“የተገፋሁት በራያነቴ ነው”

Views: 350

በሚኒስትር ዲኤታነት እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት የነበሩት አቶ ዛዲግ አብርሃ በቅርቡ ከህወሃት አባልነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አሳውቀዋል። የመልቀቃቸው ጉዳይ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል። ከድርጅታቸው ጋር ስለነበራቸው ቅሬታና ስለ ወደፊቱ የፖለቲካ ህይወታቸው ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ቢቢሲ፡ ለንደን ምን እያደረጉ ነው?

አቶ ዛዲግ፡ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የድህረ ምረቃ ትምህርቴን በመከታተል ላይ ነኝ። በቅርቡም ትምህርቴን ስለማጠናቅቅ ወደ አገር ቤት እመለሳለሁ።

ቢቢሲ፡የህወሃት አባልነት መልቀቂያውን ያስገቡት ለንደን ሆነው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ ማስገባት አይቻልም ነበር?

አቶ ዛዲግ፡ የመልቀቂያ ደብዳቤየ ላይ እንዳስቀመጥኩት በተለያየ ምክንያት አልቻልኩም ነበር። ከድርጅቱ ጋር ያለኝ ልዩነት መፈጠር ከጀመረ ቆይቷል። ያሻሽሉ ይሆን የሚለውን እያሰላሰልኩና ተስፋም ስለነበረኝ፤ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመወሰንና አሟጥጬ ለመጠቀምምጊዜ ያስፈልግ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ መልቀቂያ ማስገባት የራሱ የሆነ አካሄድ አለው። እድልም መስጠት ፈልጌ ስለነበርም ለዛ ነው ጊዜዬን የወሰድኩት። በቅርቡ የሚታዩት ምልክቶች ደግሞ ከናካቴው ከለውጥ ጋር እንደተጣሉ አስረግጦ የሚያስረዱ ነገሮች ስላጋጠሙኝ በዚያ ምክንያት የመጨረሻውን ውሳኔ ለመወሰን ችያለሁ።

ቢቢሲ፡ በድርጅትዎ ህወሃት ውስጥ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይደርስብዎ እንደነበር በመልቀቂያ ደብዳቤዎ ላይ ገልፀዋል። በግለሰብ ደረጃ ነው ወይስ እንደ ድርጅት ህወሃትን ወክሎ በደብዳቤ ነው?

አቶ ዛዲግ፡ተቋም በሰው ነው የሚወከለው፤ ደብዳቤየ ላይ እንዳስቀመጥኩት ትልልቅ ስልጣን ያላቸው መሪዎች፤ በተለይም የፖለቲካ እስረኞችን በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ፌስቡክና ትዊተር ገፅ በቀጥታ ማስተላለፋችን ከታወቀበት ከዚያ ምሽት ጀምሮ ለረዥም ጊዜ ከአንድ አመት በላይ ማስፈራሪያና ዛቻ ይፈፀምብኝ ነበር።

ይህንን የሚያደርሱብኝ ትልልቅ ስልጣን ያላቸው መሪዎች ናቸው። አሁን የግለሰብ ስም ማጥፋት ስለማያስፈልግ ስማቸውን መግለፅ አልፈልግም። የእነሱ ድርጊት እንደ ድርጅት ድርጊት ነው የሚቆጠረው፤ ከተሳደቡም፣ መልካም ስራ ከሰሩም ያው ድርጅታቸውን ወክለው ነው። የደረሰብኝን ዛቻና ማስፈራሪያም አውቀው ከጎኔ የቆሙና አይዞህ ያሉኝ በተራ አባልነት ያሉ ሰዎችም ነበሩ። ምንም እንኳን የተፈፀመው በመሪዎች ቢሆንም ይህ ነገር በተቋም ወይስ በግለሰብ ደረጃ ነው የሚለው አከራካሪ ነው። ያው እንግዲህ እንዘንላቸው ከተባለ ይህ በግለሰብ ደረጃ የተፈፀመ ነው ማለት ይቻላል። ሆኖም ግን ደብዳቤየ ላይ በግልፅ እንዳስቀመጥኩት በዛ ወቅት በወሰድኩት አቋም ነው። በግል ይህ ነው የማይባል፤ ተራ ሳይሆን ከበድ ያለ ጥቃት፣ ዛቻ ፣ ወከባና ትንኮሳ ደርሶብኛል።

እነዚህ ሰዎች ደግሞ ተራ ዛቻ ሳይሆን ጥቃት የማድረስ ብቃቱና ከፍተኛ አቅም ያላቸው ናቸው። ያደረጉት ሰዎችም እውነት መሆኑን ያውቁታል። ከዚያም አልፎ በማህበራዊ ሚዲያና በራሳቸው ኔትወርኮች የስም ማጥፋት ዘመቻ ደርሶብኛል። ይሄ ሁሉ የሆነው የህሊና እስረኞች አሉ ብዬ ስላመንኩና ሁለተኛ ያ ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ በፍጥነት እንዲታወቅ ስለተደረገ ውሳኔ የማስቀየሪያ ጊዜ አጣን፤ ሁለተኛ የህሊና እስረኛ የሚባል ነገርም እንዳለ ተጋለጠ፤ እንግልትና ስቃይም እንዳለ ተጋለጥን የሚል ስሜት የደረሰባቸው ናቸው።

በኔ እምነት ይህንን ማድረጌ ትክክል ነው፤ ለትግራይም ህዝብ እንዲሁ ለህወሃትም ችግሩ ካለ መታረሙ የሚጠቅም እንጂ እንደሆነ አይጎዳም።

ሰዎች በመደብደባቸውና በመታሰራቸው ህወሐት የሚያተርፍ አይመስለኝም። ፕሮግራሙም ላይ እንዳስቀመጠው ለዲሞክራሲ የሚታገል ድርጅት ነው። ለዲሞክራሲ የሚታገል ከሆነ እንግልትን መፍቀድ የለበትም፤ በህገ መንግሥቱ መሰረት የህሊና እስረኞች ሊኖሩ አይገባም። ስለዚህ የወሰድኩት አቋም ትክክል ነው። ትክክለኛ አቋም በመውሰዴ ግን የጥፋት አቋም ያራምዱ የነበሩ ኃይሎች ስልጣናቸውን ተገን አድርገው የማይገባ ዛቻና ድርጊት ፈፅመውብኛል።

ቢቢሲ፡ ደረሰብኝ የሚሉት ማስፈራሪያና ዛቻ እርስዎ ዛዲግ በመሆንዎ የደረሰብዎት ነው? ወይስ መነሻ አለው? 

አቶ ዛዲግ፡ በአጠቃላይ ፓርቲውን ከተቀላቀልኩ ጀምሮ የባዳነትና የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማኝ ተደርጓል። እኔ ብቻ ሳልሆን በርካታ ከራያ የመጡ ሰዎች ይህንን ስሜት ይጋራሉ። ተሰባስበንና ተገናኝተን ስናወራ ሁሉም ይህንን ይናገራል፤ ይሄ ጥቃቱና ማግለሉ ነው። በኔ እምነት የወሰድኩት ትክክለኛ አቋም ለጥቃት ዳርጎኛል፤ ያን ነገር ባላደርግ ኖሮ መገለሉ፣ መገፋቱና አድልዎ ይኖራል፤ ነገር ግን ወደዛ ደረጃ አይሸጋገርም ነበር። ያ አምባገነኑ ቡድን የህሊና እስረኞች መፈታት፣ የማዕከላዊ መዘጋትን የመሳሰሉ ውሳኔዎችና እርምጃዎች በሞኖፖሊ (ብቻዬን) ተቆጣጥሬ የነበረውን ስልጣን ያሳጡኛል፤ የማታ ማታ ኢትዮጵያ እውነተኛ ዴሞክራሲ ሊኖራት ነው የሚል ስጋት አድሮበታል። ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለእንደነዚህ አይነት ሰዎች ቦታ አይኖራትም፤ የምትሰጠውም ስልጣን አይኖርም።

ቢቢሲ፡ እርስዎ ያሳዩት የፖለቲካ እድገት በሌሎች አጋር ድርጅቶች በርታ ባይነትና ድጋፍ የተገኘ መሆኑን ገልፀው ህወሃት ግን ይህንን ይቃወም እንደነበር ገልፀዋል። ምን ማለት ነው? ምን ተጨባጭ መረጃ አለዎት?

አቶ ዛዲግ፡ በአንድ ወቅት ጉባኤ ላይ በቀረበ ግምገማ እኛ ያላፀደቅነው ስልጣን ነው የተሰጠው ተብሎ ቀርቦብኛል። ሌሎች በርካታ በኢህአዴግ ውስጥ የሚገኙ መሪዎች ወጣት ሰው ሲያዩ የስራ ፍላጎት ያለው ታታሪ ሰው ሲያዩ ደስ ይላቸዋል። ከብዙዎች ጋር አብረን ሌት ተቀን ሰርተናል። የማቅረብ ፣ የማገዝን፣ ቀናነትና የመሪነት ባህል አይቻለሁ። ህወሃት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ግን መጀመሪያውኑ ወጣት ወጥቶ እንዳይታይ በተለይ ደግሞ ከእኔ አይነት አካባቢ የመጣ ሲሆን የበለጠ ጨክነው ይገፋሉ፤ ለሌላው ትግራይ ወጣትም ቢሆን የሚያቀርቡ ሰዎች አይደሉም፤ እንደ እኔ አይነት ከራያ ለመጣ ሰው ሲሆን ግን ይበረታል።

ሌላው ቢቀር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ዴሊቨሪ ዩኒት ሚንስትር ስሆን በጠቅላይ ሚንስትሩ አቅራቢነት ነው፤ ይሁን እንጂ ለማፅደቅ ከስምንት ወር በላይ ወስዷል፤ ከዛም በላይ አላፀድቅም ብሎ ህወሐት እስከ መጨረሻው ሞግቷል።

በየደረጃው ኃላፊነት የተሰጠሁባቸው ቦታዎች ህወሐት ጠይቆ አይደለም የተሰጠሁት፤ የነበርኩባቸው የኃላፊነት ቦታዎችም የፌደራል መንግሥት የተለያዩ ቦታዎች ናቸው፤ ያም ቢሆን ህወሐት ተገፍቶ ተለምኖ ነበር ሲያፀድቅ የነበረው፤ አንዳንዴም አላፀድቅም ብሎ ያሰናክላል። ይህ የሚሆነው በእኔ እምነት አንደኛ ወጣት በመሆኔ፤ ሁለተኛ የራያ ልጅ በመሆኔ ነው። ሁለቱ ህወሐት ውስጥ የሚያስገፉ ናቸው።

ቢቢሲ፡ የማንነት ጥያቄን ሙሉ ለሙሉ መልሻለሁ ከሚል ድርጅት ጋር ላለፉት ዓመታት አብረው ሲሰሩ ቆይተው አሁን የራያ ማንነት ጥያቄ አለ ብለው መጥተዋል። ለመሆኑ የራያን የማንነት ጥያቄ እርስዎ በህወሃት ውስጥ እያሉ አንስተው ያውቃሉ?

አቶ ዛዲግ፡ ደብዳቤ ላይ በግልፅ እንዳመለከትኩት ህወሐት ውስጥ እያለሁ ማንሳት ብቻ ሳይሆን ታግየባቸዋለሁ። በመታገሌ፣ በመጠየቄ ደግሞ ጥቃት ደርሶብኛል፤ መገለል ደርሶብኛል፤ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዶብኛል። አሁንም እተካሄደብኝ ነው። ስለዚህ ሁሉንም ነገሮች አንስቼ የታገልኳቸው ነገሮች ናቸው።

የተሰጠኝ ምላሽ ደግሞ አንዳንዶቹ እናየዋለን የሚል ሲሆን፤ ሌሎቹ ደግሞ ይሄ ክህደት ነው… አንዳንዴ ‘ሊበራል’ ስለሆንክ ነው… ሌላ ጊዜ የአማራ ልጅ ስለሆንክ ነው፤ ሌላ ጊዜ ትግሬነትህን ስለምትጠላ ነው ይላሉ። እንደየ ግለሰቡና እንደየ ስብሰባው ሁኔታ የተለያየ ምላሽ ነበረው። አንድ አይነት መልስ ያጋጠመበት ሁኔታ አላውቅም፤ለመሬት አልታገልንም ግድ የለም ሕዝቡ ይወስናል የሚሉም ነበሩ። ዞሮ ዞሮ እኔ ታግያለሁ፤ ጥያቄው ይህን ነገር በአዎንታዊ መልክ አይተው የተቀበሉት ሰዎች የሉም ከሆነ ፤አላውቅም። መጨረሻ ላይ እንደማይቀየር ሳውቅ ተስፋ ስቆርጥ ወጥቻለሁ።

ቢቢሲ፡ ሌላው ያነሱት ጉዳይ ህወሃት ከለውጡ በተቃራኒ ቆሟል የሚል ነገር ነው። ምን ማለትዎ ነው?

አቶ ዛዲግ፡ በእኔ እምነት የሐገራችን ህዝቦች ዲሞክራሲ ያስፈልጋቸዋልም፤ ይገባቸዋልም። ያስፈልጋቸዋል ሲባል አገራችን ውስጥ በአስተሳሰብ በሃይማኖት በብሔር የሚገለፅ ብዝሃነት አለ። ይህንን ደግሞ አቻችሎ ለመሄድ የሚያስችለው የዲሞክራሲ ስርዓት ነው። የአገራችን ህዝብ በተለያየ ጊዜ መራር ትግል እያደረገ፣ ውድ ዋጋ እየከፈለ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማስፈር የሚያስችል በርካታ ድሎችን ለመፍጠር የታገለ ህዝብ ነው። እነዚህ ድሎች ግን በነጣቂዎችና በጥቂት ስልጣን ፈላጊዎች እየተወሰዱ፤ እድሎች እየመከኑ ነበርና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮነን እየተመራ ያለው ለውጥ ይህንን አዙሪት የሚቀጭ ነው።

እንደ ከዚህ ቀደሙ ከንፈራችንን እየመጠጥን በሃዘን የምናስታውሳቸው ድሎች ሳይሆን የማይመክን ወደኋላ የማይመለስ እድልን አግኝተናል። ህወሃት ይህንን መደገፍ ነበረበት፤ ነገርግን በተለያየ ወቅት ያወጣቸው መግለጫዎች፣ መሪዎች በሚዲያ የሚያስተላልፉት መልዕክት፣ በአጠቃላይ በኢህአዴግም ሆነ በመንግሥትም እየተንፀባረቀ ያለውን አቋም በቅርበት የመረዳት እድል አለኝ፤ የመወያየት እድል አለኝ። እናም… በእኔ አጠቃላይ ግምገማ ህወሐት ለውጡን አልተቀበለም።

ይህ ለውጥ ደግሞ በእኔ እምነት በጣም ወሳኝ ለውጥ ነው። ከዚህም የተሻለ ዲሞክራሲ ያስፈልገን እንደሆነ እንጂ የሚያንሰን አይደለም። ግን ይህንን ትንሹን ለውጥ እንኳን ካልተቀበለ፣ ሌላው ቢቀር እስረኞች ሲፈቱ የተንፀባረቀው ነገር፣ የነበረው እሰጥ አገባ፣ መሪዎችና ግለሰቦች ያሳዩት ነገር፣ በግሌም የደረሰብኝ ጥቃት፤ አይደለም ሰፊ ዲሞክራሲን የመቀበል፤ ትንሿን ተወላግዶ የበቀለውን የማረም ሂደት እንኳን ያለመቀበልና ለማደናቀፍ መታተር ነበረ። በእኔ አተያይ ህወሐት ለውጡን የተቀበለ አልመሰለኝም።

ቢቢሲ፡ ለውጡን በተመለከተ በተሰጠው መግለጫ ወቅት የፖለቲካ እሥረኞች እንደሚፈቱ ተገልፆ ከዚያ በኋላ የተባለው በተደጋጋሚ ተቀይሯል። ምን ነበር የተፈጠረው?

አቶ ዛዲግ፡ ከአንዳንድ የህወሐት ፖለቲካ አመራሮች የፖለቲካ እስረኞች ሳይሆን በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ ብየ ይፋ እንዳደርግ የማስፈራሪያ፣ የስድብ፣ የዛቻ ውርጅብኝ ተፈፅሞብኛል።

ቢቢሲ፡ ከህወሃት አመራሮች ብቻ ነው ዛቻው የመጣው?

አቶ ዛዲግ፡ ይሄ የመጣው ፓርቲው ውስጥ ካሉ ሁለት ግለሰቦች እና ሌላ ቦታ ካሉ ሁለት አመራሮች ነው። ከህወሃትጋር ጋር ቅርበት በዛቻውና በማስፈራራቱ በተዘዋዋሪ ተሳትፈዋል። ሌላው ሰው ግን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎችም ደስተኛ ነበሩ። ከዚያ በኋላ ሚዲያዎች መግለጫውን እንዲያስተካክሉ ተደርጓል።

ቢቢሲ፡ እንዲስተካከል የተደረገው በህወኃት ጫና ነው ማለት ነው?

አቶ ዛዲግ፡ ጫናው የመጣው ህወሃት ውስጥ ባሉ አንዳንድ አመራሮች ነው። የደወሉልን ግለሰቦች ቢሆኑም የህወሐት አመራሮች ነበሩ።

በወቅቱ አለቃዬ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ነበሩ፤ ሚንስትር ነኝ። ከእኔ በስልጣን ያነሱ የህወኃት አመራርና ከስልጣን የወረዱ ሁሉ ሳይቀሩ ደውለው ማስፈራሪያና ዛቻ አድርሰውብናል። እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ በስራ ላይ ያሉ ሰዎችም ማስፈራሪያ አድርሰውብኛል።

ከዚያ በኋላ በተደረጉ ስብሰባዎች እና እራሴን መከላከል በማልችልባቸው የማዕከላዊ ስራ አስፈፃሚ መድረኮችም ላይ ይህን ነገር ሆን ብለው አንስተዋል። የቀለም አብዮተኛ ነው፣ ለጥቃት አጋለጠን፣ ‘ሊበራል’ ነው፤ እያሉ የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም ዛቻና ማብጠልጠል ፈፅመውብኛል።

ቢቢሲ፡ በ13 ኛው የህወሃት ጉባዔ ላይ ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ታጭተው ሳይመረጡ ቀርተዋል። በዚህ አኩርፈው ነው ፓርቲውን የለቀቁት የሚሉ አስተያቶች ይሰማሉ። ለዚህ ያለዎት ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ ዛዲግ፡ መጀመሪያ ጉባዔው ላይ ስጠቆም፤ አንድ የማላውቀው ሰው ነበር የጠቆመኝ። ድጋፍም ተቃውሞም ቀረበ፤ በወቅቱም እኔ ራሴ እጄን አውጥቼ እኔ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል መሆን አልፈልግም ብዬ ተናግሬያለሁ። ይህ ጉባኤ 1500 ሰዎች የተሳተፉበት ነው፤ በነዚህ ሁሉ ሰዎች ፊት የተነገረ ነገር ውሸት አይደለም፤ ከእውነት ጋር ካልተጣሉ በስተቀር።

የኔ የመልቀቂያ ደብዳቤም መርህ ላይ እንጂ ኩርፊያ አያሳይም። በእኔ እምነት ህወሃት ለእኔ የማይሆን ድርጅት እንደሆነ፤ በተለይ መሪዎቹ ዲሞክራሲያዊ እንዳልሆኑ ከተገነዘብኩ ውዬ አድሬያለሁ። ትክክለኛ ጊዜ እየጠበቅኩ ነበር፤ ስለዚህ ይሄ የሚባለው ነገር ተራ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው። ማንኛውም ሰው ከህወሃት ሲወጣ (ትላልቅ መሪዎች ሳይቀር) ማንኳሰስ፣ ከፍተኛ የሆነ ስም ማጥፋት ዘመቻ፣ በሬ ወለደ ወሬ ማስተላለፍ፣ ስራ እንዳያገኙ፣ የግል ሕይወታቸውን እንዳይመሩ የማድረግ ተግባር በየተለያየ ጊዜ እንዳጋጠመ በ1993 ዓ.ም አይተነዋል። ከዚያም በኋላ እንዲሁ። እኔ በመልቀቂያ ደብዳቤዬ ላይ ‘በጥይት እንነጋገራለን” ያለኝን ሰው ስም እንኳን አልጠቀስኩም፤ ምክንያቱም ጥያቄዬ የመርህ ጥያቄ ስለሆነ።

ቢቢሲ፡ የእርስዎ ቤተሰቦች የራያ ተወላጅአይደሉም፤ እርስዎም ስለ ራያ አይመለከታቸውም የሚሉ ሰዎች አሉ። ምን ምላሽ አለዎት?

አቶ ዛዲግ፡ ወደዚህ ደረጃ መውረድ አልፈልግም፤ መጀመሪያ ማንም የሰው ልጅ የትም ቦታ የሚደርስ ጥቃትና ጉዳት ይመለከተዋል።

የነፃነት ታጋዩ ቼጉቬራ አርጀንቲናዊ ቢሆኑም የኩባ ህዝቦች ሲበደሉ ያገባኛል ብለው ታግለዋል። ታጋይ የትም ቦታ ያለ ክፉ ድርጅትን ወይም ነገርን ተቃውሞ መታገል ተገቢ ነው። በመርህ ደረጃ ትግል ድንበር የለውም፤ ደም የለውም ። እኔ ግን የራያ ልጅ ነኝ፤ ኢትዮጵያዊም ነኝ፤ ደብዳቤዬ ላይ የገለፅኩት አያቴ ከራያ የሚወለድ ነው። በዚህ ነጭ ውሸት የራያ ህዝብ እየሳቀ ነው። ስለዚህ በራያ ህዝብ እየደረሰ ያለው ጥቃት ይመለከተኛል። ላልተወለድክበትም አካባቢ መቆርቆር መልካም ነው፤ ትልቅነትን ያሳያል፤ ጠባብ አለመሆንን ያሳያል።

ቢቢሲ፡ ከሁለት ዓመት በፊት ኢህአዴግ ከአሜሪካ የተሻለ ዲሞክራሲ ገንብቷል ብለው ነበር፤ አሁን ያቀረቡት ሃሳብ ደግሞ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አይደለም። ይህንን እንዴት ያስታርቁታል? በዚያን ጊዜ ያቀረቡትን ሀሳብ ከልብ አምነውበትስ ነበር?

አቶ ዛዲግ ፡ በቀጥታ መወሰድ የለበትም። አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የፖለቲካ ምህዳር እንዴት መለካት እንደሚቻልና መለኪያዎቹ ላይ ሐሳቦችን አቅርቧል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት በነቂስ ወጥቶ ድምፅ የሚሰጠው የህዝብ ቁጥር ከአሜሪካ ጋር ስናነፃፅረው በጣም የተሻለ ነው።

ከዛ አንፃር ስናየው እንጂ ከአሜሪካ የተሻለ እፁብ ድንቅ ስርዓት ነው አላልኩም፤ ሊሆንም አይችልም። ዲሞክራሲን ከጀመርን አጭር ጊዜ ነው። እንደማይሆን አውቃለሁ። እንደዛ ብዬ የምናገር ሰው አይደለሁም።

ቢቢሲ፡ መልቀቂያዎ ላይ አሁንም በፖለቲካ ተሳትፎዎ እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል። አዲስ ፓርቲ ሊያቋቁሙ ነው ወይስ ካሉት ፓርቲዎች አንዱን ይቀላቀላሉ? 

አቶ ዛዲግ፡ ያልኩት ጊዜው ሲደርስ አሳውቃለሁ ነው። በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ፓርቲዎች አሉ። ሌላ ተጨማሪ ፓርቲ የሚያስፈልገን አይመስለኝም። እንዲያውም ያሉት ፓርቲዎች ቢሰባሰቡ ጥሩ ነው። እስካሁን ካሉት ፓርቲዎች አንዱን መቀላቀል እንጂ አዲስ ፓርቲ ማቋቋም አልፈልግም፤ ዞሮ ዞሮ ሊቀየር የማይችል ነገር የለም። ጊዜው ሲደርስ ኣሳውቃለሁ አሁን ጊዜው አይደለም።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com