በአቶ ጃዋር የዜግነት ጉዳይ ምርጫ ቦርድ ለኢሚግሬሽን ደብዳቤ ላከ

Views: 221

በአለምፀሀይ የኔዓለም

 

ምርጫ ቦርድ አቶ ጃዋር መሃመድ ኢትዮጵያዊ ዜግነት መልሶ ማግኘቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲሰጠው የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲን ጠየቀ፡፡

የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ የሀገር አቀፍም ሆነ የክልል ፓርቲ አባል መሆን የሚችለዉ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለዉ ሰዉ ብቻ መሆኑን ይደነግጋል፡፡

ከዚህ አንጻር የአቶ ጃዋር መሃመድ የኢትዮጵያዊነት ዜግነትን ማግኘት ጉዳይ ማስረጃ ይሰጠኝ ሲል ምርጫ ቦርድ ለኢሚግሬሽን፣ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በዚህ መሰረትም ቦርዱም ለኤጀንሲው እስከ የካቲት 09 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ይስጠኝ ሲል ጥያቄ በደብዳቤ ማቅረቡን በማህበራዊ ድረገጹ አስታውቋል፡፡

የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ጃዋር መሃመድ የኢትዮጵያ ዜግነታቸዉን መልሰዉ በማግኘት ሂደት ላይ ነኝ እያሉ ፓርቲዉ ግን ኢትዮጵያዊ የሚል የአባልነት መታወቂያ ሰጥቷቸዋል ሲል ቦርዱ አስታውቋል።

አሁን በስራ ላይ ባለዉ የዜግነት አዋጅ መሰረት ግለሰቡ የኢትዮጵያ ዜግነት መልሰዉ አግኝተዉ ከሆነ ይህን የሚያስረዳ ሰነድ ከደህንነት፣ኢሚግሬሽንና ስደተኞች ጉዳይ ባለስልጣን ማቅረብ እንዳለበት የተነገረው ፓርቲዉ፣ይዘዉት የነበረዉን ሌላ ሀገር ዜግነት ስለተዉና ስልጣን ላለዉ አካል ስላመለከቱ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸዉን አግኝተዋል፤ኢትዮጵያዊም ሆነዋል ሲልም ፓርቲዉ ቀደም ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲው በሰነድ እንዲያስረዳ ምርጫ ቦርድ መጠየቁ ተገቢ አይደለም ሲልም አክሏል፡፡ በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ የኢሚግሬሽን፣ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ማብራሪያ እንዲሰጠዉ ምርጫ ቦርድ ጠይቋል።

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com