የወጌሻ እጆች ይከበሩ

Views: 161
 1. መነሻ

በኢትዮጵያ የባሕል ሕክምና በጥልቀት ሲታይ፣ በሥሩ የተለያዩ ዘርፎች አሉት፡፡ ለምሳሌ የመድኃኒት አዋቂዎች እና የወጌሻ ሥራ የተለያየ ዘርፍ ነው፡፡  ዛሬ አንዱ የባሕል ሕክምና ዘርፍ የሆነውን   የወጌሻ ሥራ በጥቂቱ እንመልከት፡፡

ዋና ዋናዎቹ የተለመዱ የወጌሻ ተግባራት፡-

 • የተሠበሩትን አጥንቶች መጠገን፣
 • ውልቃትን ማስተካከል፣
 • ወለምታን መመለስ፣
 • ያለ መሥመሩ የዞረን ሥር ወደ ቦታው መመለስ፣
 • የወገብ ህመም በማሸት መፈወስ፣
 • በልምድ ማዋለድ፣
 • በወግምት ደም ማውጣት፣
 • የደም ሥሮችን ለማነቃቃት ማሸት፣
 • የተሳሰሩ ወይም ያበጡ ጅማትን ማሸት፣
 • በመውደቅ ሆዳቸውን የተቀጩ ህፃናት ማሸት እና መመለስ፣
 • የህፃናትን እጅና እግር ስብራት ወይም ቅጭት መመለስ፣
 • በቅዝቃዜ (በብርድ) የተመታን አካል ማሸት፣
 • አልታዘዝ ያለ እጅ እና እግርን ማሸት እና ማሠራት፣
 • ወደ ውስጥ የገቡ ወይም የሰረጎዱትን የአካል ክፍል በብርጨቆ መንጭቆ ማውጣት፣
 • የደደሩ እና የጠቆሩ ደም መልስ የተባሉ የደም ሥሮችን በማጀል ማከም እና ሌሎችም ለጊዜው ያልጠቀስኳቸውን በመከወን ሕክምና ያደርጋሉ፡፡

ሌሎቹ እጅግ በጥቂት ወጌሻ ባለሙያ የሚደረጉ የሕክምና ዓይነት

 • የአንጀት መታጠፍን መመለስ፣
 • የትርፍ አንጀት ህመምን ማከም እና
 • በሚገርም ሁኔታ ሙሉ ሆድን በማሸት የታመሙ የሆድ ውስጥ አባል አካልን መለየት ናቸው፡፡ ይህ የመለየት ሥራ ለምሳሌ ኩላሊት፣ አንጀት፣ ጨጓራ፣ ጉበት፣ ጣፊያ ጤነኛ መሆን አለመሆናቸውን መለየት እና አባል አካላቱ በትርፍ ስብ መሸፈንን  ለይተው የሚያስረዱ ናቸው፡፡

ይህንንም ሲከውኑ የተለያየ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ዋናው በእጅ መዳፍ እና ጣቶች ታካሚውን ማሸት ነው፡፡ የሚጠቀሙትም ለምሳሌ ቅቤ ወይም ቅባት ቀብተው በዘዴ ማሸት፣ የደረቀ አካል እንዲታዘዝ ለቀናት ማጀል (በአብሽ ሊጥ፣ በተለያዩ ቅጠላት፣ በጥቅል ጎመን ቅጠል) እና ማሸት፣ የተበተኑ አጥንቶችን ወደቦታቸው መሰብሰብ፣ የተዛነፈውን አካል ወደ ቦታው መመለስ፣ በቀጫጭን የቀርከሃ ወይም የመቃ ስንጥር አስደግፎ ማሰር፣ በጨርቅ ጠቅልሎ ማሰር፣ በመድኃኒታማ ዱቄት አጅሎ ማሰር፣ በብርጭቆ መመንጨቅ (ዋግምት) እና የመሳሰሉትን ዘዴዎች ይጠቀማሉ፡፡ ወጌሻዎቹ ከህፃናት እስከ አዛውንት እና የቤት እንስሳትን ጭምር ያክማሉ፡፡

ሁሉም ወጌሻ የተለያየ ልምድ እና የተለያየ ደረጃ ይኖራቸዋል፡፡ ለምሳሌ ከጨቅላ ህፃናት እስከ ታዳጊ የሚያክሙቱ ሌሎቹን ላያክሙ ይችላሉ፡፡ ወላድ ሴቶችን ብቻ የሚረዱም አሉ፡፡

 1. የዚህ ዕውቀት መገኛ

የወጌሻ ሕክምና ዘዴ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ አገር በቀል ዕውቀት ነው፡፡ እስከ ዛሬም በዘመናዊ ሥልጠና እና በሳይንስ ዕውቀት አልተደገፈም፡፡

 1. የሥራው ስፋት

አልተረዳን ካልሆነ በቀር፣ በአገራችን ወጌሻዎች በየመንደሩ አሉ፡፡ ትንንሽ ግልጋሎት የሚሰጡ፣ በሰፊው የሚሠሩ እና  እጅግ የታወቁት፤ ከጥንት እስከ ዛሬ የወጌሻ አበርክቶ በጣም ብዙ ነው፡፡

 1. የወጌሻ እጆች ይከበሩ ስንል ምን ማለታችን ይሆን?
 • የወጌሻ እጆች ለሚሰጡን የሕክምና አገልግሎት ተገቢውን ምስጋና እንስጥ፣
 • ለሰጡን የሕክምና ግልጋሎት ተገቢውን ክፍያ እናድርግ፣ እናም
 • እነዚህ የሕክምና እጆች እስከዛሬ ያቆዩትን እና ያካበቱትን ጥበብ ለቀጣዩ ትውልድ ያስተላልፉልን ዘንድ እናበረታታቸው፡፡
 1. እንዴት ነው የሚያስተላልፉት፣

ሀ/ በሌሎች አገራት (እንደ ህንድ፣ ባንግላዴሽ ወዘተ) እንደተደረገው፣

 • የባሕል ዘርፉ በሳይንስ እና ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂ በተቋም ተደግፎ ዕውቀቱ እንዲጠና፣ እንዲመዘገብ፣ ሕግና መመሪያ እንዲዘጋጅለት ማድረግ፣
 • ወጌሻዎችን ይህንን ክህሎት ለሌሎች በተሻለ ሁኔታ ማሰልጠን እንዲችሉ ማብቃት፣
 • ወጌሻዎች ስለ ሚሰጡት ግለጋሎት እና ስላከሟቸው ሰዎች በዝርዝር መመዝገብ እንዲችሉ ማብቃት፤

(ይህም ምዝገባ ለወደፊት ለሚደረገው ጥናት እጅግ ስለሚረዳ ነው፡፡ ለምሳሌ ሙሉ በሙሉ የዳኑ፣ በጥቂቱ ፈውስ ያገኙ፣ ያልዳኑ፣ ምን ዓይነት ህክምና እንዳገኙ ወዘተ መመዝገብ ማለት ነው)፡፡

ለ/ በተለመደው አሠራርም ቢሆን ዕውቀቱን ማስተላለፍ፣

በተጠናከረ ሁኔታ በተቋም ዕውቀቱን በስልጠና ማስተላለፍ ባይጀመር እንኳ፣

 • ወጌሻዎች እራሳቸው ከቤተሰብ አባላት ወይም ሌሎች ዕውቀቱን ለመማር ዝግጁ የሆኑትን እና ፍላጎት ያላቸውን በባሕላዊ ዘዴ ማስተማር፣
 • የዘመኑን ትምህርት የተማሩቱ ለዚህ ባሕላዊ ዕውቀት ትኩረት ይነፍጋሉ፡፡ ይልቅ አስተውሉ፤ የቀደሙት ወጌሻዎች ያለምንም ዘመናዊ ትምህርት ይህንን ያክል ሰርተዋል፡፡ ያገኛችሁትን ዘመናዊ ትምህርት ከባሕሉ ጋር ብታቀናጁ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ይረዳችኋል፡፡

የወጌሻ እጆች ጥበብ ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ጥረት እናድርግ!!!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com