በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ጥቆማዎች 29 መድረሳቸው ተገለፀ

Views: 326

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት ይፋ ከሆነ በኋላ፣ በሽታውንና የበሽታውን ክስተት በተመለከተ 29 ጥቆማዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ክትትል ለሚያደርገው አካል እንደደረሱ ተጠቁሟል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ላይ እንዳመላከተው፣ ጥቆማዎቹ በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውስጥ ለሚገኘው የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ደርሰው ክትትልና ማጣራት ተደርጎባቸዋል።

በዚህም መሠረት በ29ኙ ጥቆማዎች ላይ በተደረገው ማጣራት፤ 14ቱ በበሽታው የሚያስጠረጥሩ ምልክቶች አሳይተው ስለነበረ በሽታው መያዝ አለመያዛቸው እስኪታወቅ ድረስ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው እንዲቆዩ መደረጋቸው ተገልጿል።

ከተጠረጠሩት አስራ አንድ ሰዎች የተወሰዱ ናሙናዎችም ለምርመራ ወደ ደቡብ አፍሪካ መላካቸውንና ስምንቱ ከቫይረሱ ነፃ እንደሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን፤ የሦስቱ ውጤትም ከደቡብ አፍሪካ እየተጠበቀ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በቀጣዮቹ ቀናት በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ የሦስት ሰዎች ናሙናዎች ለምርመራ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚላኩም መግለጫው አመልክቷል።

በመሆኑም ከቻይና የሚመጡ ሰዎች በሙሉ ከሌሎች መንገደኞች ጋር ሳይቀላቀሉ ተገቢውን ሥልጠና ባገኙ ባለሙያዎች አማካይነት አስፈላጊው የሙቀት ምርመራ ቦሌ አየር ማረፊያ ውስጥ እንዲደረግላቸውና የኢሚግሬሽን አገልግሎት የሚሰጥ ልዩ መስኮት እንደተዘጋጀላቸውም ተገልጿል።

ቀደም ሲል በተለያዩ ጊዜያት በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ ስምንት ሰዎች መገኘታቸው ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ በተደረገላቸው ምርመራም ከበሽታው ነጻ መሆናቸው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

በተያያዘም የኮሮና ቫይረስ ከቻይና ውጭ በ25 አገራት መታየቱን እና በፊሊፒንስ እና በሆንግ ኮንግ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።

የዓለም ጤና ድርጅት የዓለም የጤና ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል 675 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንድሚያስፈልግ ገልጿል። አገራትም ለዚህ ስራ ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪውን አቅርቧል።

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com