ዜና

‹‹ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተገናኘ ወደ ቻይና በረራ ማቆም ዋስትና አይሰጥም›› – አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

Views: 830

ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተገናኘ ወደ ቻይና በረራ ማቆሙ ዋስትና እንደማይሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ገለፁ።

ዋና ስራ አስፈጻሚው አየር መንገዱ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተገናኘ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ እንደማያቋርጥም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

አየር መንገዱ በርካታ ዓለም አቀፍ በረራዎችን እንደማድረጉ ወደ ቻይና ብቻ በረራ ማቆም ዋስትና እንደማይሆንም ነው የተናገሩት።

ወደ ቻይና የሚደረገው በረራ ቢቆም እንኳን የቫይረሱ ተጠርጣሪዎች ወዳሉባቸው አገራት በረራ እንደማድረጉ ከስጋቱ ነጻ መሆን አይቻልም ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ አየር መንገዱ በ‹‹ትራንዚት›› ከሌሎች መዳረሻዎቹ በርካታ ቻይናውያንን እንደሚያጓጉዝም ጠቅሰዋል።

መፍትሄው ለደንበኞች እና ሰራተኞች ጤንነት ጥንቃቄ ማድረግ ብቻ ነው ሲሉም አስረድተዋል።

በመሆኑም፣ ቫይረሱን ለመከላከል አየር መንገዱ በመዳረሻ አገራትም ሆነ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከፍተኛ የቁጥጥር ስራ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አያይዘውም፣ የዓለም ጤና ድርጅት የጉዞ እገዳ ማድረግ እንደማይገባ ያቀረበውን ምክር እናከብራለን ብለዋል።

70 በመቶ ቻይናውያን መንገደኞች በትራንዚት አዲስ አበባን እንደሚረግጡ ያነሱት አቶ ተወልደ፣ በማግለል መፍትሄ እንደማይመጣ መረዳት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደምም የኢቦላ ወረርሽኝ ባጋጠመ ጊዜ አየር መንገዱ የሚያደርገውን በረራ አለማቆሙን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት 35 በረራ ወደ ቻይና ያደርጋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com