ዜና

“ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አስተማሪ የመዋቅር ለውጥ አድርገናል” ዐብን

Views: 464

ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች አስተማሪ የሆነ የመዋቅር ለውጥ አድርገናል ሲል የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዐብን) ፓርቲ አስታወቀ፡፡

ፓርቲው በጽሕፈት ቤቱ ዛሬ የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳለው ከዚህ በፊት በብሔራዊ ምክር ቤት የነበረውን አሰራር ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ መቀየሩን ገልጾ፤ ይህም የሆነበት ምክንያት ከዚህ በፊት የነበረው አሰራር በየዞኖቹ የሚገኙ የፓርቲው አባላት ገድቦ ስለነበር፣ እሱን ለማስቀረት እንደሆነ የፓርቲው አዲሱ ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ ተናግረዋል፡፡

ይህንን የመዋቅር ለውጥ ለማምጣት የአንበሳውን ድርሻ የወሰዱት የቀድሞ የዐብን ሊቀመንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) እንደሆኑ አቶ በለጠ ጠቁመው፣ ላደረጉት የለውጥ እንቅስቃሴ በፓርቲው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

አዲሱ ማዕከላዊ ኮሚቴ በሀምሳ አባላት የተዋቀረ ሲሆን፣ አስራ ሶስት የነበረውን የስራ አስፈጻሚ አባላትን ለስራው ቅልጥፍና ሲባል ወደ ዘጠኝ እንደተቀነሰ ተጠቁሟል፡፡

የቀድሞቹ ስራ አስፈጻሚ አባላት አሁን በፓርቲው በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንደሚያገለግሉ የተናገሩት አቶ በለጠ፣ ይህ ለውጥ ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያትም የፖለቲካ ትግል ወቅቱን የጠበቀ መሆን ስላለበት ተከታታይ ለውጥ በማድረግ የፖለቲካ ትግሉ በሚፈልገው አዲስ መንገድ ለመሄድ ነው ብለዋል፡፡

በሰኔ 15ቱ ባለስልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ በማረሚያ ቤት የቆዩት የዐብን አመራሮች ክሳቸው ተነስቶ በምህረት ከማረሚያ ቤት መውጣታቸው እንዳስደሰታቸው የተናገሩት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር መሀመድ ‹‹አባላቶቻችን ለእስር የተዳረጉት ዐብንን ጠልፎ ለመጣል እና ለማዳከም ሆን ተብሎ የተደረገ በሚመስል መልኩ ነው እስካሁንም በእስር የቆዩት›› ብለዋል፡፡

ዐብን ጽንፈኛ ድርጅት ነው ተብለው ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ሊቀመንበሩ ሲመልሱ ‹‹ጽንፈኛ ናቸው ተብሎ የሚነገረው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ነው፤ እኛ ስንደራጅ የዐማራን ህዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ እና ድምጹን ለማሰማት ነው፤ ይህ ማለት ግን ለሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ መልስ እንዲሰጥ አንታገልም ማለት አይደለም›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ ከኢትዮጵያ የጠበበ ራዕይ የለንም ያሉት አቶ ጣሂር፣ የዐማራ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች እኩል ተጠቃሚ መሆን አለበት ነው እንጂ የምንለው ፍላጎታችንም ራዕያችንም ጽንፈኝነት አይደለም ብለዋል፡፡

ትግላችን የዐማራን ህዝብ ማዕከል አድርጎ ነው የተነሳው ዐማራ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ጥያቄ ይታገላል ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

ዐብን በዛሬው መግለጫ እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እና ከጎረቤት አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ያሳስበናል ያለ ሲሆን፣ ሁሌም ቢሆን መንግሥት በሚያደርጋቸው ድርድርና ውይይት የሀገራችንን ጥቅም ያስከበረ መሆን አለበት ብሏል፡፡

አፍራሽ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ተገኝተን አናውቅም ያለው የዐብን  መግለጫ፣ በእንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች ላይ እንደምንሳተፍ ተደርጎ በተለያዩ አካላት ብዙ ፕሮፓጋንዳ ይደረግብናል፤ እኛ ግን በእንደነዚህ ዓይነት አሉባልታዎች አንረታም ብሏል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com