የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በአዲስ አበባ በሚገኙ ስምንት ጤና ጣቢያዎች መሰጠት ተጀመረ

Views: 219

በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ የመንግሥት ሆስፒታሎችን ጫና ለመቀነስ በስምንት ጤና ጣቢያዎች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ማስጀመሩን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የመንግሥት ሆስፒታሎችን ጫና ለመቀነስ በከተማዋ ካሉት 99 ጤና ጣቢያዎች በስምንቱ ጤና ጣቢያዎች እናቶችን ለማዋለድ የቀዶ ጥገና አገልግሎት እንዲጀመር ተደርጓል።

ከመላ አገሪቱ ለተሻለ ሕክምና ተልከው የሚመጡ ታካሚዎች በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 13 የመንግሥት ሆስፒታሎች አቅም በላይ ነው ያሉት በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የሜዲካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ወ/ሪት ማኅሌት ግርማ ናቸው፡፡

ይህንን ጫና ለመቀነስ በከተማዋ የሚገኙ ጤና ጣቢያዎች በእውቀት እና በልምድ የዳበሩ ባለሙያዎችን በመመደብ ኅብረተሰቡ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ጥረት እያደረግን ነው ሲሉ ኃላፊዋ ተናግረዋል።

እነዚህን ስምንት ጤና ጣቢያዎች ወደ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከፍ በማድረግ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ዳይሬክተሯ ለኢቲቪ ገልጸዋል፡፡

በጤና ጣቢያዎች የተገልጋዩን ፍላጎት ማርካት ባይቻልም፣ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ቢሮው አመልክቷል።

በአንዳንድ ጤና ጣቢያዎች ላይ የሕክምና ዶክተሮች ተመድበዋል ያሉት ወ/ሪት ማኅሌት፣ ስፔሻሊስት ሐኪሞችን ከሆስፒታሎች ወደ ጤና ጣቢያዎች በማምጣት እንዲሠሩ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በጤና ጣቢያዎቻችን የሰው ኃይል እጥረት ባይኖርም፣ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት የተነሣ የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶች እጥረት መኖሩን ቢሮው አመልክቷል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com