ማሾ ትንሽዋ አረንጓዴ ወርቅ

Views: 1010

መነሻ

ስሟ በእንግሊዘኛ መንግ ቢን (Mung bean) ሲሆን፣ በአማርኛ ማሾ ነው፡፡ አገሪቱ “የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል ”  እንደሚባለው ማሾን ወደ ውጪ ትልካለች፤ ምስር ደግሞ ወደ አገር ውስጥ ታስገባለች፡፡ ይህን ምን ይሉታል? ማጣቀሻ አንድ

ከጥራጥሬ ወገን የሆነችው ማሾ ጥሩ የፕሮቲን መገኛ ናት፡፡ በአገራችን ልዩ የሚያደርጋት ድርቅን ተቋቋሚነቷ፣ በተዘራች በሁለት ወር መድረሷ እና ወደ ውጪ የምትሸጥ ባለዋጋ ሰብል መሆኗ ነው፡፡

በብዙ የዓለም አገራት ትለማለች፡፡ ህንድ ዋና መነሻ አገሯ ስትሆን፤ በዚህ ዘመን ከህንድ ሌላ በባንግላዲሽ፣ ፓኪስታን፣ ሲሪላንካ፣ ታይላንድ፣ ላኦስ፣ ካምፖዲያ፣ ቬትናም፣ ኢንዶኔዥያ፣ ማሌዥያ፣ ቻይና፣ በአፍሪካ አገራት እና በአሜሪካ ትመረታለች፡፡

በኢትዮጵያም ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ቤንሻጉል ክልሎች ትመረታለች፡፡ በተለይም ቀደም ሲል በብዛት ደቡብ ወሎ ውስጥ እና በቅርቡ ደግሞ ሰሜን ሸዋ አሳግርት እና መርሃቤቴ በብዛት ትመረታለች፡፡

የማሾ ዋና ዋና ጥቅሞች

 • ማሾ በቆላ ምድር በቀላል የእርሻ ሥራ ምርት ይገኝባታል፣
 • በውጪ ገበያ ተፈላጊ ስለሆነች፣የውጪ ምንዛሬ ታስገኛለች፣
 • መሬትን የማከር ከፍተኛ ብቃት ስላላት የአፈር ለምነትን ትጠብቃለች፣
 • በአጭር ቀናት (በ 6ዐ ቀናት) ትመረታለች፣
 • በቆላ ምድር ትለማለች፣ ድርቅን ትቋቋማለች፣
 • በፕሮቲን፣ ማዕድናት እና ቫይታሚን የበለፀገች ናት፣
 • ለወጥ እንደሌላው ጥራጥሬ ታገለግላለች፡፡

በሙሉ አቅም አልታረሰም

አገሪቱ ማሾን በብዙ መጠን ማምረት እና ለውጪ እና ለአገር ውስጥ ገበያ በሽበሽ ማድረግ ትችል ነበር፡፡ የሆነው ግን በአነስተኛ መጠን ይመረታል፤ ያቺ ተሰብስባ ለውጪ ገበያ ትሸጣለች፡፡ በአገሪቱ ከተሞች በስፋት ገበያ ላይ የለችም፡፡ ህዝቡ ምን ዓይነት ጣዕም እንዳላት እንኳን አላያትም፡፡

ማሾ በአርሶ አደሩ ዘንድ

ማሾ በከፍተኛ መጠን በምትመረትበት አካባቢ ለምግብነት አይጠቀሙም፡፡ ሆን ተብሎ ወይም ባለማወቅ “ማሾ የሳሙና ጥሬ ዕቃ ናት” የሚል ግንዛቤ በማህበረሰቡ ውስጥ ስለሰረፀ አይመገቡትም፡፡ ይህ እርማት ያስፈልግል፡፡ ማሾ ጥሩ ምግብ ስለሆነች ነው ወደ ውጪ የምትሸጠው፡፡ በብዙ አገራት በተለያየ ሙያ ተሠርታ ለምግብነት ትውላለች፡፡ ምናልባት ወደ ውጪ ገበያ ለመሸጥ የምርት መጠን ይቀንሳል በሚል ሥጋት ከሆነ በዓመት ውስጥ እስከ 4 ጊዜ በተለያየ ማሳ ላይ መዝራት ይችላሉ፡፡

እንዴት መመገብ ይቻላል?

ማሾ በተመረተችበት ዓመት ከላይ ምስል ላይ እንዳለችው በጣም አረንጓዴ መልክ አላት፤ እስከ 3 ዓመት በቆየት ትችላለች፡፡ ብዙ ዓመት ስትቆይ ከፊሉ እህል ቀላ ይላል፡፡ ከታች በምስሉ ያለችው ሁለት ዓመት የከረመች ናት፡፡

ጥሬ ማሾ

ሀ/ እንደ አተር ወይም አደንጓሬ ለሽሮ፣ ለወጥ፣ ለንፍሮ እና ለመሳሰሉት መጠቀም ይቻላል፣

ለ/ ምስርን ተክታ እንደ ምስር ክክ፣ እንደ አዚፋ ወዘተ መሆን ትችላለች፣

ሐ/ በስንዴ ላይ ቀይጦ (ስንዴ 7 እጅ እና ማሾ 3 እጅ መጥኖ) በማስፈጭት ዳቦ ለመጋገር ትውላለች፤

መ/ በጥሬም ሆነ የጎነቆለችው ከተቀቀለች በኋላ ከማንኛውም አትክልት ጋር ተሠርታ ልትቀርብ ትችላለች፤

በግራ ጥሬ ማሾ እና በቀኝ የጎነቆለ ማሾ

 ሠ/ በማጎንቆል ማሰዳት

የጎነቆለች ማሾ

ለማጎንቆል ጥቂት ቀናት ያስፈልጋል

 • አበጥሮ፣ ለቅሞ፣ አጥቦ፣ በውሃ ነክሮ ማሳደር፣ጠዋት እንደገና ውሃውን መቀየር
 • በውሃ ውስጥ አንድ ቀን ተኩል ከቆየች በኋላ ማጥለል እና አስሮ ማቆየት፣
 • በታሠረችበት ጨርቅ ላይ በትንሹ ውሃ መርጨት፣
 • በሚቀጥለው ቀን ከላይ እንዳለው ትሆናለች፤
 • ካስፈለገ ብቅለቱን ከዚህ የበለጠ ማሳደግ ይቻላል፡፡
 •  

ብቅለቱ ካደገ በኋላ በሰላጣ መልክ ወይም በመቀቀል አብስሎ አዘጋጅቶ መጠቀም ይቻላል፡፡

ከፍተኛ ጤናማ ንጥረ ምግብ ይዛለች

ኸልዝላይን ማሾ የሚከሉትን እና ሌሎችም የጤና በረከት አላት ይላል፡፡  ማጣቀሻ ሁለት

1/ ካሎሪ፣ ፕሮቲን፣ አሠር፣ ማዕድናት (ማንጋኒስ፣ማግኒስየም፣ፎስፈረስ፣ አየረን፣ፖታስየም፣ ዚንክ ወዘተ) ቫይታሚን (ቫይታሚን ቢ1፣ ቢ2፣ቢ5፣ቢ6) እና ሌሎችም

2/ አንቲኦክስደንት ስለያዘች ስር የሰደደ በሽታን አደጋ ትቀንሳለች፣

3/ በውስጧ የያዘችው የአንቲኦክሲደንት ዓይነት ለልብ ጤና ይረዳል፣

4 /አደገኛ ኮልስትሮልን በመቀነስ የልብ ሕመምን አደጋ ትቀንሳለች

5 /በፖታስየም፣ ማግኒዝየም እና አሰር የዳበረች ስለሆነ የደም ግፊትን ትቀንሳለች

6 /በያዘችው ሟሚ አሠር እና ተስማሚ እስታርች የተነሳ ለምግብ ስልቀጣ ትረዳለች

7 /ስኳር ወደ ደምዥረት በቀስታ እንደለቀቅ በማድረግ የደም ስኳርን እንዲስተካከል ትረዳለች

ማጠቃለያ

ይቺን ትንሽዋን አረንጓዴ ወርቅ ማሾን በብዙ ቆላ ምድር በሰፊው መዝራት እና ለውጪ ገበያ በብዛት ማቅረብ ጥቅም ያስገኛል፡፡ በሌላም በኩል በዚህ ዘመን የምስር እጥረት በመድረሱ ምስርን ተክታ ለአገር ውስጥ ገበያ ተፈላጊ ልትሆን ትችላለች፡፡ እጅግ የሚገርመው ማሾን ያጣጣመ ሰው መልሶ ሌላ ምስር አይመርጥም፡፡ ጥፍጥና ማሾ ትበልጣለች፣ ለጤናም ይበልጥ ትስማማለች፡፡

                                                                             

ማጣቀሻ አንድ    http://www.ethiopianimporter.com/ethiopia-export-data/mung-bean.html#

ማጣቀሻ ሁለት    https://www.healthline.com/nutrition/mung-beans#section8

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com