ጎደሬን የበላው እንጂ ያረሰው ይንቀዋል

Views: 737

ሀ/ ጎደሬ ምን ዓይነት ተክል ነው

ጎደሬ፣ ሌላው ስሙ በእንግሊዘኛ ታሮ (Taro) ነው፡፡  በደቡብ ኤስያ እና ምዕራብ አፍሪካ አገራት ዓይነተ ብዙ ስለሆነ በእኛ አገር የሚለማው Ethiopian taro (Colocasia esculenta  ኮሎካሳ እስኩለንታ)  ይባላል፡፡  ጎደሬ መገለጫው የሥራሥር ምርት ነው፡፡ በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ በተለይም በወላይታ፣ ሐድያ፣ ዳውሮ፣ ኮንታ፣ ከፋ፣ ቤንች፣ ማጂ፣ ጅማ፣ ጋሙጎፋ ዞኖች፣ እንዲሁም በጋምቤላ ክልል  እና ሌሎችም  ለጊዜው ያልጠቀስኳቸው ቦታዎች ይበቅላል፡፡  እንዲሁ በጅምላ በእኛ አገር ሲገመገም ጎደሬን፣ ያረሱት ይንቁታል፣ የበሉት ያወድሱታል ነው ነገሩ፡፡  በአብዛኛው በሚታረስበት ቦታ ለቤት ፍጆታ ያውሉታል፡፡ ገበያ ላይ በብዙ አልተለመደም፡፡ ሲታማ የደሃ ምግብ” ተብሎ ነው፡፡ አምራቾቹ ከሌላ አካባቢ ለሚሄድ ሰው ውድ ምግብ ብለው አያቀርቡትም፡፡ እንግዳ ሲመጣ ይልቁንም ከምግብ ገበታ ያርቁታል፡፡

በ2ዐዐ8 አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ዳውሮ ዞን፣ ታርጫ ከተማ  ላይ ቶኮ ባኢ የዘመን መለወጫ በአል ነበር፡፡ ከብዙ የአገሪቱ ክፍሎች እንግዶች ተጋብዘው በዚያ በዓል ላይ እኔም ነበርኩ፡፡ የበዓሉ አዘጋጆች ለበዓሉ ተሳታፊዎች ጎደሬን ከአይብ፣ ቅቤ እና ቅመማት ጋር አሰናድተው ለትንግርት አቅርበው ነበር፡፡ ለጉድ ተበላ፡፡ አብዛኛው የመሀል አገር ሰው ለጉድ ከወረደበት በኋላ “የባህል ምግብ ነው”  ከማለት በቀር፣ ከጥፍጥናው ብዛት ተደመመ እንጂ ጎደሬ መሆኑን ያወቀም፣ የጠየቀም አልነበረም፡፡

በዚያው ሳምንት ውስጥ በከተማው በነበሩት ምግብ ቤት “ጎደሬ ሠርታችሁ አቅርቡልን? ” በማለት ሲጠየቁ “አይደረግም፣ የደሀ ምግብ ነው!፣ በቤታችን ብናቀርበው ዳግመኛ ደንበኛ ተመጋቢ ሰው ድርሽ አይልም”  አሉ፡፡ ቢለመኑ አንሰማም አሉ፡፡ ቢቸግረኝ በ 1ዐ ብር ገዝቼ ወደ ምግብ ቤቱ አመጣሁ እና በስንት ልመና ለማለዳ ቁርስ አብረን አሠናዳነው፡፡ ተቀቀለ  በቅቤ፣ አይብ፣ ጨው እና ቅመማት ታሸ፡፡ በእንጀራ  ለ14 ሰው ቀርቦ ተበልቶ ተረፈ፡፡ ይህ ሲሆን የቤቱ እማወራ “አንቺ አቅርቢ እንጂ ጎደሬ ምግብ ነው ብዬ አላቀርብም”  ብላ ተደበቀች፡፡ የተመገቡት ሁሉም ደስተኞች ነበሩ፡፡

“ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” ድሮ ቀረ፡፡ አሁን “ከሞኝ ደጃፍ አዝመራ ይታፈሳል” ሆኗል ነገሩ፡፡ ጎደሬን ለማስተዋወቅ ብዙ ተደክሟል፡፡ ያወቁት ጥቂቶች እየተመገቡ ነው፡፡ ግን ብዙ ይቀራል፡፡ በአገር ውስጥ “የደሀ ምግብ” የሚል መታወቂያ ያገኘው ጎደሬ በቅርቡ ወደ ውጪ መላክ ተጀምሯል፡፡ የኛ ሰውማ በአገሩ የተመረተውን ምርት ጠቀሜታ ሳይረዳው፣ በውድ ዋጋ ከውጪ የሚገባለትን ምግብ እና መድሃኒት ይሸምታል፡፡

ለ/ የጤና ጠቀሜታው ምንድነው?   ማጣቀሻ አንድ

 • በአጥንት መሳሳት ለተጎዱ ሰዎች ጥሩ ምግብ ነው፤
 • ተሰብረው ሕክምና ላይ ላሉት ቶሎ እንዲያገግሙ ይግዛል፣
 • ለስኳር ታማሚዎች የደም ስኳርን ለመቆጣጠር ይረዳል፣
 • ለምግብ ሥርዓተ ስልቀጣ ምቹ ነው፤
 • እበጠት (በማንኛውም የሰውነት አካል ከወደ ውጭ ላለ አካላት፣
 • የቆዳ ህመም ላለባቸው፣
 • ለደም ዝውውር ይረዳል፣
 • ፀረ ካንሰር የሆነ ንጥረ ነገራት አሉት፣
 • አሰር ስለያዘ የልብ ህመም አደጋን ይቀንሳል፣ እና
 • ሌሎችም ብዙ የጤና ጥቅሞች አሎት፡፡

የንጥረ ምግብ ይዘት   ማጣቀሻ አንድ

 • ከድንች የበለጠ ካርቦሃድሬት አለው፣
 • ጥሩ አሰር አለው፣
 • ከማዕድናት፣ ማንጋኒስ፣ ማግኒስየም፣ ፖታስየም፣ ኮፐር፣ እና
 • ከቫይታሚን ውስጥ ቢ6፣ ሲ እና ኢ፣
 • እንዲሁም መጠነኛ ፕሮቲን አለው፡፡

ሐ/ የምግብ አሠራር ዓይነት

1/ እንደተለመደው ቀድሞ ይታጠባል፣ ይቀቀላል፣ይላጣል፣ ተቆራርጦ ይቀርባል ወይም በፈለጉት አሠራር ያዘጋጁታል፡፡ ለምሳሌ በዚህ አይነት  በቀላሉ  ማዘጋጀት ይቻላል፡፡

መቀቀል፣ መላጥ፣ መክተፍ፣ በቅቤ እና ሮዝመሪ ቅጠል በትንሹ መጥበስ፣ ጨው እና የሚፈልጉትን ቅመም መጨመር፣ በቃ፡፡ በዚህ ዓይነት ተሠርቶ የተመገበ ሰው ለምንጊዜም ቃናውን (ጣዕሙን) አይረሳውም፡፡

ጎደሬ ተቀቅሎ የተጠበሰ

 2/ ሥሩ ቀድሞ ይታጠባል፣ ይቀቀላል፣ ይላጣል፣ ይከተፋል፣ እንደ ድንች ወጥ ይሰራል፡፡

የጎደሬ  ወጥ

3/ ይታጠባል ይላጣል፣ በስስ ይከተፋል፣ ይደርቃል፣ ይፈጫል፡፡ ብቻውን በጥንቃቄ ሊፈጭ ይችላል፡፡ ወይም ለዳቦ ከታሰበ ከስንዴ ጋር፣ ለአጥሚት ከአጃ እና ገብስ ጋር፣ ለእንጀራ ከጤፍ ጋር ይፈጫል፡፡በሌሎች አገራት ዱቄቱን ኬክ፣ ብስኩት፣ የተለያዩ ምግቦችን ይሰሩበታል፡፡

4/ ለእንጀራ አጠቃቀሙ ፡ ከነጭ ጤፍ ጋር፣ የደረቀውን ጎደሬ  በ4፣ ለ1 መመጠን ነው፡፡ ይህ ማለት  ከ4 እጅ ጤፍ ጋር 1 እጅ ደረቁን ጎደሬ ሸክሽኮ አደባልቆ፣ የሚፈልጉትን ቅመም አክለው (ለምሳሌ አብሽ፣ድንብላል፣ወዘተ) ማስፈጨት ነው፡፡ በተለመደው አሠራር መጋገር ነው፡፡ እንጀራው ለስላሳ እና ልዩ ጣዕም ይኖረዋል፡፡ ለዳቦም ሲሆን በዚሁ መጠን ከስንዴ ጋር ማዘጋጀት ይቻላል፡፡  ማጣቀሻ ሁለት፣

እንጀራ፣ ነጭ ጤፍ  እና ጎደሬ (4፡1) ተመጥኖ የተጋገረ

መ/ የአመጋገብ ጥንቄቄ

“አሳን መብላት በብለሀት” እንደ ተባለው ጎደሬም ጥቂት ብልሃት ይፈልጋል፡፡ ጎደሬን ተቀቅሎ በትኩስ በልቶ ውሀ አይጠጣም፣ ጎደሬን በልቶ በላዩ ቡና አይጠጣም፡፡ ይቺን ብልሃት የዘነጋ ለደረት ቃር ይጋለጣል፡፡  ይልቅስ የተቀቀለ ጎደሬ በቆጭቆጫ ወይም በሚጥሚጣ ሲበላ ይስማማል፡ ፡

ሠ/ ጎደሬ አዝመራው

ጎደሬን በቀላሉ ማልማት ይቻላል፡፡ ሞቃት ወይናደጋ ይስማማዋል፡፡ የሚተከለው እራሱ ሥሩ ለተከላ ተብሎ የሚዘጋጀው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እንደየአካባቢው ወይም እንደ ጎደሬው ዓይነት ከመጋቢት ወር እስከ ግንቦት ድረስ ይተከላል፡፡ የሚደርሰው ከመስከረም እስከ ታህሳስ ድረስ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው ከህዳር እስከ ጥር ባሉት ወራት ነው፡፡ በሚደርስበት ወቅት ገዝቶ መጠቀም ጥሩ ነው፡፡ በዱቄት መልክ የሚያዘጋጁትን በወላይታ እና አርባምንጭ ማጠያየቅ ነው፡፡

በሚመረትበት አካባቢ የጎደሬ ምርት ለብዙ ቤተሰቦች የኑሮ ደጋፊ ነው፡፡ የጎደሬን ምርት እና ምግብነት ችላ ባንለው ይሻለናል፡፡ በሰፊው ስለ ጎደሬ ማጥናት ወይም መሥራት ያቀደ አንድም ወደሚመረትበት መሄድ ነው፣ ሁለትም የአረካ እና የጅማ እርሻ ምርምር ቢጎበኝ መልካም ነው፡፡                    

ማጣቀሻ አንድ  https://www.healthline.com/nutrition/taro-root-benefits#section1

ማጣቀሻ ሁለት፣  በቀለች ቶላ፣ 2ዐዐ4፣ በዐይነት እንጀራ፣ ለምለም እንጀራ ከብዝሀ ሰብሎች፣ አልፋ

አታሚዎች፣ አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com