ዜና

የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ፀደቀ

Views: 2678

የኢፌድሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክር ዛሬ ታህሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ አመት የስራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ስብሰባ የጦች መሳሪያ አስተዳደር ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ በሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አዋጅ ቁጥር 1177/2012 በሚል አፅድቆታል።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ በውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከቀረበ በኋላ የምክር ቤቱ አባላት አስተያየትና ጥያቄ አቅርበው ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ በአብላጫ ድምፅ፣ በሁለት ተቃውሞና በአራት ድምፀ ተአቅቦ አዋጁ ሊፀድቅ ችሏል፡፡

አዋጁ ዓላማ ካደረጋቸው ጉዳዮች መካከል የሀገርና የህዝብን ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ግለሰቦችና ድርጅቶች ሀብትና ንብረታቸውን ለመጠበቅ የሚይዟቸውን መሳሪያዎች በህግና በስርዓት ማስተዳደር የሚሉት ዋነኛ ናቸው፡፡

ሆኖም፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ ጉዳት አድራሽ እቃ ተብለው የተጠቀሱት ገጀራ፣ ሜንጫ፣ ጦርና ቀስት የማህበረሰቡ የእለት ተእለት መገልገያና የባህል መገለጫ በመሆናቸው መካተታቸው ተገቢ አይደለም የሚል አስተያየት በአባላቱ መነሳቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ዘግቧል፡፡

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንዳሉት፣ ጉዳት አድራሽ እቃዎችን በተመለከተ፤ እቃዎቹ ለልማትና ለእርሻ ስራ ሲተገበሩ ሳይሆን ሰውን ለማጥቃት መጠቀም ተገቢ እንዳልሆነ ነው አዋጁ የሚደነግገው።

በዚህም፣ የጦር መሳሪያ ለመታጠቅ ፍቃድ የተሰጠው ሰው ፍቃድ ከተሰጠው ክልል ውጪ ባሉ የክልልና ትላልቅ ከተሞች የጦር መሳሪያውን ለህዝብ በሚታይ መልኩ ታጥቆ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑም በአዋጁ አንቀፅ 5/1 “ሸ” ተገልጿል።

የጦር መሳሪያ ሰዎች ንብረታቸውንና የአካባቢያቸውን ሰላምና ደህንነት የሚጠብቁበት በመሆኑም ፍቃድ ከተሰጠበት ክልል ውጪ ወደሌላ አካባቢ እንዳይጓዝ የተገለጸ ሲሆን፤ ውርስን በተመለከተም ማሻሻያ መደረጉንና በውርስ ህጉ መሰረት እንደሚሰራና ማንኛውም ህጉ የሚፈቅድለት ሰው መውረስ እንደሚችል ሰብሳቢው አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው አዋጁን ከማፅደቅ በተጨማሪ የፌዴራል ዳኝነት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅንና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com