‹‹የሕዝብ ታዛቢዎች›› ከሰሙ፤ ሲቭል ማኅበራት ምርጫን ለመታዘብ ተመራጭ ሆኑ

Views: 195
  • በምርጫ 97 ሲቭል ማኅበራት ምርጫውን መታዘብ እንደሚችሉ ውሳኔ ያሳለፉ ዳኛ፣ በሰፈራቸው በልዩ ኃይል ተደብድበዋል፤ በልዩ ሥፍራም ታስረዋል!

(ዜና ሃተታ)

ጌታቸው ወርቁ

 

ገለልተኛ ያልሆኑ አካላት፣ ‹‹የሕዝብ ታዛቢ›› በሚል ሥያሜ፣ ምርጫ እንዲታዘቡ የሚደረግበት ሕገ-ወጥ አሰራር መቅረቱን ምርጫ ቦርድ ገለጸ፡፡ በ1997 ዓ.ም የምርጫ ጉዳዮች በፍርድ ቤት መታየት ከጀመሩ በኋላ፣ ፊት በማጥቆር የጀመረው የገዢው ፓርቲ ጫና፣ በድብደባ ተጠናቅቆ፤ ፍርድ ቤት ሥራ እስካቆም ጊዜ ድረስ፣ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት ሲሉ የሕግ ምሁሩ አቶ ብርሃኑ ታየ ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጸዋል፡፡

ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ፣ የሲቭል ማኅበራት ምርጫ እንዳይታዘቡ ተከልክለው፤ በምትካቸው ‹‹የሕዝብ ታዛቢ›› በሚል ሥያሜ፣ ምርጫ ይታዘቡ የነበሩ ኃይሎች፣ ለገዢው ፓርቲ ወገናዊ መሆናቸው፣ ቦርዱ በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ እንዳይሆን አድርጓል ሲሉ የምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ለኢትዮ-ኦንላይን ገለጹ፡፡

ህወሓት/ኢሕአዴግ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ፣ የሲቪክ ማኅበራት ምርጫ እንዳይታዘቡ ሲከለክል፣ በምርጫ ቦርድ የሕግ መዋቅር ውስጥ ‹‹የሕዝብ ታዛቢ›› የሚል ተተኪ አሰራር ዘርግቶ፤ ተአማኝ አካላቱን አሰማርቶ እንደነበር ባለድርሻ አካላት በጋራ ይገልፃሉ፡፡

‹‹በመራጭ ሕዝቡ ዘንድ ብዙ አቤቱታና አስተያየት ለቦርዱ የሚቀርበው በምርጫው አስፈፃሚዎችና ‹‹የሕዝብ ታዛቢ›› ተብለው በሚቀርቡት ሰዎች ገለልተኛ አለመሆን ላይ ነው›› ሲሉ ለኢትዮ-ኦንላይን የገለጹት የምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስ፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች ገለልተኛ ካልሆኑ ደግሞ አሰራሩን መቀጠል ጥቅም የለውም፤ አስፈላጊም አይደለም›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ይህን አሰራር ከሕጉ ውስጥ እንዲወጣ አድርገናል፤ ስለዚህ የሕዝብ ታዛቢ የሚባል አሰራር ሕግ ውስጥ ስለሌለ ሕጋዊ አይደለም በማለት ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

ማንኛውም የሲቭል ማኅበራት ተመዝግበውና እውቅና አግኝተው በሀገር አቀፍ ደረጃ ምርጫውን በገለልተኝነት መታዘብ ይችላሉ ሲሉ የቦርዱ አማካሪ ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጸዋል፡፡

እነዚህን ማኅበራት ቦርዱ የተቋቋሙለትን ዓላማ በማየት እውቅና ይሰጣል ሲሉ ለኢትዮ-ኦንላይን የገለጹት ወ/ሪት ሶሊያና፣ የእውቅና ሠርተፍኬታቸውን እየያዙ፣ የምርጫ ታዛቢዎቻቸውን አሰማርተው ምርጫውን መታዘብ ይችላሉ፤ አይከለከሉም በማለት አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን፣ ድርጅቶቹ የተቋቋሙለትን ዓላማ ሲገልጹ፣ ምርጫ መታዘብን እንደ አንድ ዓላማቸው ወይም ሥራቸው አድርገው መግለጽና ማካተት አለባቸው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በዚህ አሰራር ቢያንስ ለምርጫ አሰብ ያደረጉ፣ ምርጫ ለመታዘብና ለማስተማር ዕቅድና ዝግጅት ያላቸው አካላት ምርጫውን መታዘብ ስላለባቸው ነው ይህን መሥፈርት መመሪያው ላይ ያስገባነው ብለዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ ውስጥ እነዚህ የሲቭል ማኅበራት ወደ ምርጫ ቦርድ መጥተው የሚመዘገቡበትንና እውቅና የሚወስዱበትን ጊዜ እናሳውቃለን በማለት ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስ ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጸዋል፡፡

በ1997 ዓ.ም በምርጫ መታዘብ ሚና ላይ መሰማራት የፈለጉ የሲቭል ማኅበራት በምርጫ ቦርድ ላይ ያቀረቡትን ክስ ሲመለከቱ ከነበሩ ሁለት ዳኞች አንዱ የነበሩትን ዳኛ ብርሃኑ ታየ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ዘጋቢያችን አናግሯቸዋል፡፡

ከመጋቢት 1996 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1999 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዳኝነት ሙያ አገልግያለሁ የሚሉት የሕግ ምሁሩ አቶብርሃኑ ታየ፤ የምርጫ ጉዳይን ማየት እስከጀመርንበት 1997 ዓ.ም ጊዜ ድረስ በዳኝነት ሥራዬ ብዙም ችግር አልነበረብኝም ብለዋል፡፡

ከ1997 ዓም ምርጫ ጋር ተያይዞ የምርጫ ጉዳዮች መታየት ከጀመሩ በኋላ ግን ነገሮች እንደነበሩት መቀጠል አቆሙ፤ ከሥራ አካባቢም ፊት በማጥቆር የጀመረው ጫና፣ በድብደባ ተጠናቅቆ፤ ፍርድ ቤት ሥራ እስካቆም ጊዜ ድረስ፣ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት ሲሉ ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጸዋል፡፡

የምርጫው ውድድር ፉክክሩ መጋል የጀመረው 1997 ዓ.ም ታኅሳስ- ጥር አካባቢ ነው፤ ከዛ እየጋለ መጥቶ እስከ ሚያዚያ 30 1997 ዓ.ም ያ ታሪካዊ ሰልፍ እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስ ደህና ነበር፤ ከዚያ ታሪካዊ ሰልፍ ከተካሄደ በኋላ ግን፣ ፍርድ ቤቶች ላይ የነበረው ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተቋም ደረጃ አስተዳደራዊ ጫና አለ፤ እንደገና ደግሞ በሚዲያ የሚፃፈው ነገር ጫና ነበረው፤ በቤተሰብ ላይ ጫና ነበረው፤ በግልም፣ በጎንም ዳኞች ላይ ጫና ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶች ይደረጉ ነበር ሲሉ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

በተለይ የምርጫውን ጉዳይ የምናይ ሁለት ዳኞች ላይ ጫናው ከፍተኛ ነበር ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ ጫናው በገዢው ፓርቲ ቢበረታም፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚመጣ ጫና ነበር፤ ከገለልተኛ ወገንም ሆነ በጉዳዩ ላይ ጉጉ የሆነው ሕብረተሰብ ሁሉ፣ ፍርድ ቤቱ ላይ ተስፋ በመቁረጥና ምንም ሊሰሩ አይችሉም በማለት ፍርድ ቤቱና ዳኞች ላይ ጫና ያሳርፉ ነበር ብለዋል፡፡

በወቅቱ ትንሽ ጎላ ብሎ የሚታየው ጫና የሲቭል (ሲቪክ) ማኅበራት የሚባሉት ምርጫ እንዳይታዘቡ በምርጫ ቦርድ ተከልክለው ነበር፤  ምክንያቱ ደግሞ እናንተ የተቋቋማችሁለት ዓላማ ምርጫን መታዘብ አያስችልም በሚል ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ብዙ የሲቪክ ማኅበራት በጋራ የተሳተፉበት ‹‹የሲቪክ ማኅበራት ቅንጅት›› የተባለ ሕብረት በምርጫ ቦርድ ላይ ክስ መስርተው ነበር ሲሉ ትውስታቸውን ለኢትዮ-ኦንላይን የተናገሩት አቶ ብርሃኑ ታየ፣ እኔ ጉዳዩን ያን ያህል የተወሳሰበ ጉዳይ ሆኖ አላገኘሁትም ነበር፡፡

በወቅቱ የጠየቅኳቸው ጥያቄዎች ሁለት ነበሩ፤ አንደኛው የሲቪክ ማኅበራቱን ስትቋቋሙ ምርጫ የመታዘብ ዓላማ አላችሁ ወይ ብዬ ጠየቅኳቸው፤ እነርሱም እንደሌለ ነገሩኝ፡፡

ምርጫ ቦርድን ደግሞ ሲቪክ መኅበራት ምርጫን እንዳይታዘቡ የሚከለክል ወይም የታዛቢዎችን የሚመለከት መመሪያ አላችሁ ወይ ብዬ ስጠይቅ እነርሱም- እንደሌላቸው ነገሩኝ፡፡

ስለዚህ፣ ምርጫ እንዳይታዘቡ ቦርዱ በራሱ ፈቃድ ብቻ እንደከለከላቸው ተረዳሁ፤ በዚህ ላይ ሁሉም ነው የተከለከሉት ወይስ እነርሱ ብቻ ናቸው ለሚለው ጥያቄ፣ የሃይማኖት ተቋማት ግን ተፈቅዶላቸው እንደነበር አረጋገጥኩ በማለት አቶ ብርሃኑ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማትም ከሃይማኖት ተግባር ውጪ ምርጫ የመታዘብ ተግባር የተቋቋሙለት ዓላማቸው ውስጥ አለመኖሩን ለማጣራት ለእነርሱ እንዴት ተፈቀደ ብዬ ስጠይቅ ለሃይማኖታቸው ሲሉ እውነቱን ይመሰክራሉ ሲሉ የምርጫ ቦርድ ጠበቃ መለሱልኝ ብለዋል፡፡

ስለዚህ ጉዳዩ ሃይማኖተኛ ስለሆኑ እውነት ይናገራሉ፤ ሲቪክ ማኅበራት ደግሞ ሃይማኖተኛ ስላልሆኑ እውነት አይናገሩም የሚል መስፈርት ብቻ ሆኖ አገኘሁትና በአዳሪ አይቼ ውሳኔ ሰጠሁ፡፡

ውሳኔዬ የነበረው አንደኛ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የለውም፤ ሁለተኛ በወቅቱ ማኅበራትን የሚያስተዳድረው ሕግ የፍትሐብሄር-ሕጉ ብቻ ነበር፤ በኋላ ነው አዳዲስ ሕጎች የወጡት፡፡

ያኔ በፍትሐብሔር ሕጉ ላይ በምናይበት ሰዓት ማኅበራት በቅድሚያ መስራት ያለባቸው ለዓላማቸው ነው፤ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ከዓላማቸው ጋር የማይጋጭ ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ሕጉ ይፈቅዳል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በመዝገቡ ላይ ይሄን ጠቀስኩና የሕብረተሰቡ ፍላጎት የሚወክሉ ተቋማት መሆናቸውን አወሳሁ፤ በወቅቱ ይህ ጉዳይ ምርጫ ቦርድንም ሆነ ሲቭል ማኅበራቱን አላከራከረም፡፡

ምክንያቱም አንዳንዶቹ የሴቶችን ጉዳይ ሌሎቹ የሕፃናትን ጉዳይ፣ አንዳንዱ በድህነትቸ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ጥቅም ለማስከበር የሚሰሩ ማኅበራት በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡

ከምርጫ ዓላማ  አንዱ ደግሞ የሕብረተሰቡን ጥቅም ያስከብራል የሚባል ፓርቲ የሚመረጥበት ነው የሚሉት የሕግ ምሁሩ አቶ ብርሃኑ፤ የሕብረተሰቡን ጥቅም ያስከብራል የሚባል ፓርቲ ለመወዳደር ምርጫ በሚያደርግበት ሰዓት እነርሱ በድህነትም፣ በሴትነትም ይሁን በሕፃናት መብት የሚከራከሩ ማኅበራትን ምርጫውን እንዳይታዘቡ ማድረግ ምንም ምክንያት አልነበረውም ሲሉ አስረግጠው ይገልፃሉ፡፡

ይህን ሕገ-መንግስቱም አይከለክልም፤ የምርጫ ሕጎችም ገደብ የላቸውም፤ እንዲሁም ፍትሕአብሔር ሕጉ ደግሞ ይፈቅዳል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ነጥቦች አጣቀስኩና ማኅበራቱ ሊታዘቡ ይገባል ብዬ ውሳኔ ሰጠሁ፡፡

ይህ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ አፈፃፀሙም ወዲያው ተጀመረ፤ በዚህ ሁኔታ ሌሎች ማኅበራትም መጥተው ምርጫ ቦርድ ላይ ተመሳሳይ ክስ መሰረቱ፡፡ ይህንንም ሌላኛው ዳኛ አፈፃፀሙን ጨረሱ፡፡ የኔ ውሳኔ እስከ ሰበር ሄዶ ጸንቷል ሲሉ ለኢትዮ-ኦንላይን አስረድዋል፡፡

ሆኖም፣ በዚህ ውሳኔዬ የተነሳ የመንግሥት አካላት ነን ያሉ ኃይሎች በግል ስልኬ ማስፈራራት፣ ዛቻ፣ ጫና ሲያሳድሩብኝ ቆይተው፣ ማኅበራቱ ምርጫ በታዘቡበት ሁሉ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሲሸነፍ ደግሞ የመንግሥት አካላት ነን ያሉት ቡድኖች ቤቴ መጥተው ከነ ወንድሜ ደብድበው እግሬን ሰብረው በልዩ ቦታ አሰሩኝ፤ ሥራዬንም በዚሁ ጫና ለቀቅኩ ብለዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com