የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) እንዲቆም ተወሰነ

Views: 439

አሁን በሀገሪቱ የተስፋፋው የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) በሚል ስያሜ የሚደረገው የቁማር ጨዋታ እንዲቆም ከስምምነት ላይ መደረሱን የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሲገልፅ፤ የብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር ግን የተለየ አቋም መያዙ ተጠቁሟል፡፡

በሚኒስቴሩ የወጣቶች ስብዕና ልማት ዳይሬክተር አቶ ዓለሙ ሠይድ የስፖርት ውርርድ በሚል የሚካሄደው የቁማር ጨዋታ እንዲቆም መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ የስፖርት ውርርድ የቁማር ጨዋታ በዜጎች ስነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አጠቃላይ የሚያደርሰውን ችግር 26 አባላት ባሉት የፌዴራል የአሉታዊ መጤ ልማዶችና አደንዛዥ ዕፅ ግብረ ኃይልና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ የሆኑበት መድረክ በማዘጋጀት የሚያደርሰው ችግር እንደተፈተሸ ተጠቁሟል፡፡

በዚህም መሰረት በጥር ወር ውስጥ ለስፖርት ውርርድ በሚል ይሰጥ የነበረው ፈቃድ የቆመ ሲሆን፤ አይጠቅምም ተብሎ ከተወሰነ በሥራ ላይ የሚገኙት አቋማሪ ድርጅቶች የውላቸው ጊዜ እስኪጠናቀቅ ብቻ ሊቆዩ እንደሚችሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ‹‹በወቅቱ በተደረገው መድረክ የብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያመጣንለት አዲስ የመዝናኛ ቴክኖሎጂ ነው›› ማለቱን አስታውሰው፤ ግብረ ኃይሉና በመድረኩ የተገኙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ተወካዮች ድርጊቱ ቁማር እንደሆነ ለአገር ፀር መሆኑን አምነው እንዲቆም መግባባት ላይ ቢደርሱም፤ አስተዳደሩ ግን ለሕዝቡ መዝናኛ ቴክኖሎጂ ነው በሚል በአቋሙ መፅናቱን ገልፀዋል፡፡

የስፖርት ውርርድ ቁማር እንጂ ቴክኖሎጂ አለመሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ ‹‹ሕዝቡ እንደማይጠቅመው እየተናገረ ብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳደር ይህን መሰል አቋም መያዙ ለሕዝብ የተቋቋመ ድርጅት ቢሆንም እንኳ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ግን የሕዝብ ውግንናው አጠራጣሪ ነው፡፡ ችግሩን ለማቃለልም ዝግጁ አይደለም›› ብለዋል፡፡

በክልል የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው ፈቃድ አሰጣጡን እንዲመረምሩ፣ ያልጀመሩት ደግሞ ከክልል ፕሬዚዳንቶች ጀምሮ የሚመለከታቸው የቢሮ ኃላፊዎች ፈቃድ አሰጣጡን እንዲያጤኑና ፍቃድ እንዳይሰጥ መግባባት ላይ መደረሱን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፤ እርምጃ መውሰድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት በመጀመሩ ይዋል ይደር እንጂ ችግሩ እልባት እንደሚያገኝ ጠቁመዋል ሲል የዘገበው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com