በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የቻይና ከፍተኛ ባለስልጣናት ተባረሩ

Views: 233

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሟቾች ቁጥር ከአንድ ሺህ በላይ መድረሱን ተከትሎ ቻይና በሽታውን በአግባቡ አልተቆጣጠሩም ያለቻቸውን በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት “ከሥልጣን ማባረሯ” ተገለጸ።

ከሥልጣን ከተነሡት መካከል የሁቤይ ግዛት የጤና ኮሚሽን ሓላፊ እና የኮሚሽኑ ዋና ጸሐፊ ይገኙበታል።

በተጨማሪም የግዛቱ ቀይ መስቀል ምክትል ዳይሬክተር ዣንግ ቂን “ሥራን ቸል በማለት” እና “እርዳታዎችን በአግባቡ ባለመያዝ” በሚሉ ምክንያቶች አባርራለች።

ሁለቱ የሁቤይ ግዛት ባለሥልጣናት በሌሎች ሰዎች እንደሚተኩ የቻይና ብሔራዊ የጤና ኮሚሽን ምክትል ዳይሬክተር ዋንግ ሄሽንግ ተናግረዋል።

በትላንትናው ዕለት በሁቤይ ግዛት ብቻ ሪከርድ ሆኖ የተመዘገበ የ103 ሰዎች ሞት የተከሰተ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 1016 ደርሷል።

ነገር ግን በአገር አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ቀን በፊት ከነበረው 20 በመቶ ማለትም ከ3062 ወደ 2047 መውረዱ ተገልጿል።

ከሁቤይ ግዛት ቀጥሎ በኮሮና ቫይረስ ክፉኛ የተጠቃው ሁዋንግጋንግ ግዛት የጤና ኮሚሽን ሓላፊም ከሥልጣን መወገዳቸው ተጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት በመላው ቻይና ውስጥ 42 ሺህ 200 የተረጋገጡ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች መኖራቸውም ታውቋል።

ከእነዚህ ሕመምተኞች መካከል 31 ሺህ 728ቱ በሽታው በተነሣበት ሁቤይ ውስጥ መሆናቸውን ብሎም 974 ሞት መመዝገቡን የግዛቱ የጤና ኮሚሽን አረጋግጧል።

በሌላ በኩል ትናንት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ አራት አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ ቁጥሩ ወደ ስምንት ከፍ ብሏል።

በተመሳሳይ ጃፓን ውስጥ በዮኮሃማ ወደብ እንድትቆም በተደረገችው ዳያመንድ ፕሪንስስ መርከብ ውስጥ ከሚገኙ 3700 ተሳፋሪዎች መካከል ተጨማሪ 65 ሰዎች መያዛቸውን ተከትሎ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 135 መድረሳቸውን ቢቢሲን ዋቢ አድርጎ ኢቲቪ ዘግቧል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com