ሠንሰል ለአስም እና ለሳል የታመነ ነውን?!

Views: 478

የሰንሰል ምስል በመንገድ ዳርቻ

መነሻ፡-

ለሁሉ ጊዜ አለው እንዲሉ፣ የኢትዮጵያ ተክሎች ቀስ-በቀስ፣ ተራ-በተራ ወደ ጉልህ የአትኩሮት ርዕሰ-ጉዳይ እየሆኑ ናቸው፡፡  ሠንሰል በዚህ ሰሞን አዲስ አበባ ውስጥ ርዕሠ-ጉዳይ ሆኖ ተወሳ፡፡ ዜናው ተራ ወሬ ነው ወይስ የተጨበጠ ጠቀሜታ ነገር ይኖረው ይሆን? እንፈትሸው፡፡

ሠንሰል በኢትዮጵያ ምድር እንደሌላው “ባድማ ጠባቂ” ተክሎች ለዘመናት ከአጥር ዳርቻ፣ ከመንገድ ጥግ ለጥግ እና በየመንደሩ ሲበቅል የኖረ ተክል ነው፡፡  በጣም የጎላ ወይም የተለመደ ባይሆንም፣ በጥቂቱ ለባሕል ሕክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በቅርብ ወራት በብዙ የአዲስ አበባ ሰዎች ዘንድ በሰፊው ለአስም እና ለሳል ጠቀሜታ እንዳለው ይወሳል፡፡ ይህ እስከምን የታመነ ነው? ይህ የዛሬ ዋና ርዕሰ ጉዳያችን ነው፡፡

ሀ/ ሠንሰል ተክሉ

የሠንሰል ተክል በሳይንሳዊ መጠሪያው Justicia schimperiana ወይም Adhatoda schimperiana (አዳቶዳ እስችምፕሪያና) ይባላል፡፡ በግዕዝ ስሚዛ፣ በኦሮሚፋ ዱሙጋ (Dhumuga)  ተብሎ ይጠራል፡፡

ታዋቂው የጀርመን የዘረ-ዕፀዋት አሳሽ ጆርጅ ዊልሃልም እስችምፐር (Goerge Wilhelm Schimper) ከ1837 እስከ 1863 እ.ኤ.አ በኢትዮጵያ ቆይታ አድርጎ ተክሎችን ሲያጠና የኖረ ሰው ነው፡፡ ጆርጅ ዊልሃልም እስችምፐር እንደ ጥናቱ ስፋት እና እንደ እድልም ሆኖለት ጥቂት የኢትዮጵያ ተክሎች በስሙ (እስችምፐርያና ወይም እስችምፐሪ እየተሰኙ) ተሰይመዋል፡፡ ከእነሱም ውስጥ ሠንሰል፣ የፍየል ጎመን፣ የውሻ ስንደዶ፣ የጅብ ሽንኩርት፣ መጭ፣ ደደሆ፣ እንቆቆ፣ ጮጮሆ፣ ቀረፋ እና ጦስኝ ይገኙበታል፡፡ ማጣቀሻ አንድ

ሠንሰል በብዛት ተስፋፍቶ የሚገኘው በምስራቅ አፍሪካ አገራት በተለይም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ እና ታንዛንያ ነው፡፡ በተፈጥሮው ብዙ ችግር ተቋቁሞ ደጋ ምድር እና ቆላ ይበቅላል፡፡ እርጥበታማ መሬት ይወዳል፡፡ ሆኖም ድርቅን ይቋቋማል፡፡ አበቃቀሉ እንደ ቁጥቋጦ (shrubs) ነው፡፡   ማጣቀሻ ሁለት እና ሶስት

በብዙ የአገሪቱ ገጠር አካባቢ እንደ አካባቢው መጠሪያ በስም ለይተው ያውቁታል፡፡ በአዲስ አበባ በተለይም በመንገድ ዳርቻ፣ በየወንዛ ወንዙ፣ በየመንደሩ፣ በብዛት የሚገኝ እና አመቱን ሙሉ አረንጓዴ ለምለም ቢሆንም፣ በብዙዎች ዘንድ ስሙን ለይተው አያውቁትም፡፡ አንዳንዶች ጭራሽ ከግራዋ ጋር ያመሳስሉታል፡፡ በተለምዶ የጠላ ዕቃ ማጠቢያ እና ብቅል ሲያበቅሉ መሸፈኛ (መርገጫ) ሆኖ ያገለግላል፡፡

በቅርብ ወራት አዲስ አበባ ውስጥ በብዙዎች ለአስም እና ለሳል ፋይዳ እንዳለው እየተወሳለት ይገኛል፡፡ በእውነቱ ግን ሠንሰል ጠቀሜታው ከተባለለት በላይ ነው፡፡ ከቶውንም ሠንሰልን ማን ከዋጋ ቆጥሮት ያውቃል? ሠንሰል በብዙ የአገራችን ነባር ዕውቀት እና በሌሎች የጥናት ውጤቶች እንደተነገረው ለብዙ በሽታ የተፈጥሮ መድኃኒት ነው፡፡ በሌሎች አገራት በዘመናዊ ደረጃም ተዘጋጅቶ ይገኛል፡፡

ለ/ ሠንሰል ለአስም እና ለሳል የመታጠኛ ዘዴ

  • ማጠብ፣ ቅጠሉን መልምሎ፣ ሙልጭ አድርጎ በበቂ ውኃ 3 ጊዜ ደጋግሞ ማጠብ፣ ይህ በላዩ የሚገኘውን አቧራ፣ ተባይ፣ ተውሳክ ወዘተ ለማጽዳት ይረዳል፣
  • በሸክላ እቃ መቀቀል፣ መቸም ቢሆን እንፋሎቱን ለመታጠን የሚውሉ ተክሎችን ለመቀቀያ የሸክላ ድስት ወይም ማሰሮ መጠቀም ነው፡፡ ያለጥንቃቄ በብረት ድስት መቀቀል ትክክል አይደለም፡፡ ብረትድስቱ ከምን ዓይነት ብረት እንደተሰራ እንኳን አናውቀውምና፡፡
  • እንፋሎቱን ማወድ፣ በብዙ መጠን መቀቀል እና እንፋሎቱ ቤቱን እንዲያውደው ማድረግ፣ ይህ የታመመውን ሰው ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡን ሁሉ ከበሽታ ለመታደግ ይረዳል፡፡ ነዶ ባለቀለት የከሰል ፍም ላይ ወይም በእንጨት ፍም ላይ አስቀምጦ ለአንድ ሰዓት እንዲፈላ እና እንፍሎቱ በቤት ውስጥ እንዲተን ማድረግ ነው፡፡
  • እንፍሎቱን መታጠን፣ ግማሽ ኪሎ ያህል ቅጠል በአንድ ሊትር ውኃ ጥዶ ማፍላት ነው፡፡ መፍላት ጀምሮ 1ዐ ደቂቃ ያህል ከቆየ ማውረድ እና ወደ ታማሚው መኝታ ቦታ መውሰድ ነው፡፡ ከመኝታ በፊት የሳል ወይም የአስም ታማሚ ሰው በመኝታ ክፍሉ ውስጥ፣ ከላይ ተሸፋፍኖ እንፋሎቱን በአፍና አፍንጫው ወደ ውስጥ እየሳበ ለአስር ደቂቃ ያህል መታጠን አለበት፡፡ ከፈለገም መልሶ በእሳት ላይ ጥዶ ሲፈላ አውርዶ መታጠን ይችላል፡፡  ታማሚው በእረፍት ላይ ያለ ወይም ከቤት የሚውል ከሆነ በማንኛውም ጊዜ በቀን እስከ 3 ጊዜ መታጠን ይችላል፡፡
  • በሞቀ ውሃ መታጠብ፣ በታጠኑት ማግስት ወይም ወደ ውጪ ከመውጣት በፊት ገላን መታጠብ ያስፈልጋል፡፡ ምንጊዜም አንዳች ነገር ታጥኖ፣ ሳይታጠቡ መውጣት አይገባም፡፡ በተለይም ለፀሐይ ጨረር ከመገለጥ እጅግ መጠንቀቅ ያሻል፡፡

ይህ ሲሆን ሳል እና አስምን ቀላል ያደርጋል፡  ጉንፋን ቶሎ ያበስላል፡፡ እንደበሽታው ጽናት ለአንድ ሳምንት ወይም በሳምንት ጥቂት ቀናት፣ ወይም ውጤቱን እያጤኑት እንደ አስፈላጊነቱ መጠቀም ነው፡፡

ጥንቃቄ፣  በከሰል ፍም ላይ ማፍላት እና መቀቀል ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከሥር የከሰል ምድጃ ላይ አድርጎ መታጠን አይገባም፡፡ የከሰሉን አደገኛ ነገር ወደ ውስጥ ታጥነው ሌላ በሽታ ላይ መውደቅ ሊያስከተል ይችላል፡፡

ሐ/ ሠንሰል መላ ሰውነትን መታጠን

ለምች፣ ለብርድ ቁርጥማት እና ለመሰል ህመም መላ ሰውነት መታጠን በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ ዘዴው ከላይ እንደተነገረው ሆኖ፣ መላ ሰውነትን በሠንሰል እንፋሎት ደህና አድርጎ መታጠን ነው፡፡ ታጥኖ አድሮ ገላን መታጠብ ግን መረሳት የለበትም፡፡

ሠንሰል ለሌሎም ህመም ብዙ ቀጠሜታ ያለው ነው፡፡ በተለይ ግን ለወባ ብዙ ጥናቶች በአገር ውስጥ እና በውጪ ተደርጓል፡፡ ለጋ ቅጠሉ ለወባ በሽታ እንደ ሻይ ተፈልቶ በስኳር፣ በቀን አንድ ኩባያ ለሶስት ቀናት ይጠጣል፡፡ ይህንን  በማጣቀሻ አራት ላይ ባለው ሊንክ በሰፊው አንብቡ፡፡

መ/ ሠንሰል ለዓይን ሕመም

ለቀላል የዓይን ሕመም ከላይ በተነገረው ዘዴ እንፋሎቱን ማታ ለዓይን መታጠን እና የተቀቀለበትን ሸክላ ዕቃ ከድኖ ማሳደር ነው፡፡ በማለዳ ውኃውን ማጥለል እና በጥላዩ ውኃ ዓይንን መታጠብ ነው፡፡ ለአንድ ሳምንት ይህ ዘዴ በገጠር አካባቢ ለብዙዎች ይረዳል፡፡

ሠ/ የሠንሰል ሌሎች ጠቀሜታዎች 

በቋሚ አጥርነት፣ ተስተካክሎ እየተቆረጠ ለብዙ ዘመናት ያገለግላል፡፡ በእርከን ላይ ሲተከል ሥሩ አፈር ይይዛል፡፡ የእንጨት ግንዱ በገጠር ለቤት መሥሪያ ይውላል፡፡ በሚያብብ ወራት ግሩም የንብ መኖ ያፈራል፡፡ እንዲያውም “የሠንሰል ማር” ተብሎ በተሻለ ዋጋ የኩላሊት ጠጠር ያደቃል ተብሎ ይሸጣል፡፡ ቅጠሉ ተጨምቆ ሲረጭ ሶስት አጽቄን ያስወግዳል፡፡ በማሳ ዳርቻ ሲተከል በከብት ብዙ ስለማይበላ ጥሩ አጥር ይሆናል፡፡  በዙሪያው ያለውን የአፈር ልምላሜ ይጨምራል፡፡ ሠንሰሉ ለተወሰነ አመታት ተተክሎ ቢነቀል ያ ቦታ አፈሩ ለምነቱ የተሻለ ሆኖ ይገኛል፡፡ ሠንሰልን ለማልማት በደህና የዝናብ ወራት ከወደ አናቱ ያለውን ዘንግ ቆራርጦ መትከል ነው፡፡

ማጠቃለያ፡-

ሠንሰል በሸክላ ዕቃ ተቀቅሎ እንፋሎቱን በቤት ውስጥ ማወድ ወይም መታጠን ለጤና መልካም ነው፡፡ ከላይ እንደተነገረው ለአስም፣ ለጉንፋን፣ ለሳል፣ ለመተነፈሻ አካላት እንፋሎቱን መታጠን ይረዳል፡፡   ነገር ግን፣ የሠንሰል እንፋሎት የሰውነት መቆጣት (አለርጂ) የሚያስከትልበት ሰው መጠቀም የለበትም፡፡ የጤና ጠቀሜታው ብቻውን ሳይሆን ሌሎች ተስማሚ መድኃኒት እየወሰዱ፣ ምግብ በማስተካከል፣ የአካባቢን ጽደት በመጠበቅ እና በተጨማሪ የሠንሰል እንፋሎት መታጠን ውጤታማ ያደርጋል፡፡

ሠንሰል ከዚህም በላይ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በቂ እርጥበት ካገኘ፣ አመቱን ሙሉ መትከል እና ማባዛት ይቻላል፡፡ ለተፈጥሮ እንክብካቤ በእጅጉ የሚረዳ ነው፡፡ ለተፈጥሮ መድኃኒት ብዙ ጥናት ቢደረግበት የተሻለ ይሆናል፡፡

ማጣቀሻ፡-

  1. ማጣቀሻ አንድ፡  በቀለች ቶላ (ሐምሌ 2ዐዐ9)፣ የዕፀዋት መጠሪያ፣ በሳይንሳዊ፣ አማርኛ እና ሌሎችም፡ አልፋ አታሚዎች፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
  2. ማጣቀሻ ሁለት  https://botany.cz/en/justicia-schimperiana/
  3. ማጣቀሻ ሶስት Bekele-Tesemma, A., 2007. Useful trees and shrubs for Ethiopia: identification, propagation and management for 17 agro climatic zones. Technical Manual No 6. RELMA in ICRAF Project, Nairobi, Kenya.
  4. ማጣቀሻ አራት  https://uses.plantnet-project.org/en/Adhatoda_schimperiana_(Jansen,_1981)#Medicinal_uses

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com