህል መሳብ ነው፡፡
 • የታጠኑት ቀን ከሆነ ለጥቂት ሰዓት ተሸፋፍኖ መተኛት፣ ወድያውም ትኩስ ሻይ፣ ሾርባ፣ አጥሚት፣ ወይም የሞቀ ውሀ አንድ ኩባያ ያህል መጠጣት፡፡ ለሥራ የሚነሱ ከሆነ እጅግ ባልቀዘቀዘ  ውሃ ፊትን መታጠብ ነው፡፡
 • የሚታጠኑት ማታ ከመኝታ በፊት ከሆነ፣ ከታጠኑ በኋላ የተገኘውን ጠጥተው መተኛት፣ ለሌትም ቢሆን ትኩስ ነገር መጠጣት እና ጠዋት ገላን በሞቀ ውሃ መታጠብ ነው፡፡   

1.2 የእፅዋት ሻይ በትኩሱ መጠጣት

 • የእፅዋት ሻይ መጠጣት (1)፣ የዳማከሴ ሻይ ወይም የጨሞ አገራዊ ሻይ

እንዴት እንደሚዘጋጅ በዚሁ አምድ ላይ ሀገራዊ ሻይ ለጉንፋን በሚል በዚህ ሊንክ  https://ethio-online.com/archives/5306  ላይ በሰፊው አንብቡ፡፡

 • የእፅዋት ሻይ መጠጣት (2)፣ የበሶቢላ ሻይ፣ የግራዋ ሻይ (bitter leaf) ፣ የዝንጅብል ሻይ፣ የእርድ ሻይ፣ የነጭ ሽንኩርት፣ የፓፓያ ቅጠል፣ የአስማ ዊድስ ሻይ፣ እንዴት ማዘጋጀት እንደምትችሉ በዚህ ሊንክ https://ethio-online.com/archives/5455   ላይ እያንዳንዱ በምስል ስለተገለፀ አንብቡ፡፡
 • የእፅዋት ሻይ መጠጣት (3)፣ የግዛዋ ሻይ፣ ግዛዋ በብዙ ነገሩ እጅግ የታመነበት መድኃኒት ነው፡፡ ለዚህ ለዛሬው መከራ ጊዜዋ ተመራጭ ሆኖ ቢገኝ አይገርምም፡፡ በዚህ https://ethio-online.com/archives/7776     ሊንክ ላይ አንብቡ፡፡

ማሳሰቢያ፡-

የተለመደውን ቀይ ሻይ በስኳር እና ጥቁር ቡና በስኳር መደጋገም ይቅርባችሁ፡፡ የሚሻለው ከእነዚህ ከላይ ከተነገሩት ውስጥ አገር እና ቤት ያፈራውን ያለ ስኳር ወይም በማር መጠጣት ነው፡፡

1.3 በቂ ፈሳሽ መጠጣት

 • ንፁህ ውሃ ቢቻል ሞቅ አድርጎ የሎሚ ውሃ ጨምቆ መጠጣት፣
 • ከተገኘ አዘውትሮ የማር-ውሃ ላይ የሎሚ ውሃ ጨምቆ መጠጣት
 • የጤና አዳም ፍሬ አብሮ የተወቀጠ የሱፍ ውሃ መጠጣት፤
 • የኑግ ውሃ በማር መጠጣት፣
 • በአንድ ብርጨቆ ውሃ ላይ አንድ ማንኪያ ጥሬ ፌጦ (ያልተወቀጠ) በትኖ ማሳደር፣ ጧት እንደ ተልባ መምታት፣ ጨው እና የሎሚ ውሀ አክሎ በሳምንት ሶስት ቀን መጠጣት፡፡

1.4 ተጨማሪ ማባያዎች

ከታች ያሉት ተጨማሪ ማባያዎች ከዋናው ምግብ ጋር እንደ መድኃኒት የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ከተነገሩት ውስጥ በአንድ ጊዜ አንዱን ብቻ መጠቀም ይሻላል፣ ከበዛ ጨጓራን ይጎዳል፡፡

 • ሁለት ፍንካች ነጭ ሽንኩርት አድቅቆ መክተፍ፣ ከሱፍ ውሃ፣ ጨው እና የሎሚ ውሃ ጋር ቀምሞ በእንጀራ መመገብ፤ በቀን ሁለት ጊዜ በቂ ነው፡፡
 • አንድ የሾርባ ማንኪያ የፌጦ ዱቄት (Garden cress )፣ በሎሚ ውሃ እና ጨው ለውሶ በእንጀራ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ፤
 • የተቀቀለ የባቄላ ጉንቁል ላይ የፌጦ ዱቄት፣ ጨው እና ትንንሽ ቃሪያ አድርጎ በቀን አንድ ጊዜ መብላት፤
 • አንድ ማንኪያ የጥቁር አዝሙድ ዱቄት በውሃ ለውሶ በእንጀራ መብላት፤
 • በአረንጓዴ ቃሪያ ወይም በቀይ ቃሪያ የተዘጋጀ ዳጣ (በሌላ አጠራር ቆጭቆጫ) በእንጀራ መብላት፡፡

2. ትኩሳትን ማስታገስ

በማንኛውም ህመም ቢሆን ትኩሳት ሲከሰት ቶሎ ማስታገስ ያስፈልጋል፡፡ በኮሮና ምክንያት ትኩሳት ቢከሰት ለምሳሌ እንደዚህ ማስታገስ ይቻላል፡፡

2.1 እርጥብ የጤና አዳም ቅጠል ለማንኛውም የትኩሳት ህመም ፍቱን ነው፡፡ የጤና አዳም ቅጠል  አንድ ጭብጥ ያህል በማሽን መፍጨት ወይም በቡና ሙቀጫ መውቀጥ፣ አንድ ብርጭቆ ለብ ያለ ውሃ ጋር መዘፍዘፍ፣ ትንሽ አቆይቶ መጭመቅ፣ ይህን ጥላይ ውሃ ከእግር ጀምሮ፣መቀባባት፣ መላው አካል፣ ሆድ፣ ጀርባ፣ አንገት ፊት እና እራስ ድረስ መቀባባት ነው፡፡ ከዚያም ሳሳ ያለ ለብስ ለብሶ ጥቂት መቆየት፡፡ ትኩሳቱ ሲወርድ ገላን በሞቀ ውሃ መታጠብ እና እረፍት ማድረግ፡፡

2.2 የአብሽ ዱቄት አንድ ስኒ ያህል በአንድ ሊትር ውሃ ላይ ነስንሶ፣ መምታት እና በሊጥ መልክ ማዘጋጀት ቀጥሎም መላ ሰውነትን መለቅለቅ ትኩሳትን ያበርዳል፡፡ ካስፈለገ እራስን መለቅለቅ፣ ቅዝቃዜን ይስብና ሰውነትን በረድ ያደርጋል፡፡ ቆይቶም በሞቀ ውሃ ገላን መታጠብ እና እረፍት ማድረግ ነው፡፡

2.3 እርጥብ የኒም ቅጠል ወይም የሚሊያ ቅጠል በቅርበት የተገኘውን ግማሽ ኪሎ ያህል መውቀጥ፣ ሞቅ ባለ ውሃ ውስጥ የተወቀጠውን እና ጨው ዘፍዝፎ በዚህ ውሃ ጥቂት ጊዜ ተነክሮ መቆየት እና በዚሁ ውሃ ሰውነትን በየቀኑ መታጠብ ወይም በቀን ሁለት ጊዜ መታጠብ ቀጥሎም የወይራ ዘይት ሰውነትን መቀባት ይረዳል፡፡ ነገር ግን ዘወትር እርጥብ ቅጠል ለማግኘት ካልተቻለ ከሚገኝበት ቦታ ሰብስቦ ደረቁን በመቀቀል መጠቀም ይቻላል፡፡ በድሬዳዋ ከተማ የሚገኘው

3. የምግብ በሆድ ውስጥ አለመፈጨት፣ ማስመለስ፣ ለምግብ ፍላጎት ማጣት ሲከሰት

የዝንጅብል ሻይ መጠጣት፣ አብሽ መጠጣት፣ ወይም ሌሎች ለምግብ ስልቀጣ የሚረዱ ምግቦች እና መጠጥ መጠቀም ነው፡፡

ስለ አብሽ ጠቀሜታ በዚህ ሊንክ ላይ  https://ethio-online.com/archives/2359    አንብቡ፡፡

ሐ/ ለይቶ ማከሚያ (ማቆያ) ውስጥ ወይም በራስ ቤት ውስጥ (ቢቻል ለብቻ ክፍል ውስጥ) በሚቆዩበት ጊዜ

ለኮሮና ቫይረስ ተብሎ የሚሰጥ መደበኛ  መድኃኒት ካለ በአግባብ እየወሰዱ፣ የሚነገረውንም ምክር እየተገበሩ፣  በተለምዶ ለጉንፋን ከሚደረገው በበለጠ ጥንቃቄ የተለያየ ዘዴን በማጣመር እራስን ማከ ም፣ ወይም የቤተሰብ አባልን ማከም ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የሚቻለው ከሆነ ታማሚው ለራሱ፣ (የማይቻለው እንደሆን አስታማሚዎች ለራሳቸው ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረጉ ይህን በማድረግ ያስታምሙ)

 • ጠቃሚ የእፅዋት እንፍሎት እየታጠኑ፣ (ባህር ዛፍ ቅጠል፣ ሰንሰል፣ ዳማከሴ፣ ወዘተ) ይቆዩ፣
 • በቂ የሞቀ ውሃ እየጠጡ (በቀን ከ 3 እስከ 4 ሊትር) በሽታውን ያስታግሱ፣
 • የእፅዋት ሻይ ያለስኳር በማር እየጠጡ፣ (ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሱትን) ይቆዩ፤
 • ጠቃሚ አትክልት (ነጭ እና ቀይ ሽንኩርት፣ ጎመን፣ ቃሪያ፣ ዝንጅብል፣ ብሮኮሊ ወዘተ) ይመገቡ፤
 • እንደየ ሰው ተስማሚ ፍራፍሬዎችን ይመገቡ፣
 • ክፍላቸውን በመድኃኒት እፅዋት በጭስ መልክ እያጠኑ፣(በወይራ፣ ጡንጅት፣ ግዛዋ፣ እጣን፣ቀበርቾ ወዘተ ) ይቆዩ፤ ይህም በአየር ላይ ያሉትን ቫይረስ ለማዳከም ይረዳል፡፡
 • ጠቃሚ አገራዊ ምግቦች እየተመገቡ (ጤፍ፣ ገብስ፣ ኦትስ፣ ዳጉሳ፣ ባቄላ፣ ሽንብራ ወዘተ) እራሳቸውን ያስታምሙ፤
 • የጤና ቀውስ ከሚያስከትሉ ልማዶች (ሲጋራ፣ አልኮል መጠጥ፣ ጫት ወዘተ) ያድቡ፣
 • የሰውን በሽታ የመከላከል አቅም ስለሚያዳክሙ ስኳር እና ማንኛውም ጣፋጭ መጠጥ አይጠቀሙ፣
 • የፍርኖ ዱቄት ምግቦችን እና የታሸጉ አልሚነት የሌላቸው ምግቦችን ይተው፣
 • ጥሬ ስጋ፣ ያልተፈላ ወተት፣ ጥሬ እንቁላል አይመገቡ፣
 • ወድያው የተዘጋጁ ምግቦች እና ትኩስ ምግብ እንጂ ቀዝቃዛ ምግብ እና መጠጥ አይመገቡ፣
 • ቀድሞ ለሌላ ህመም የሚወስዱት የተፈጥሮ መድኃኒት ወይም ዘመናዊ መድኃኒት ካለ ሳያቋርጡ በአግባቡ ይጠቀሙ፡፡

በእነዚህ እና ሌሎችም እራሳቸውን ማስታመም ይጠቅማቸዋል፡፡

በክፍል ሁለት ቀጣይ ምክሮች ይኖራሉ፡፡  እግዚአብሔር በማያልቀበት ምህረቱ አብዝቶ ይጠብቀን፡፡

ማጣቀሻ፣

በቀለች ቶላ፣ 2ዐዐ9 ዓ.ም ህክምና በቤታችን፣ የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና በተፈጥሮ መድኃኒት፣ 5ኛ እትም፣ አልፋ አታሚዎች፣ አዲስ አበባ፡፡

ፎት፡ https://m.dw.com/image/52344012_101.jpg

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com