ግራዋ እንስራን ከማጽዳት እስከ መድኃኒትነት

Views: 856

መነሻ

ግራዋ በሳይንሳዊ ስሙ፡ ቨርኖኒያ አሚግዳኒና (Vernonia amygdalina) ይባላል፡፡ በእንግሊዘኛ ቢተር ሊቭ (bitter leaf) መራር ቅጠል እንደማለት እና በአፋን ኦሮሞ ደግሞ ዴብቻ (Dheebicha) ይባላል፡፡ ለጽዳት፣ ለምግብነት፣ ለአጥር፣ ለእንስሳት መኖ፣ ለሰው እና ለእንስሳት መድኃኒት እና ለሌሎችም ብዙ ነገሮች ይጠቅማል፡፡ ግራዋ ዝናው ብዙ ነው፡፡

1ኛ. ግራዋ በአፍሪካ አገራት

በዊኪፒዲያ ላይ እንዲህ ይነበባል ፡፡ (Wikipedia, the free encyclopedia)

በአፍሪካ ሀሩራማ ክልል ተስፋፍቶ የሚበቅለው ቁጥቋጦ መሰል ግራዋ ቁመቱ እስከ 5 ሜትር ያድጋል፡፡ በብዙ የአፍሪካ አገራት በተለያየ መጠሪያ ይታወቃል፡፡

ለምግብነት

በምዕራቡ የምድር ሰቅ አካባቢ ያሉ የአፍሪካ አገራት ቀንበጡን ግራዋ ለሾርባ ወይም ለወጥ ይጠቀሙታል፡፡

በምዕራብ ታንዛኒያ ውስጥ በታንጋኒካ ሐይቅ ምሥራቃዊ ክፍል ነዋሪ የሆኑት እነ ቶንግዌ (Tongwe)  ለመድኃኒትነት በውሃ ዘፍዝፈው በቀዝቃዞው ለወባ፣ ለአንጀት ጥገኛ ተውሳክ፣ ለተቅማጥ እና ለሆድ ህመም ይጠቀሙታል፡፡ በብዙ የአፍሪካ ማህበረሰቦች ዘንድ የሚታዘዝ ማከሚያ የሆነው ለወባ ንደድ፣ ለብለሃርዝያ፣ ለአሜባ ተቅማጥ፣ ለብዙ የአንጀት ተውሳክ እና ለሆድ ህመም ነው፡፡

በናይጀሪያ ለጋ ዘንግ እንጨቱን በማኘክ ለጥርስ ጤና ይጠቀማሉ፡፡ በኡጋንዳ ግንዱ እንደ ሳሙና ያገለግላል፡፡ በጋና ከጠንካራ ይልቅ ቀንበጥ ቅጠሎቹ  ለፀረ ስኳር በሽታ እና የሰውነትን መነፍረቅ ወይም መቁሰል እንዲሚያክም እውቅና ሰጥተውታል፡፡

2ኛ. አበቃቀል

በሚያብብ ጊዜ ብን ያሉ ደቃቅ ዘሮች አሉት፡፡ እነዚህኑ መዝራት፣ ሲያድጉ በሚፈልጉት ቦታ መትከል፡፡ ብዙ ጊዜ ችግኙ ቀደም የተክሉ አበባ በተበተነበት ቦታ ሁሉ አድጎ ይገኛል፡፡ ይህን ችግኝ እዚያው መንከባከብ፣ ወይም ቦታ ቀይሮ መትከል፡፡

ዘንጉን ወደ አንድ አቅጣጫ ማጋደም፣ ወደ ላይ ብዙ ዘንጎች እንዲበቅሉ ዕድል ይፈጥራል፡፡

3ኛ. አገርኛ የግራዋ መድኃኒትነት

ሀ/ ለአፍንጫ ነስር

በጣም ለጋ የግራዋ ቅጠል ማጠብ፣ በእጅ ማሸት እና መጭመቅ፣ በመሐረብ ማሰር እና መጭመቅ፡፡ ፊትን ታጥበው ወድያው ወደ ኋላ ጋደም ብሎ ወደ አፍንጫ ማንጠባጠብ፡፡ ትንሽ ተገጋግቶ መቆየት፡፡

ለ/ ለእሳት ቃጠሎ

ለእሳት ቃጠሎ ቁስል በጣም ተፈላጊው የድግጣ ቅጠል ነው፡፡ ሆኖም ድግጣ በማይገኝበት ጊዜ ግራዋ ያገለግላል፡፡ ቅጠሉን አጥቦ ወቅጦ ጨምቆ ማዘጋጀት፡፡ በቁስሉ ላይ ነጠላ ጨርቅ ሸፍኖ የጭማቂውን ውኃ መጨመር ነው፡፡ ይህም እርጥብ ሆኖ እንዲቆይ ማድረግ፡፡ በየቀኑ እስከሚድን እንደዚሁ ማድረግ፡፡

ሐ/ ለእከክ

እርጥቡን የግራዋ ቅጠል አጥቦ፣ ወቅጦ፣ በዚሁ እያሹ ማጠብ ነው፡፡

መ/ የግራዋ ጭማቂ መጠጣት

ፈጽሞ ነፍሰጡር ሴቶች ግራዋ እንዳትጠጡ፡፡ ግራዋ ለመጠጥ ሲዘጋጅ ምሬት ለመቀነስ ወይም የመድኃኒት ብቃቱን ለመጨመር በሶቢላ ቅጠል አብሮ መጨመር ይቻላል፡፡

ለአሜባ እና ለጃርድያ

አንድ እፍኝ የግራዋ ቀንበጥ ቅጠል ማጠብ፣ በውቀጥ፣ አንድ ብርጭቆ ውሃ ጨምሮ መጭመቅ እና ማጣራት፣ አንድ ማንኪያ ማር ጋር ጠዋት መጠጣት፡፡ በተከታታይ ለሶስት ቀናት ቢጠጣ የአሜባ እና ጃርድያን ከሆድ ውስጥ ያስወግዳል፡፡

ለቫይቫክስ የወባ ዓይነት

አንድ እፍኝ የግራዋ ለጋ ቅጠል ማጠብ፣ መውቀጥ፣ አንድ ብርጭቆ ውሃ ጨምሮ መጭመቅ፣ አንድ ማንኪያ ማር አክሎ መጠጣት፡፡ ለአንድ ሳምንት መጠቀም የወባ በሽታውን ያስወግዳል፡፡

ለአንጀት ተስቦ (ታይፎይድ)  

አንድ እፍኝ የግራዋ ለጋ ቅጠል ማጠብ፣ መውቀጥ፣ አንድ ብርጭቆ ውሃ ጨምሮ መጭመቅ፣ አንድ ማንኪያ ማር አክሎ መጠጣት፡፡ ለአንድ ሳምንት መጠቀም ታይፎይዱ ከአንጀት እንዲወገድ ይረዳል፡፡ እንዳያገረሽም ያግዳል፡፡

ለሆድ ውስጥ ጥገኛ ትሎች

ከላይ እንደ ተነገረው በተመሳሳይ ዘዴ መጠቀም፡፡ ለሶስት ቀን ቢጠጡት በቂ ነው፡፡

ለችኩንጉንያ በሽታ

ቅጠሉን አጥቦ መውቀጥ፣ በፈላ ውሃ ላይ ጨምሮ በሻይ መልክ ይዘጋጃል፡፡ ካስፈለገ ማር አክሎ አንድ ብርጭቆ መጠጣት፡፡

ስለ ችኩንጉንያ ይበልጥ በዚሁ መረጃ መረብ ላይ በዚህ https://ethio-online.com/archives/5455  ሊንክ ላይ አንብቡ፡፡

ሠ/ ግሩም አረንጓ ወጥ ለመስራት

በአገራችን በጣም ውስን በሆነ ደረጃ የሳማ ቅጠል እና ግራዋ በአንድነት አረንጓ ወጥ ይሰራል፡፡ ምንም እንኳን ግራዋ መራር ቢሆን፣ የሳማ ጣዕም ጥሩ ወጥ እንዲሆን ይረዳዋል፡፡

አሠራሩ

የሳማ ቅጠል ስለሚለባለብ በጥንቃቄ መቀንጠስ እና ማዘጋጀት፣ ግራዋ ከታች በምስሉ እንዳለው ቅጠሉ ተለይቶ ይቀነጠሳል፡፡ በተደጋጋሚ ይታጠባል፡፡ ይቀቀላል እስከ አንድ ሰዓት ሊቆይ ይችላል፡፡ ግራዋው ከበሰለ በኋላ እንዳገና ከሳማ ጋር መልሶ መቀቀል እና በአንድ ላይ መላግ ወይም መለንቀጥ፡፡ ቀጥሎም እንደተፈለገበት ጉዳይ ጨው፣ ማር ወይም የሚፈልጉትን ቅመማት መጨመር እና በእንጀራ መመገብ፡፡

ረ/ ለቤት እንስሳት

ለእንስሳት ቃጠሎ ጭማቂውን በመቀባት ማከም ይቻላል፡፡ በፈንገስ ወይም በእከክ ለተያዘ እንስሳ ቅጠሉን ጨፍጭፎ፣ እንስሳውን ማጠብ ነው፡፡

ሰ/ በእንስሳት አካል ላይ ለሚራቡ ጥገኞች

በእንስሳት አካል ላይ መዥገር፣ ቅማንዥር እና ቅጫም የተራባ እንደሆን፣ የግራዋን ቅጠል ጨፍጭፎ፣ በጨው ዘፍዝፎ የእንስሳን አካል በደንብ ማጠብ ነው፡፡

ሸ/ ለቤት ዕቃ ጽዳት

ግራዋ ለጠላ መጥመቂያ ዕቃ፣ ለጠጅ ዕቃ፣ ለውሃ ዕቃ ጽዳት በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ በቅጠሉ ቀጥታ ማጠብ ይቻላል፡፡ ወይም ዕቃውን በሌላ ማጠብያ አጥቦ፣ በግራዋ ጥላይ ውሃ በደንብ ማለቃለቅ እቃውን ከብዙ ነገሮች ጽዱ ያደርጋል፡፡

  1. ግራዋ በኪኒን መልክ

በሌላ አገራት በኪኒን መልክ በተለያየ ደረጃ ተዘጋጅቶ ይገኛል፡፡ ከታች ያለው ምስል ለምሳሌ ለነቀርሳ (ካንሰር) ተብሎ የተመረተ ነው፡፡

This image is  Courtesy  to

https://www.nairaland.com/5549700/benefits-bitter-leaf-capsules-cancer

ማጠቃለያ

ግራዋ መነሻ አገሩ አፍሪካ ቢሆንም፣ በዚህ ዘመን በሰለጠኑት አገራት በእጅጉ የተራቀቀ ውጤት ተመርቶበታል፡፡ በእኛ አገር ቅጠሉ እንደሚጠጣ መንገር እራሱ ለአድማጩ የሚከብድ ነው፡፡ ብዙዎች ይመራል በማለት ይተቻሉ፡፡ ልብ ማለት የሚገባን ግን ግራዋ ፀረ ፈንገስ፣ ፀረ ተውሳክ የሆነ፣ ሲጠጣ ለሰው ጤና በብዙ ፍቱን የሆነ ተክል ነው፡፡ በቀላሉ ከቆላ እስከ ደጋ ቢተክሉት ይበቅላል፡፡ ለምግብም፣ ለመድኃኒትም ይሆናል፡፡ ግራዋን አልሙ፣ ጤናችሁን ተንከባከቡ፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com