አዴፓ ከለውጡ እያፈነገጠ ነው!

Views: 126

የአዴፓ/ብአዴን ልሳን የሆነችው በኩር ጋዜጣ የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በፊት ገጿ ‹‹ለውጥ የሚባለው ነገር ከቃል ያላለፈ እና ነባሩን አመራር እና ስርዓት ያስቀጠለ በመሆኑ ሀገሪቱን ወደ አደጋ እየከተታት እንደሆነ አስነብባለች::

በኩር ጋዜጣ ከምሁራን ጋር ባደረገችው ቆይታ ምሁራኑ እንዳሉት ‹‹የለውጥ ኃይል የሚባለው መንግስት የአማራን የፖለቲካ ኃይል ያገለለ እና በተቃርኖ የቆመ ነው፤ ለውጡ ነባሩን ስርዓት በማስቀጠሉ ምክንያት ሀገሪቱን ወደ አደጋ እየከተታት ነው›› ብለዋል፡፡

“የለውጥ ጊዜው በተራዘመ ጊዜ እንኳን ተቋማዊ ማሻሻያ አላደረገም” በማለት ትችታቸውን የሚጀምሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ዮናስ ናቸው:: ይህ መሆኑም በትናንት እና በዛሬው መካከል ያለውን ልዩነት አሳጥቶታል ብለዋል::

 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫም እየተደጋገመ ነው የሚሉት ዶ/ር ዮናስ በለውጥ ጊዜ ላይ ስለሆን ነው እያሉ ህግን አለማስከበር የመንግስትነት ሚናው ምንድ ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ::
“በቀድሞ አፋኝ ኃይሎች በሚመራ የህግ እና የፀጥታ ተቋም ውስጥ ለውጡን ገቢራዊ ማድረግ አይቻልም” የሚሉት ዶክተር ዮናስ ይህ ባለበት ሁኔታ በተቋማት መካከል መናበብ ሊኖር አይችልምም ብለዋል::

ለአብነት በሀገሪቱ ተማሪ ሲታገት የፌዴራል ፖሊስ የምርመራ ክፍል ምን ይሠራል? ኃላፊነቱን ባለመወጣቱስ ምን ተደረገ? የሚሉት ዶ/ር ዮናስ:: በተማሪዎች እገታ መንግስት ተጠያቂ ነው ሲሉ ለበኩር ጋዜጣ ተናግረዋል::

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነታቸውን በማይወጡ አስፊፃሚ አካላት ላይ እርምጃ ሲወስዱ አይታይም:: የሀገሪቱ ሠላም እያደረ እየተናጋ ሲሄድ “የለውጥ ጊዜ ላይ ስለሆን ነው” እያሉ ማሳበቡም ሚዛን አይደፋም ይላሉ የህግ ባለሙያው::

በሠላም እጦት ምክንያት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደት የተስተጓለበት፣ የሃይማኖት ተቋማት ጥቃት እየደረሰባቸው፣ በነፃነት ሃይማኖታዊ በዓላትን ማክበር እንኳ ያልተቻለበት የፖለቲካ ድባብ ተፈጥሯል:: በዚህ የከፋ ድባብ ላይ ደግሞ ነሃሴ 10/2012 ዓ.ም ምርጫ ይደረጋል ተብሎ ታቅዷል በማለት አብራርተዋል::

ዶክተር ዮናስ ህግ ሳይከበር እንኳን ዲሞክራሲ ወደ ዲሞክራሲ መንገድም መጓዝ አይቻልም ይላሉ:: ለውጥ የሚባለው ከቃል ያለፈ እና ነባሩን አመራር እና ስርዓት ያስቀጠለ መሆኑ ሀገሪቱን ወደ አደጋ እየከተተ ነው ብለዋል::

አቶ ልደቱ አያሌው አሁን ያለው የሀገሪቱ መንግስት ወደ የት እንደሚሄድ እንኳ ግልፅ ፍኖተ ካርታ የሌለው እና የመንግስትነት ቁመና የሌለው አድርገው ይወስዱታል ፤ለዚህም የሀገሪቱ ሁነኛ መፍትሔ የሽግግር መንግስት ነው ይላሉ ስትል በኩር ጋዜጣ አስነብባለች::

ሌላኛው በኩር ጋዜጣ ያነጋገረቻቸው ምሁር በጎንደር ዩኒቨርስቲ የፌዴራሊዝም መምህር የሆኑት አቶ አይተነው ሙሉ ‹‹ሀገሪቱ በስውር ያሉ ኃይላት ወደ ሚጠመዝዙት ኢ-መንግስታዊ ሁኔታ እያመራች ነው›› ይላሉ::

መደበኛ የመንግስት ተቋማት በኢ-መደበኛ አካላት ብልጫ ተወስዶባቸዋል:: በኢ-መደበኛነት የታጠቀው ኃይል ከመንግስት መደበኛ የጸጥታ ኃይል በላይ ሆኖ የአምልኮ ቦታዎችን ያቃጥላል፤ ተማሪ ያግታል:: በአንዳንድ አካባቢዎችም ነጻ ቀጣና ወይም ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆኑ አካባቢዎች ተፈጠረዋል:: ለዚህም አቶ አይተነው የወለጋ አካባቢን በአብነት ያነሳሉ::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ‹‹ቤተክርስቲያን የሚያቃጥል፣ መስጊድ የሚያወድም፣ ተማሪን የሚገድል፣… ነውረኝነትን ባህል ያደረገ የጥፋት መንገድ ተከፍቷል›› ብለዋል:: ነገር ግን ይላሉ አቶ አይተነው ሙሉ ‹‹ ይህን ማስተካከል ያለበት ራሱ መንግስት ሆኖ እያለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ሌላው አብረው ችግሩን ከመናገር ውጭ የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ አልሰሩም›› ይላሉ::

ባሳለፍነው ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ደ/ር) ለፓርላማ አባላት ያደረጉት ንግግራቸው እንደከዚህ ቀደምቶቹ የተመሳሰለ እንጅ ያደገ መፍትሔ ይዞ እንዳልመጣ ይናገራሉ:: አቶ አይተነው እንደሚሉት አሁን ያለው ወከባ እና ትርምስ የሚፈጠረው ብዙው በመንግስት እውቅና ነው ይላሉ:: ከዚያም ህዝቡ ሲያማርር ህግ አስከበርኩ ብሎ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎችን ያሥራል::

በተለይ የለውጥ ኃይል የሚባለው መንግስት የአማራን የፖለቲካ ኃይል ያገለለ እና በተቃርኖ የቆመ ነው ይላሉ አቶ አይተነው::

ህግ ለማስከበር የጸጥታ ተቋማት በሙያ እና በክህሎት መዋቀር ሲገባቸው ተረኝነትን ለማስቀጠል በሚመስል መንገድ በብሔር መሆኑ በሀገሪቱ ለውጡ እንዲከስም አድርጓል የሚሉት ደግሞ ዶክተር ዮናስ ናቸው::፡

እንደ ዶክተር ዮናስ ገለጻ ቢያንስ የጸጥታ ተቋሙ ከፖለቲካ ጫና በተላቀቀ ሁኔታ በግልጽ በሙያ ሊደራጅ ይገባ ነበር::

የተቋማት ስርዓታዊ አሰራር እና መናበብን ማሳደግ፤ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ተቋማትን በአሰራርም ሆነ በሰው ኃይል እንደገና ማደራጀትን በቀዳሚ መፍትሔነት ያስቀምጣሉ:: የለውጥ መንግስት የሚባለው በጣም የዘገየ እና ተቋማዊ አሰራሩን ፈጥኖ አለማሻሻሉ የአደጋ ምንጭ መሆኑንም ምሁራኑ ይናገራሉ::

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com