የቀይ ሽንኩርት ብክነት በማሳ እና በድስት

Views: 487

መነሻ፡- 

የቀይ ሽንኩርት ምርት በአገራችን ከፍተኛ ነው፡፡ በአንዳንድ የአዝመራ ዘመን ሞልቶ ተርፎ ገበያ ጠፍቶ በስብሶ ይደፋል፡፡ ዋጋው አንዳንዴም ከፍ ይላል፣ ሌላ ጊዜ ዝቅ ይላል፡፡ በምንም ዋጋ ቢገዛ ቀይ ሽንኩርትን በቁሌት ገደልነው እንጂ፣ በአግባብ አልተመገብነውም፡፡ ለጤናችን፣ ለገንዘባችን፣  ላመረተውም ሰው እና ላመረተችው መሬት ዋጋ አልሰጠነውም፡፡ ቀይ ሽንኩርትን በድስት ውስጥ ጨምረን አቁላልተን ለዘመናት ገደልነው፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡

1/ የቀይ ሽንኩርት ጤና በረከት

1.1 ይህ የጤና በረከት መረጃ ጂአን ካርፐር “ፉድ ዩር ሚራክል መደሲን”

(FOOD YOUR MIRACLE MEDECINE) በሚለው መጽሐፏ ላይ የከተበችው ነው፡፡  ማጣቀሻ አንድ

 • ጥሬ ቀይ ሽንኩርት የነቀርሳ (ካንሰር)  አምጪ ጂን  (carcinogens )  ወይም የነቀርሳን ሴሎች (cancer cells) የሚዋጉ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች አሉት፤
 • ቀይ ሽንኩርትን በመደበኛነት በጥሬው መመገብ አስምን ይፋለማል፡፡ በተለየም የሰውነት መቆጣትን (አለርጂ) የሚያስከትሉ ነገሮች ዘንድ ከመቅረብ በፊት ቀድሞ የቀይ ሽንኩርት ጁስ መጠጣት የሰውነት መቆጣትን ይገታል፤
 • ጭንቀትን ለመቀነስ እና ዘና ያለ እንቅልፍ ለማግኘት፣ ቀይ ሽንኩርት መመገብ ይረዳል፤
 • የደም መርጋትን ይከለክላል፣ ቀደምት የአሜሪካ ዶክተሮች “ቀይ ሽንኩርት ደም ያጠራል” ብለው ያዙ ነበር ይባላል፤
 • ግማሽ ፍንካች ጥሬ ቀይ ሽንኩርት በየቀኑ መመገብ፣ የደም ኮልስትሮልን ለመቆጣጠር በእጅጉ ይረዳል፣
 • ለስኳር በሽተኞች የደም ስኳርን በተረጋጋ ደረጃ እንዲቆይ ጥሬ ሽንኩርት ወይም የተቀቀለው ይጠቅማል፤
 • ስብ የበዛባቸውን ምግብ በሚመገቡበት ወቅት፣ ጥቂት የተከተፈ የቀይ ሽንኩርት አብሮ መመገብ ምግቡ ውስጥ የታጨቀው ስብ የደም መታገትን እንዳያስከትል ይከለክላል፤ (ለካስ ለዚህ ኖሯል በርገር ላይ በስስ የተቆረጠ ቀይ ሽንኩርት ጣል የሚደረገው፣)
 • ለጠነከረ ሳል፣ ለኃይለኛ ጉንፋን ግሩም ሽሮፕ ለማዘጋጀት፣ በአንድ ትልቅ ድስት ውስጥ ውሃ ማፍላት፣ በትልቁ ድስት ውስጥ ሌላ አነስተኛ ድስት ማስገባት፣ በዚህ ውስጥ ስድስት መካከለኛ እራስ ቀይ ሽንኩርት በደቃቅ የተከተፈ እና ሁለት ስኒ ያህል ማር መጨመር፡፡ ከሥር ከሚፈላው ውሃ፣ ከውሰጥ ያለውን ድስት ያሞቃል፣ የውስጠኛው ድስት ሙቀት ሽንኩርቱን እና ማሩን በአንድ ላይ ያበስላል፡፡ እስከ ሁለት ሰዓት ቀስ ባለ ሙቀት መቀቀል፡፡ ይህን በሌላ እቃ ማጥለል እና እንደ ሽሮፕ በተወሰነ የሰዓት ልዩነት በሾርባ ማንኪያ መውሰድ ለሳል ጥሩ መድኃኒት ነው፡፡
 • ቀይ ሽንኩርትን በጥሬው ከሌሎች ሰላጣ ምግቦች ጋር መመገብ፣ ለትኩሳት፣ ለጉሮሮ መከርከር፣ ለሳይነስ፣ ለጉንፋን ማስታገሻነት ይረዳል፡፡

1.2 ሌሎች የጥሬ ቀይ ሽንኩርት ግልጋሎት

 • ቀይ ሽንኩርት ፀረ ባክቴሪያ እና ፀረ ፈንገስ ነው፡፡ እበጥ ገላ ላይ ማሰር፣ ላመረቀዘ  ሰውነት የሽንኩር ፍንካች ሞቅ አድርጎ በላዩ ማሠር ይጠቅማል፡፡
 • የቀይ ሽንኩርት ጭማቂ ለራስ ቆዳ ሲቀቡት አዲስ ፀጉር እንዲበል ይረዳል፡፡
 • ንብ ስትነድፍ ፍንካቹ ይታሽበታል፣ መለባለብን ይቀንሳል፡፡

1.3 ጥሬ ቀይ ሽንኩርት ሊያስከትል የሚችለው ችግር

ሀ/ ቃር፣  ግሳት እና ሆድ ውስጥ ጋዝ

ጥሬ ቀይ ሽንኩርት በባህርይው የተነሳ ከተመገቡ ከ ሁለት ሰዓት በኋላ ቃር እና ግሳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ እንዲሁም ሆድ ውስጥ ጋዝ (ፈስ) ያበዛል፡፡ እንደዚህ በጣም የሚቸገሩ ሰዎች ለዚህ ምላሽ እራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ከቶውንም ጥሬ ቀይ ሽንኩርት መመገብ ካልቻሉ ለ1ዐ ደቂቃ ያህል በጥንቃቄ ቀቅለው መመገብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሌላው ጥሬ ዝንጅብል አብሮ መብላት፣ ወይም የዝንጅብል ሻይ አብሮ መጠጣት ይረዳቸዋል፡፡ ዝንጅብል የምንጊዜም የቀይ ሽንኩርት አጃቢ፡፡

ዝንጅብል

ለ/ የአፍ ሽታ

ጥሬ ቀይ ሽንኩርት ማዘውተር ወይም ከተመገቡ በኋላ የአፍ ሽታን ሊለውጥ ይችላል፡፡ ይህን በአግባብ አፍን እና ጥርስን ማጽዳት፣ ሽታን የሚከላከሉ እንደ ቀረፋ፣ ቡና፣ ጤና አዳም እንጨት ያሉትን ማኘክ፡፡

2/ ቀይ ሽንኩርት በቤተሰብ አስቤዛ ውስጥ

በአንድ ቤተሰብ የወር አስቤዛ ከጠቅላላው አትክልት ጋር ሲወዳደር ከፍተኛው የድርሻ መጠን ቀይ ሽንኩርት ነው፡፡ ቤተሰቦች ቀይ ሽንኩርትን በብዛት ቢገዙም ጥቂት እንኳን ጥሬውን አይመገቡም፡፡ እንደሚገዛው ቀይ ሽንኩርት መጠን፣  ለጤና ጠቃሚ በሆነ መንገድ ተመግበውት ቢሆን ኖሮ ብዙ በሽታን ይሰብሩት በነበር፡፡ በቤተሰቡ የስኳር ታማሚ፣ የደም ግፊት፣ የሳል፣ የአስም  ወዘተ ታማሚ ቢኖር ከተገዛው ቀይ ሽንኩርት ላይ ተቀንሶ የተለየ ምግብ አይሠራለትም፡፡ ያው የተለመደው አሠራር ብቻ ነው፡፡

የተለመደው ባልትና

በብዙ ቤት የተለመደው የቀይ ሽንኩርት አሠራር ሽንኩርቱ ለረዥም ሰዓት  ከዘይት እና ከበርበሬ ጋር ሲቁላላ ቆይቶ ሲያበቃ ሌሎች ነገሮች ተጨማምረው ለምግብነት ይቀርባል፡፡  አብዛኛው ዘይት ጥራቱን ያልጠበቀ በከፍተኛ ሙቀት የተመረተ ነው፡፡ ይህም ሆኖ እንደገና በሌላ ከፍተኛ ሙቀት መጎዳት አይኖርበትም ነበር፡፡  ስለ ዘይት ተጨማሪ ነገረ ጉዳይ በዚሁ ዓምድ ላይ  “ዘይት ለምን እንዴት?” በሚል ርዕስ በዚህ ሊንክ ላይ አንብቡ፡፡ https://ethio-online.com/archives/5914

የአገራችን በርበሬ ከእርሻው ማሳ ላይ ተሰብስቦ እንዲደርቅ በመሬት ላይ ሲሰጣ ብልሽት ይጀምረዋል፡፡ ቀጥሎም ብዙ ጉዳት ላይ የሚጥል ገጠመኞች አሉት፡፡ እናም በመጨረሻም ከቀይ ሽንኩርት እና ዘይት ጋር በድስት ውስጥ በከፍተኛ ሙቀት እየተማታ ይሰናዳል፡፡ ስለ በርበሬ ሐተታ “በርበሬአችን እና የአፍላቶክሲን ችግሮች” በሚል ርዕስ  በዚህ ላይ ተመልከቱ፡፡ https://ethio-online.com/archives/2483

አሁን እንደዚህ ቀይ ሽንኩርት፣ ዘይት እና በርበሬ በከፍተኛ ሙቀት ቀብጦ ሲዘጋጅ እነሆኝ እንደዚህ ውብ ነው፡፡ አትለፉኝ ይላል፡፡

የቀይ ወጥ ናሙና

እህሳ፣ አሁን ይህን ወጥ ሲመገቡት የቃና ጥግ ነው ይጥማል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ውስጥ የገባው ቀይ ሽንኩርት ቢመገቡት ምንም ጠቀሜታ የለውም፡፡ ጠቀሜታ ማጣቱ ብቻም ሳይሆን ከዘይት እና በርበሬ ጋር ተበሳስሎ ለጊዜው ምቾት ይነሳል፡፡ በዘመናት ብዛት ደግሞ የሚያስከትለው አይታወቅም፡፡

3/ የቀይ ሽንኩርት ምርት እና ግሽበት

የቀይ ሽንኩርት ምርት በአገሪቱ ብዙ ተደክሞበታል፡፡ ብዙ የእርሻ ማሳ ላይ በተለይም በመስኖ በብዛት ይታረሳል፡፡ ለምርምር እና ለስረፀት ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል፡፡ ብዙ ማሳ የሽንኩርት ምርት አፍርቷል፡፡ ማጣቀሻ ሁለት፤

ብዙ ሴቶች፣ ወጣቶች በእርሻ ማሳ ላይ ብዙ ላብ አፍሰዋል፤ በብዙ ለፍተዋል፡፡ ደላሎች በጥሩ አገበያየተዋልም፣ በሌሎችም ላብ ብዙ አትርፈዋል፡፡ በአትክልት ገበያ የቀይ ሽንኩርት ምርት በመኪና እየተጫነ ቀርቦ ተራግፎአል፡፡ በብዙ ገበያ ቦታ፣ በየሱፐር ማርኬቱ፣ በየሱቁ፣ በየመንደሩ ቀይ ሽንኩርት ተኮልኩሎ ተመጥኖ ይሸጣል፡፡

አምራቹ ለመሬት ዝግጅቱ፣ ለዘሩ፣ ለአዝመራው፣ ለገበያው  ወዘተ “ብዙ ደክሞበታል” ቢባል አይገልፀውም፡፡

በሽንኩርት እርሻ በለስ እየቀናቸው፣ ብዙዎች በብዙ አትርፈዋል፡፡ አንድ ሚሊዮን ብር አውጥተው ሶስት ሚሊዩን አግኝተው ይሆናል፡፡ ከዚህ በላይ አውጥተው በዚሁ ልክ ብዙ አትርፈዋል፡፡

ይህም  ቢባል እንኳን፣ አሁንም በለስ እየከዳቸው፣ ብዙዎች ብዙ ከስረዋል፣ ቤታቸው እና  ኑሮአቸው ተናግቷል፡፡ ከግምት በላይ በሆነ ኪሳራ የተነሳ እራሳቸውን ስተው ለእብደት ተዳርገዋል፡፡ ቤታቸውን ጥለው ጠፍተዋል፡፡ ሕይወታቸውን  በገዛ እጃቸው ያጠፉትን ቤት ይቁጠረው፡፡ ስንቶች ልጆች ያለ አባት ቀርተዋል፣ ተንከራተዋል፣ በጉስቁልና አድገዋል፡፡

ሽንኩርቱ ትርፍ ይገኝበታል በሚል ግምት አንጡራ ሀብታቸውን አሟጠው፣ በከፍተኛ ብድር ወይም በከፍተኛ ሌላ የዕዳ ጫና ውስጥ ገብተው መሬት ተኮናትረው ማምረት ይጀምራሉ፡፡ ወጪ ከመሬት ኪራይ ይጀምርና፣ ደጋግሞ ማሳረስ፣ ዘር፣  ማዳበሪያ፣ የሰው ጉልበት፣ ፀረ አረም፣ ፀረ ተባይ፣ ወዘተ እያለ ይቀጥልና፣ ምርቱ ደርሶ ገበያ ይፈለጋል፡፡

በዚያን ወቅት የገበያው ዋጋ ቀድሞ ከተገመተው በታች ይሆን እና ሽንኩርቱ የወጣበትን ጠቅላላ ዋጋ ቀርቶ፣ በእለቱ ለነቃይ፣ በጆንያ ለሚሞሉት፣ ለሚጭኑት፣ የመኪና ኪራይ ወዘተ የሚከፈል ዋጋ መሸፈን ያቅተዋል፡፡ ያኔ ማሳዎች በሙሉ፣ ገበያው በሙሉ ሽንኩርት በሽንኩርት ሆኗል ማለት ነው፡፡ ያኔ ተመጋቢው አንዱን ኪሎ በ 5 ብር ይገዛል ማለት ነው፡፡

በምሳሌ ለማስረዳት በአንድ ማሳ ላይ አንድ አምራች ምርቱ እስከሚደርስ ድርስ  አንድ ሚለዮን ብር አወጣ እንበል፡፡ ገና ሌላም ወጪ ይጠበቅበታል፣ ማስነቀያ፣ መቁረጫ እና በጆንያ ማስሞላት፣ የደላላ፣ የማስጫኛ ወዘተ ሁለት መቶ ሺ ብር ያስፈልገዋል፡፡ ይህም ሆኖ ሽንኩርቱ ሲሸጥ መቶ አምሳ ሺ ብር በላይ አያወጣ ይሆናል፡፡ በዚህ ደረጃ እንግዲህ ቢያንስ ሌላ ኪሳራ ከሚደርስበት ሽንኩርቱን ዓይኑ እያየ መሬት ላይ መተውን ይመርጣል፡፡ አምራቹ ከሰረ፣ መሬቱም ከሰረ፡፡

የሽንኩርት አዝመራ ጉዳ-ጉድ የትየሌለ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ማጥናት የፈለገ ይበርታ፡፡ ለዛሬው ግን በዚች አጭር ጽሑፍ ማመልከት የተፈለገው፣

 • ምነው? በሌላው የዓለም አገራት ሞልቶ ተሻሽሎ የሚገኘው የቀይ ሽንኩርት ምርት መሰብሰቢያ ዘዴ፣ የቀይ ሽንኩርት ማቆያ መሣሪያ እና ዘዴ፣ የማድረቂያ መሳሪያ እና ዘዴ፣ የማሸጊያ መሳሪያ ወዘተ ወደ እኛ አገር የማይመጣው?
 • ምነው? መረጃው ቀድሞ ተነግሮ የምርቱ መጠን ገደብ ቢበጀለት፡፡ እና
 • የሚመለከተው የግብርና ሚኒስቴር ይህን ችግር አጥኑ እና የመፍትሔ ሓሳብ አቅርቡልኝ ቢል ምንነበር?
 • ሌሎቹስ ስለ እርሻ እና ምግብ ነገረ ጉዳይ ላይ እሠራለሁ የሚሉቱ የት ናቸው?

ማጠቃለያው

ለቀይ ሽንኩርት ምርት በአገሪቱ ውስጥ በቂ የቴክኖሎጂ እና የገበያ ዝግጅት አልተደረገም፡፡ ሲቀጥል ቀይ ሽንኩር በቁሌት የሞተ እንጅ ያልተበላ ጥሬ ሀብት ሆነ፡፡ ለምርቱ ብክነትም ሆነ ለስነምግቡ ብክነት ሁሉም የድርሻውን ይወጣ፡፡ ምክክር እና ትምህርት በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ቤተሰቦችም እባካችሁ ስለ አበሳሰሉ የራሳችሁን ትኩረት አድርጉ፡፡ ቀይ ሽንኩርት ለጤና ያለውን ዋጋ አስተውሉ፡፡

                                                     

ማጣቀሻ አንድ፤  JEAN CARPER, 2000, FOOD YOUR MIRACLE MEDECINE, HOW FOOD CAN

PREVENT AND TREAT OVER 100 SYMPTOMS AND PROBLEMS, Pocket books, Great Britain

ማጣቀሻ ሁለት፤ January 2018 Onion (Allium cepa L.) Yield Improvement Progress in Ethiopia: Review   https://www.researchgate.net/publication/322742624_Onion_Allium_cepa_L_Yield_Improvement_Progress_in_Ethiopia_Review

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com