ዜና

የስኳር በሽታን ውስብስብ ችግር ተከላከሉ!

Views: 1293

መነሻ

በእንግሊዘኛ አጠራሩ ዲያቤትስ መሊተስ (Diabetes mellitus) ይባላል፡፡ በአማርኛ የስኳር በሽታ ተብሎ ይታወቃል፡፡ ነገረ ጉዳዩ ሰውነት ግሉኮስን ማስተካከል አቅቶት ወይም አስተካክሎ መጠቀም ተስኖት መረበሽ ሲከሰት ነው፡፡ ግሉኮስን ሴሎች እንደ ነዳጅ ተጠቅመውት ኃይል እና ኢንሱሊን ያመነጩበታል፡፡

መኪና ለማሽከርከር ነዳጅ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፤ የሰው አካልም ለመሥራት፣ ለመጫወት በጠቅላላው ለመንቀሳቀስ የኃይል ምንጭ ወይም ስኳር (በሌላ አጠራር ግሉኮስ) ያስፈልገዋል፡፡ የስኳር በሽታ ምክንያቱ በቂ ኢንሱሊን በጣፊያ ያለመመረት፣ ምንም ያለመመረት ወይም የተመረተው ኢንሱሊን በአግባብ ሠራ ላይ አለመዋል፤ መሆኑ ቢታወቅም ትክክለኛ መንስዔው፣ በብዙ ሳይንቲስቶች ብዙ መላ ምት ይነገራሉ፡፡

የሆነው ሆኖ፣ የበሽታው ስሜቶች እና ምልክቶች በአንድነት ለበሽታው መከሰት መረጃ ይሰጣሉ፡፡ እነዚህም፣

 • ከፍተኛ የውሃ ጥም፣ ውሃ በብዛት መጠጣት እና ከመጠን በላይ መሽናት፣
 • ከፍተኛ የረሀብ ስሜት እና ምግብ በብዛት መብላት፣
 • የክብደት ማሽቆልቆል እና በቀላሉ መድከም፣
 • የዕይታ መቀነስ እና በቀላሉ በኢንፌክሽን በተለይም በቆዳ ኢንፌክሽን መጠቃት እና የሰውነት ማሳከክ ናቸው፡፡ ማጣቀሻ አንድ

የስኳር በሽታ ሁለት ዋና መደብ አሉት፡፡ ዓይነት አንድ እና ዓይነት ሁለት፡፡ በተለምዶ በብዙ አገራት እስከ 8ዐ ከመቶ የሚከሰተው ዓይነት ሁለት እና በአነስተኛ መጠን የሚከሰተው ዓይነት አንድ ነው፡፡ ሆኖም ዶ/ር ሽታዬ አለሙ የ26 ዓመታት የስኳር ህመም ጥናት በጎንደር ዩኒቨርስቲ አድርገው አይነት አንድ የተሰኘው የስኳር በሽታ ዓይነት ባልተለመደ መልኩ በገጠር ነዋሪዎች ላይ ከፍ ብሎ እንደሚታይ አመላክተዋል፡፡ የዚህን ሰፊ ዘገባ “በስኳር ህመም ላይ የሚደረገው ምርምር”  በሚል ርዕስ 15.05.2019 እ.ኤ.አ  https://www.dw.com  የቀረበውን አንብቡ፡፡

በእዚህ በአሁኑ ጽሑፍ ላይ ትኩረት የተደረገው በተለይ ለዓይነት ሁለት የስኳር በሽታ ነው፡፡

ዓይነት ሁለት የስኳር በሽታው እንደጀመረ ጥቃቱን በመከላከል፣ የተለያዩ የተፈጥሮ መድኃኒት በመውሰድ፣ ምግብን በማስተካከል በሽታውን ማስታገስ እንደሚቻል ብዙዎች የባሕል ሐኪሞች እና በሌላም አገራት የሚገኙ የዕፀ መድኃኒት ተመራማሪዎች እና አቀንቃኞች ይሞግታሉ፡፡ (ይህን ሰፊ ጉዳይ በብዙ መረጃ መረብ እና መጽሐፍት አንብቡት፡፡)

በማንኛውም መንገድ ቢገለጽ የስኳር በሽታ ውስብስብ ጉዳት የሚያስከትል ጠንቀኛ በሽታ ነው፡፡ ህመሙ ብቻም ሳይሆን፣ ለህመሙ ማስታገሻ ወይም መቆጣጠሪያ የሚሰጡ መድኃኒቶች ሌሎች ተከታይ የበሽታ ጫና እና አደጋ በኩላሊት፣ በዓይን፣ በጥርስ፣ በልብ ላይ እና በሌሎችም ላይ ያስከትላሉ፡፡ ለምሳሌ የኩላሊት ከሥራ ውጪ (ድክመት) መድረስ፣ የዓይን ዕይታ መዳከም፣ የጥርስ ተሰባብሮ ማለቅ፣ የልብ ሥራ መጓደል፣ የደም ዝውውር መጓደል እና ለደም ግፊት መጋለጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ደግነቱ ይህ ሁሉ ጥቃት በአንድ ሰው ላይ በአንድ ጊዜ አይከሰትም፡፡ እንደየሰው የተለያየ ጉዳት በጊዜ ብዛት ይከሰታል፡፡

አሁን በዚህ ጽሑፍ ላይ ለመንገር የፈለግነው ከመደበኛው መድኃኒት ጎን ለጎን ተፈጥሮአዊ የሆኑ ጉዳቱን ለመከላከል ወይም ለመመከት የሚረዱ ዘዴዎችን ለመጠቆም ነው፡፡ ይህን ተጨማሪ ዘዴ መጠቀም ትርፉ ምንድነው? ቢባል፣

 • ቢቻል በሽታውን እንደጀመረ ሰሞን ሥር ሳይሰድ ለማስቀረት፣
 • የሚወሰደውን ዘመናዊ መድኃኒት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለመቀነስ ወይም፣
 • በሽታው እና ዘመናዊ መድኃኒቱ የሚያመጣውን የጎንዮሽ ጉዳት ለማስቀረት ወይም ለማዘግየት ነው፡፡

ልብ በሉ፣ የተነገሩ ምግቦች ወይም መጠጦችን ስትወስዱ አለርጂ (የሰውነት መቆጣት) የሚያስከትሉትን እና ለአመጋገብ በደም ዓይነት የተመረጡ እና የተከለከሉትን ለዩ፡፡

የስኳር በሽታን በምግብ እና መጠጠጥ መከላከል

ሀ/ ተመራጭ ምግቦች

 • ጤፍን በእንጀራም ሆነ በተለያየ መንገድ መመገብ የደም ስኳርን ለመቆጣጠር ይረዳል፡፡ አሜሪካ ውስጥ በጤፍ ላይ እጅግ ርብርብ የሚያደርጉት ጤፍ በብዙ ልክ፣ የጤና በረከት ስለሆነ ነው፡፡
 • ኦትስ (የፈረንጅ አጃ) ቢቻል አገር ውስጥ የተመረቱት፣

አኩሪ አተር በወተት እና በተለያየ አሠራር ተዘጋጅቶ፣

አኩር አተር ከታጠበ በኋላ

 • ገብስ (ቆሎ፣ ቅንጨ፣ዳቦ፣ ብስኩት፣ በሶ ወዘተ)
 • የግብጦ ቆሎ፣
 • ሽምብራ፣ ባቄላ፣ ምስር፣
 • አንገተ ረዥም ሚሌት፣ በሌላ አጠራር ዱከሃም፣ ጥሩ እንጀራ ወይም ዳቦ ይሆናል፡
 • ኪኑዋ (ኪኙዋ) መመገብ በዚህ ሊንክ ላይ አንብቡ፡  https://ethio-online.com/archives/6116
 • አማራንስ (አሉማ) ዘር፣ ለዳቦ፣ ለእንጀራ ይሆናል፣

አማራንስ የተክሉ ምስል

ለ/ ሬይ ለስኳር ታማሚ ተመራጭ ዳቦ

የምግብ ዓይነት የበሽታውን ጫና ይመክታል ካልን የሬይ (ጆሎንጌ) ዳቦ ከሁሉም ተመራጭ ነው፡፡ ሬይ በአገራችን በጭላሎ ጋለማ ሠንሠለታማ ተራሮች በምዕራቡ ግርጌ በጥቂቱ በአነስተኛ እርሻ ይታረሳል፡፡ ስለ ሬይ ይበልጥ በዚሁ መረጃ መረብ ላይ አንብቡ፡፡

የጆሎንጌ ጤና ዳቦ https://ethio-online.com/archives/2066    

ከሬይ እህል የሚጋገር ዳቦ፣ ብዙ የጤና ጥቅሞች አሉት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ያጠግባል፣ ለምግብ ስልቀጣ ሥርዓት ይረዳል፣ ለረዥም ጊዜ ጉልበት ይሰጣል፣ ቫይታሚኖች አሉት፣ ማዕድናት አሉት፣ የትልቁ አንጀት እና በጡት ነቀርሳ የመያዝን አደጋ ይቀንሳል፡፡ ሙሉ እህሉ ሬይ በዳቦ ወይም በማንኛውም ዓይነት ምግብ ተዘጋጅቶ ለቅድመ ስኳር እና ለስኳር ታማሚዎች በእጅጉ ይረዳል፡፡ በዚህ ላይ ይበልጥ አንብቡ፡፡ (https://www.berman.co.il/en/virtue-rye-bread-pre-diabetic-diabetic-patient/ )

በዓለም ላይ እጅግ ዝቅተኛ የስኳር ታማሚ ካሉባቸው አገራት ኢስቶኒያ እና ሉቲንያ ይገኙበታል፡፡ ሁለቱም አገራት ከሚመገቡት ዋና የዳቦ ዓይነት የሬይ (የጆሎንጌ) ዳቦ አንዱ እና ዋናው መሆኑ አንድ እውነት ይነግረናል፡፡ ለማረጋገጥ በዚህ (https://en.wikipedia.org/wiki/Estonian_cuisine እና  (https://trip101.com/article/traditional-food-in-lithuania)  ላይ አንብቡ፡፡

ሐ. ለስኳር በሽታ ከህዝብ እውቀት (ከሕክምና በቤታችን ላይ የተወሰደ)   ማጣቀሻ ሁለት          

 • በየ 2 ወራት የአበሻ ኮሶ መጠጣት፣ የአበሻ ኮሶ ዛፍ ሴቴ አበባው በኅዳር ወር ይሰበሰባል፣ ደርቆ፣ ይፈጫል፣ ዱቄቱ አንድ ሾርባ ማንኪያ በውሃ ተቦክቶ አንድ ቀን ተኩል ቆይቶ ቀጠን ተደርጎ ይጠጣል፡፡ (ብዙ ጊዜ ያስቀምጣል፣ ጥንቃቄ ማድረግ ነው)
 • አዘውትሮ የአብሽ ዱቄት በውሃ ላይ ነስንሶ አሳድሮ ማለዳ መምታት እና ያለ ስኳር መጠጣት፣
 • የእንቧጮ ቅጠል እንደሻይ እያፈሉ ያለ ስኳር አዘውትሮ መጠጣት፣ (ዛፍ በሌለበት እንቧጮም አድባር ነው፣ ይሉት ተረት አለ፡፡) ይህ ዱር በቀል ተክል በቀደመው ዘመን በአረብ አገራት እጅግ ፍቱን የስኳር በሽታ መድኃኒት ነበር፡፡ አኛም አገር የሚጠቀሙት አሉ፡፡
 • ለጉበት እና ለኩላሊት ጤና የሚረዱ ነገሮች ለስኳር በሽታ ጭምር ሊረዱ ይችላሉ፡፡ እንደ መቅመቆ፣ ነጭ ኮሸሽላ ያሉ ተክሎች፡፡

መ. ለስኳር በሽታ ከዕፀ ደብዳቤ መጽሐፍ ላይ የተወሰደ   ማጣቀሻ ሶስት

 • መተሬ ፍሬው ተወቅጦ ተበጥብጦ ይጠጣል፡፡
 • የቆላ እንጆሪ ቅጠል እንደ ሻይ ተፈልቶ ይጠጣል፡፡
 • የጥንጁት ቅጠል ለስኳር እና ሀሞት ለሚበዛበት የሚጠጣ፣

የቆላም ሆነ የደጋ ቀጠጥና (Common mullein, Verbascum sinaiticum) ሌላው ስሙ (የአህያ ጆሮ) ቅጠላቸው ወይም ሥሩ ተጨፍጭፎ ለስኳር እና ለጉበት በሽታ የሚጠጣ፣

ዱር በቀል ቀጠጥና

 • የእሬት ክንፍ ውሀ ለደም ብዛት እና ለስኳር በሽታ ያገለግላል፡፡
 • ወርቅ በሜዳ ( Coccinia sp. )ሥሩ ደርቆና ተፈጭቶ ለስኳር በሽታ እንደሚያድን የታወቀ ነው፡፡
 • የሎሚ እሸት (Satureja sp.)  ቅጠሉ እንደሻይ ተፈልቶ ሲጠጣ ለስኳር በሽታ ይሆናል፡፡

ሠ. ለስኳር በሽታ የተመረጡ አትክልቶች   

 • ራዲሽ በሠላጣ መልክ መመገብ ወይም ቅጠሉን ጨምቆ መጠጣት፣
 • ቻዮቴን በጥሬው በሰላጣ መልክ ወይም እንደ ድንች ቀቅሎ አብስሎ መመገብ፡

ቻዮቴ ፍሬው

 • ተርኒፕ ቅጠሉ ወይም ሥሩን በመቀቀል ወይም በሠላጣ መልክ መመገብ፣
 • ብሮኮሊ፣ አበባ ጎመን፣ አብስሎ መመገብ፣

ብሮኮሊ

 • ፋሶሊያ (አደንጓሬ ዝንቡጥ)፣ ሰላጣ፣ ሰለሪ፣
 • ካሮት እና ቀይ ሥር፣ በጥሬው በሠላጣ ዓይነት ተሠርቶ፡፡

ቻያ ጎመን፣ አብስሎ መመገብ፣

ቻያ ጎመን፣

 • ታማሪሎ ፍራፍሬ፣ (የቲማቲም ዛፍ) ተቀቅሎ የውስጡ ፍሬ ወጥቶ በጁስ መልክ መውሰድ በጣም ይረዳል፡፡

ታማሪሎ

ረ. ለስኳር በሽታ የተመረጡ ፍራፍሬዎች   

 • የቁልቋል በለስ (አሾካ ) ጁስ ተመጥኖ እጅግ ተስማሚ ነው፡፡

https://ethio-online.com/archives/4036

 • አፕል፣ አቮዶ፣ ሙዝ፣ በኩረ ሎሚ፣ ኮክ፣ብርቱካን፣ እና የመሳሰሉትን፣
 • ወይን ፍራፍሬ ወይም ዘቢብ (ደረቅ የወይን ፍሬ)

ወይን ፍራፍሬ

ሰ. ለስኳር በሽታ መጠጥ

     ከንፁህ ውሃ በተጨማሪ እነዚህ ጠቃሚ መጠጥ ናቸው፡፡

 • የአኩር አተር ወተት
 • አረንጓዴ ሻይ
 • የዕፀዋት ሻይ (የሳማ፣ መቅመቆ፣ ከርከዴ ወዘተ) በዚሁ አምድ ላይ

ይበልጥ ተመልከቱ ሻይ ለጤና ክፍል አንድ   https://ethio-online.com/archives/4769  እና  የሎሚ ሣር የጤና ሻይ https://ethio-online.com/archives/6591

 • በቤት ውስጥ በአግባብ ተፈልቶ ቀዝቅዞ፣ የረጋ የላም ወተት፣ ስኳር የሌለው፡

ሸ. ለስኳር በሽታ የሚከለከሉ ምግቦች እና መጠጥ

 • ስኳር እና በስኳር የተዘጋጁ ምግብ እና መጠጦች ሁሉ፣
 • ከስንዴ እና ከሩዝ የተሠሩ ፓስታ፣ መኮረኒ፣ ኬክ፣ ብስኩት ወዘተርፈ፣
 • ትራንስ ፋትስ የሚባሉ ስብ ምግቦች፣ በተለይም በኬሚካላዊ ቅንብር የተለወጡ፣ ለማቆየት እና ተረጋግተው እንዲቆዩ ተብለው እጅግ የሚቀናበሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ማርጋሬን፣ ክሬሞች፣ እና ሌሎችም ሲሆኑ ኢንሱሊን እንዳይሰርግ በማገድ፣ የሆድ ላይ የስብ ክምችት ማብዛት እና የልብ ጤና ቀውስ ያስከትላሉ፡፡
 • በአትክልት ቃና የጣሙ ዩጎርት፣ ስቡ ዝቅተኛ ቢሆንም ብዙ ስኳር አለው፡ ይህ ለከፍተኛ የደም ስኳር እና የኢንሱሊን ብዛት ይዳርጋል፡፡
 • በፋብሪካ ማጣጣሚያ የተዘጋጁ የቡና መጠጦች፣
 • ለስኳር በሽታ ተብለው ያልተገለፁ በፋብሪካ የተዘጋጁ ማጣፈጫዎች እንደ አጌቫ ኔክተር (Agave nectar)፣ ማር፣ ማፕል ሲረፕ (Maple syrup) ያሉት ዓይነት፣
 • በፋብሪካ ተቀናብረው የታሸጉ ስናክ ምግቦች እና የጁስ መጠጦች፣
 • ድንች፣ ስኳር ድንች፣ በተለይም በዘይት ተጠብሰው የቀረቡትን መተው፡፡

መከልከል ስላለባቸው ነገሮች በሚከተለው ሊንክ ላይ ይበልጥ አንብቡ፡፡

https://www.healthline.com/nutrition/foods-to-avoid-with-diabetes#section13

ማጠቃለያ

የስኳር በሽታን እዚህ ላይ ከተገለፁትም በተጨማሪ እጅግ ብዙ የምግብ፣ የመጠጥ እና የዕፀ መድኃኒት አማራጮች አሉ፡፡ ታካሚው እራሱ እና ቤተሰቡ ለችግሩ መፍትሔ ትኩረት አድርገው በመረዳዳት የበሽታውን አስከፊ ገጽታ መመከት ይችላሉ፡፡ ዋናው ጉዳይ የበሽታውን አስከፊነት ተረድቶ በጊዜው አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ነው፡፡ በሌሎች አገራት ለዚሁ ተብለው የሚዘጋጁ የተፈጥሮ መድኃኒት በቀላሉ ገበያ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡ በእኛም አገር ብዙ የባሕል ሐኪሞች መድኃኒቱን በዘልማድ በባሕላዊ ዘዴ አዘጋጅተው ያቀርባሉ፡፡ ሆኖም የአመጋገብ መርሁን ሁሌም መከተል ያስፈልጋል፡፡

የስኳር በሽታን ውስብስብ ችግር ተከላከሉ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

                                               

ማጣቀሻ አንድ፡ ጫንያለው ካሳ፣ ትልቁ ሀብትዎ ጤንነትዎ፣ መሠረታዊ የጤና ግንዛቤ እና

የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ አሰጣጥ፣ አዲስ አበባ፡፡

ማጣቀሻ ሁለት፡ በቀለች ቶላ፣ 2ዐዐ9 ዓ.ም፣ ሕክምና በቤታችን፣ የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና በተፈጥሮ

መድኃኒት፣ 5ኛ እትም፣ አልፋ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፡፡

ጣቀሻ ሶስት ገላሁን አባተ፣ 1981 ዓ.ም ዕፀ ደብዳቤ፣ ከጥንት እስከ ዛሬ፣ ሥነ ሕይወት ክፍል

ሳይንስ ፋካልቲ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ፡፡

Comments: 1

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com