ዜና

ኅዳጣን ሲባል…

Views: 109

ረቡዕ ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ምዕራብ አርሲ ዶዶላ፤ በዘርና በሃይማኖት ማዕከልነት የተሰባሰቡ ወጣቶች ‹‹መጤ›› ባሏቸው ዜጎች ላይ የጅምላ ጥቃት መፈጸም ጀመሩ፡፡ በዚህ የተደናገጡት የጥቃት ሰለባዎች ለአካባቢው የመንግሥት አካላት የ‹‹ድረሱልን›› ጥሪ ቢያቀርቡም፤ በጎ ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡

በብሔርና በሃይማኖት ልዩነት ሳያደርግ በግዛት ወሰኑ የሚኖሩ ዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማስከበር ኃላፊነት ያለበት ምድራዊው መንግሥት፣ ጥበቃ ሊያደርግላቸው ፈቃደኛ ባለመሆኑ፤ የሰማያዊውን መንግሥት ከለላ ሽተው ከመኖሪያ ቀዬአቸው በመሰደድ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ለመጠለል ተገድደዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ መከሰት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዜጎች ‹‹መጤ›› እየተባሉ ሲገደሉ፣ ለዘመናት ከኖሩባቸው ቀዬዎች ሲፈናቀሉና ሀብት ንብረታቸው ሲዘረፍ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉ የመንግሥት አካላት ጉዳዩን በቸልታ ሲመለከቱ፣ ከዚያም አለፍ ሲል የድርጊቶቹ አስተባባሪዎችና ፈጻሚዎች ሆነው መቆየታቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

የ‹‹መጤ›› እና የ‹‹ተወላጅ›› ፍረጃ ይበልጡን እንዲገንን በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ዋነኛ መንሥዔ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል አንዱ የኢፌዴሪ አባል ክልሎች የተዋቀሩት ብሔርን መሠረት ባደረገ አከላለል መሆኑ ነው፡፡

ግለሰቦችን ሰው በመሆናቸው ሳይሆን በተወሰነ ቡድን አባልነታቸው ፈርጆ እውቅና የሚሰጠው ብሔርን መሠረት ያደረገ የክልል አወቃቀር በአንድ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን የክልሉ ‹‹ባለቤቶች›› እና ‹‹መፃተኞች›› አድርጎ ይከፋፍላል፡፡ በዚህም ምክንያት በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ነገር ግን የክልሎቹ ‹‹ባለቤቶች›› ተደርገው የሚታሰቡት ብሔሮች ተወላጆች ያልሆኑ ዜጎች ኅዳጣን ከመሆን አልፈው በክልል ሕገ-መንግሥቶች ዕውቅና ተነፍጓቸዋል፡፡

በአንድ ብሔር በተሰየሙ ክልሎች የሚኖሩ ኅዳጣን በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ዕውቅና የተሰጣቸው የመምረጥና የመመረጥ፣ የእኩልነት፣ የመዘዋወር፣ የመደራጀት፣ በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብቶቻቸውን ሲገፈፉ ይስተዋላል፡፡

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት ‹‹ማይኖሪቲስ›› በሚል ርዕስ ባወጣው ጽሑፍ በዓለም ላይ የሚገኙ አገራት በጠቅላላ በብሔር፣ በጎሣ፣ በሃይማኖት ወይም በቋንቋ ኅዳጣን የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አካትተው የያዙ መሆናቸውንና እነዚህ ኅዳጣን የየማኅበረሰቦቻቸውን ብዝኃነት የሚያበለጽጉ መሆናቸውን ያስታውሳል፡፡ ምንም እንኳ በሁሉም ክፍለ ዓለማት የተለያዩ ኅዳጣን ቢገኙም፣ ብዙዎቹን የሚያመሳስላቸው ጉዳይ በአገራቸው ጉዳይ የመገለልና መድልዎ ሰለባዎች መሆናቸው ነው፡፡

እ.ኤ.አ ከ2008 – 2014 ዓ.ም በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የነበሩት ደቡብ አፍሪቃዊቷ የሕግ ምሁር ቫኒተምፒሌይ በ2009 ዓ.ም የተከበረውን የሰብዓዊ መብቶች ቀን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ በሁሉም ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ኅዳጣን ለሥጋት፣ ለመድልዎና ለዘረኛነት ተጋላጮች ናቸው፡፡ እንዲሁም፣ በሚኖሩባቸው አገራት ብዙኃኑ በሚሳተፉባቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና የባሕል ማበልጸጊያ እንቅስቃሴዎች ሙሉ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ይገለላሉ፡፡

የሰብዓዊ መብቶችና ለኅዳጣን የሚደረገው የሕግ ጥበቃ ዋነኛ ዓምዶች ከአድልዎ ነጻ የመሆንና የእኩልነት መርሖዎች ናቸው፡፡ እነዚህ መርሖዎች ከሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች አኳያ ለሰዎች ሁሉ ተግባራዊ የሚደረጉ ሲሆኑ በዘር፣ በቆዳ ቀለም፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በብሔር ላይ ተመሥርተው የሚፈጸሙ መድልዎችን ይከለክላሉ፡፡

እነዚህን ሁለት መርሖዎች በማክበር የኅዳጣንን በውሳኔ የመስጠት ሂደት ውስጥ የመሳተፍ መብት ጨምሮ ለበርካታ የሰብዓዊ መብቶች መከበር አመቺ ሁኔታን መፍጠር ይቻላል፡፡

የኅዳጣን መብቶች መከበር በአንድ አገር ውስጥ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለዘላቂ ሰብዓዊ ብልጽግና፣ ለሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ የእነርሱን ውጤታማ ተሳትፎ ማረጋገጥና የሚፈጸምባቸውን መገለል እንዲያበቃ ማድረግም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችን በማክበር ብዝኃነትን እንደ ጸጋ መቀበል ይጠይቃል፡፡

የሲቪልና የፖሊቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 27 ለኅዳጣን መብቶች ጥበቃ ያደርጋል፡፡ በጎሣ፣ በሃይማኖት ወይም በቋንቋ ላይ የተመሠረቱ አናሳ ማኅበረሰቦች ባሉበት አገር ውስጥ የእነዚህ አባል የሆነ ሰው ከሌሎች የማኅበረሰቡ አባላት ጋር በባሕሉ እንዳይጠቀም፣ በሃይማኖቱ እንዳያምን ወይም አምልኮውን እንዳይፈጽም፣ ቋንቋውን እንዳይጠቀምበት መብቱ ሊገፈፍ እንደማይችል በቃልኪዳኑ ላይ ሠፍሯል፡፡

ከሁሉ በላይ ግን አገራት ተገቢውን የሕግና ሌሎች እርምጃዎችን በመውሰድ የኅዳጣንን መብት እንዲያስከብሩ መመሪያ ሆኖ ሊያገለግል የሚችለው የተመድ የኅዳጣን መብቶች መግለጫ ነው፡፡ የመግለጫው አንቀጽ አንድ ‹‹መንግሥታት በግዛት ወሰኖቻቸው የሚገኙ ኅዳጣንን የብሔር፣ የባሕል፣ የሃይማኖት እንዲሁም የቋንቋ ማንነት መጠበቅና ይህ ማንነታቸው የሚጎለብትበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለባቸው፡፡›› በማለት ይደነግጋል፡፡

ምንም እንኳ፣ ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ብዝኃነትን ለማስተናገድና የሕዝቦችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለማስከበር ምቹ መደላድል ስለሚፈጥር ከሌሎች የመንግሥት አወቃቀር ዓይነቶች ይልቅ ተመራጭ ቢሆንም፣ በጥንቃቄ ሊያዙ የሚገባቸው ጉዳዮችን አስከትሎ የሚመጣ ነው፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ የኢኮኖሚና የፖሊቲካ ዕድሎችን ለመቆጣጠር በሚደረግ ፉክክር የተነሣ በክልል ተወላጆችና ‹‹በመጤዎች›› መካከል ግጭቶች ሲከሰቱ ታዝበናል፡፡

2012 ዓ.ም የምርጫ ዘመን ነው፡፡ የዘንድሮው ምርጫ እስካሁን እንዳየናቸው ምርጫዎች የአንድ ወገን የበላይነት ወይም ጠቅላይነት የሚንጸባረቅበት እንደማይሆን ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡ የመንግሥት ሥልጣንን ለመያዝ የሚደረገው ፉክክር በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ብቻ ሳይሆን ድርጅቶቹ ‹‹ይወክሏቸዋል›› ተብለው በሚታሰቡ ማኅበረሰቦችም መካከል ጭምር እየሆነ መምጣቱን እየተመለከትን ነው፡፡

በዚያውም ልክ ደግሞ፣ ፓርቲ አከል የሆኑ ግለሰቦች በፖሊቲካው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉበትን ዕድል አግኝተዋል፡፡ በጣም አሳሳቢው ጉዳይ የፖሊቲካ ድርጅቶቹ ፉክክር ማየል ወይም የተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች መግነን ሳይሆን፣ ከእነዚህ የፖለቲካ ዘዋሪዎች ብዙዎቹ ትኩረት በሚያደርጉባቸው አካባቢዎች ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚጠቀሙበት መንገድ ከአድልዎ ነጻ የመሆንና የእኩልነት መርሖዎችን በመጣስ ኅዳጣንን ለጥቃት የሚያጋልጥ መሆኑ ነው፡፡

ስለሆነም፣ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት አካላት እንዲሁም የፖለቲካ ተዋንያን በዓለም አቀፍ ቃል ኪዳኖችና በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት እውቅና የተሰጣቸውን ሰብዓዊ መብቶች በማክበር ‹‹ወገኔ›› ብለው የሚቆጥሩት ብሔር ተወላጅ ያልሆኑ ዜጎችን በተለይም ኅዳጣንን ከጥቃት እንዲከላከሉ ማሳሰብ ግብዝነት አይሆንም፡፡ ሠላም!!!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com