የጤፍ ዋጋ መናሩን ቀጥሏል

Views: 399

መንስዔው በውል ያልታወቀው የጤፍ ዋጋ ንረት፣ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው። ወቅቱ ጥሩ ምርት የተሰበሰበበት ቢሆንም፣ የጤፍ ዋጋ ንረት ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

የጤፍ ዋጋ ንረት መንስዔ አንዳንዶች ከአቅርቦት ማነስ መሆኑን ሲገልፁ፣ ሌሎች ደግሞ የገበያው ሥርዓት ብልሹነት ነው ሲሉ ይደመጣሉ።

አቶ ኢሳያስ ለማ በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ የምርት አቅርቦት ማነስ በምክንያትነት መነሳቱን አይስማሙም። የ5 አመት መረጃ የሚያሳየው የሚታረሰው የጤፍ መሬት ከ 2.8 ሚሊዮን ሄክታር ወደ 3.15 ሚሊዮን ሄክታር ከፍ ብሏ፤ በመቶኛ ሲሰላም በ 4.5 አድጓል ብለዋል።

በምርት ደረጃም የዛሬ አምስት አመት የነበረው አጠቃላይ የጤፍ ምርት 44.7 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 58.15 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ እንዳለም ገልፀው፣ ምርታማነቱም በሄክታር ይገኝ ከነበረው ከ16 ወደ 18 ኩንታል አድጓል ሲሉ ገልጸዋል።

አንድ ሰው አመታዊ የእህል ፍጆታው በአማካይ አንድ ነጥብ አምስት ኩንታል ነው፤ በዚህ ስሌት አንድ ሰው ሲወለድ 1.5 ኩንታል ፍላጎት ይኖረዋል ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ ከዚህ አንፃር የምርትና ፍላጎት አለመጣጣም ጥያቄ ቢነሳም፣ አሁን የሚስተዋለው የዋጋ ንረት ምክንያታዊ ነው ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የኢንስፔክሽን ሪጉራቶሪ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ጥላዬ የችግሩን አሳሳቢነት ሲገልፁ፣ የምግብ ዋጋ ንረት ከ2011 ዓ.ም ግንቦት ወር ወዲህ ነው የጀመረው፣ ቢሮው ከመጠባበቂያ ምግብ ክምችት ያገኘውን 90 ሺህ ኩንታል ለከተማው ነዋሪ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያውን አረጋግቷል፤ አሁን ምርት የገባበት ወቅት ቢሆንም ችግሩ አልተቀረፈም።

ገበያውና አምራቹ ጋር ያለው ዋጋ አለመራራቁን በምክንያት በማንሳት አቅርቦቱ ከምንጩ መፈተሽ አለበት ብለዋል።

ከአርሶአደር የአካባቢ ነጋዴ፣ ከዛ ከፍ ያለ ነጋዴ ከእርሱ ደግሞ የከተማ ነጋዴ፣ ደላላ፣ ወፍጮ ቤት እያለ ሰንሰለቱ ይረዝማል። የንግድ ሱቆች ኪራይ ዋጋ፣ የኤሌክትሪክና የውኃ ታሪፍ መጨመር እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ለአጠቃላይ የምግብ ዋጋ ንረት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በክትትልና ቁጥጥር ስራ ተለይቷል።

አቶ ኢሳያስ የገበያ ሥርዓቱ ብልሹነት ስለመኖሩ ቢገልፁም፣ አቶ ሀብታሙ ግን ነፃ ገበያ በመሆኑ መንግሰት የዋጋ ትመና ውስጥ አይገባም። ለዋጋ ንረት ምክንያት የሆኑትን ግን ይለያል፤ የምርት ማነስ፣ ሕገወጥነት፣ በአቅርቦት ሠንሰለት ውስጥ ማነቆዎች ካሉ ለይቶ መፍትሔ ያስቀምጣል፤ የምርት አቅርቦት ችግር ተጠቃሽ ነው ሲሉም ይናገራሉ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com