ዜና

መልካም ዓድዋ፤ ክብር ለዐርበኞቻችን!

Views: 111

(ይህ ጽሑፍ፣ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሰብሳቢ አቶ መላኩ አላምረው ካቀረቡት ንግግር ላይ ተቀንጭቦ የቀረበ ነው፡፡)

… በኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሀገረ-መንግሥት ታሪክ ውስጥ ህዝብ- ከህዝብ የሰበረም ሆነ ያሰበረ አናውቅም፤ የሰበረም ሆነ የተሰበረ ማኅበረሰብ የለም፤ ወይም የሰበረም አሊያም የተሰበረ እና የሚሰበር ነፍጠኛ የለም፤ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የተሰበረ ህዝብ አናውቅም፡፡

ሆኖም፣ የተሰባበረች አገርን ጠግነው በክብር ያቆሙ ነፍጠኞች ነበሩ እንጂ፣ የትኛውንም ህዝብ የሰበሩም ሆነ በማንኛውም አካል የተሰበሩ ነፍጠኞች አልነበሩም፤ የሉም፤ አይኖሩም። ለአገር ዳር-ድንበር መከበር አጥንታቸው የተሰበረና ደማቸው የፈሰሰ እንጂ፣ የራሳቸውን ወንድሞች የሰበሩ ነፍጠኞች የሉም። አይኖሩም፡፡

እኛ የምናውቀው ነፍጠኛ መይሳው አፄ ቴዎድሮስን ነው። እርሱ ቅስሟ ተሰባብሮ የተበተነች አገር ለመሰብሰብ ላይ-ታች ሲዋከብ በገዛ ወገኑ ክህደት በመስዋዕትነት የነፍሱን ምድራዊ ጉዞ ሰብሮ ወደ ሰማይ ከፍታ በመሸኘት፣ ራሱን ለአገር ክብር የሰጠ የምንጊዜም ጀግናችን፣ የልባችን ንጉስና የእጃችን ሠንደቅ ነው።

እኛ የምናውቀው ነፍጠኛ ተሰባብራ የተበታተነች አገር ጠጋግነው የመላው ኢትዮጵያዊያንን ወኔ ሰብስበው፣ በአድዋ ተራሮች ላይ የፋሺስትን ቅስም ሰባብሮ አረንጓዴ-ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ዓላማን በክብር ማማ ላይ ለዘለዓለም ቀጥ አድርጎ ያቆመን አባት ዐርበኛውን- እምዬ ምኒልክን ነው።

እኛ የምናውቃቸው ነፍጠኞች፣ በአድዋ አቀበት፣ ዳገት፣ ተራራ ስር ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው፣ ፋሺስትን ከእግር እስከ አንገቱ ሰባብረው፣ ማንም በማይሰብረው የነፃነት ምሰሶ ላይ የነፃነት ሠንደቅ ያውለበለቡልንን እነ ራስ አሉላ አባ ነጋ፣ እነ ፊት-አውራሪ ገበየሁ፣ እነ ባልቻ ሳፎ፣ እነ እቴጌ ጣይቱ፣ እነ ንጉሥ ሚካኤል፣ እነ ራስ መንገሻ ዩሐንስ፣ እነ ራስ መኮንን፣ እነ ፊት አውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ እና ሌሎችም እልፍ- አዕላፍ ጀግኖች ናቸው።

እኛ የምናውቀው ነፍጠኛ፣ ፋሺስት ጣሊያን ዳግም በቀል ተጠምቶ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፣ ነፍጠኞችን አስተባብሮ ፋሺስትን ቁም ስቅሉን አሳይቶ በዱር በገደሉ እየሰባበረ በመጣል ነፃነትን ለንጉሡ ያስረከበውን አባ ኮስትር በላይ ዘለቀን ነው።

እኛ የምናውቀው ነፍጠኛ በጠላት ቡድን ሮም አደባባይ የኢትዮጵያ ሀውልት ተሰብሮ ሠንደቅ ዓላማ ሲወገድ ሲያይ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ጎራዴውን ከጠላት እጅ ነጥቆ ፋሽስት ሰብሮ እና ሰባብሮ የጣለውን ጀግናው ዘርዓይ ደረሰን ነው።

እኛ የምናውቀው ነፍጠኛ፣ በምድረ ጣሊያን ዜጎችን አስተባብሮ የነጭን ጦር ድል መትቶ ጠላትን እየሰባበረ ድባቅ በመምታት የአገሩን ሠንደቅ ባልተሰበረ ዓላማ ላይ ከፍ አድርጎ ያውለበለበ ነጮች ተንበርክከው የለመኑት ጥቁሩን አብዲሳ አጋን ነው።

እኛ የምናውቃቸው ነፍጠኞች አገር በቅኝ ተገዝታ የህዝባቸው ቅስም እንዳይሰበር ነፍጥ አንግበው የተዋደቁትን እነ መንገሻ ጀምበሬን፣ ሽፈራው ደርበውን፣ ኃይለየሱስ ዳምጤ፣ ጃገማ ኬሎ እና ተዘርዝሮ የማያልቁ እልፍ- አዕላፍ ጀግኖችን ነው።

እኛ የምናውቃቸው ነፍጠኞች አሁን አለን የምንለው ባሕል፣ እምነት፣ ትውፊት፣ ቅርስና ማንነት ከቀኝ ገዢዎች ጠብቀው ያቆዩልንን፣ አምልኳችንን በገለፅን፣ ቅርሳችንንም  ባሳየን ቁጥር፣ በምስጋና ልናስባቸው የሚገቡ በአጥንታቸው ስብርባሪ ጠላትን እየወጉ ነፃ ምድርን እስከ ውብ ባሕልና እምነቱ ያወረሱን የሀገር እና የህዝብ ጠበቃ ባለውለታዎቻችንን ነው። መልካም የአድዋ ድል በዓል!!!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com