ዜና

ገቢ እያደገ ነው!

Views: 308

ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ በወር ተገኘ

  • የኦንላይን ግብር ከፋዮች ብዛት 15 ሺህ ሊሆን ነው

የገቢዎች ሚኒስቴር በህዳር ወር 19.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከግብር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የህዝብ አጀንዳ እየሆኑ እና ግንዛቤው እየጨመረ በመምጣቱ፣ የገቢ አሰባበሰቡ ከመቼውም በተሻለ መልኩ እድገት እያሳየ መሆኑን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል፡፡

በዚሁ መሠረት በህዳር ወር 18.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 19.2 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 104 በመቶ ማሳካት ችሏል፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት አምስት ወራት እያስመዘገበ ያለው የገቢ አሰባሰብ ውጤት አበረታች እና ስኬታማ በመሆናቸው የዓመቱን እቅድ ለማሳካት ማሳያዎች ይሆናሉ ተብሏል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ 10 ሺህ የፌዴራል ግብር ከፋዮችን በተያዘው ወር  መጨረሻ ላይ ወደ ዘመናዊ የታክስ ሥርዓት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ግብር ከሚከፍሉ ግብር ከፋዮች መካከል  4 ሺህ 671 ግብር ከፋዮች ኦን ላይን ፋይል የሚያደርጉ ሲሆን፣ እነሱን ጨምሮ 10 ሺህ ግብር ከፋዮችን ወደ ዘመናዊ የታክስ ሥርዓት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡

ዘመናዊ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት የግብር ከፋዩን ጊዜ እና ወጪ ለመቆጠብ ያግዛል፣ ግብር ከፋዩም ይህንን አውቆ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ አገልግሎቱን እንዲጠቀም ጥሪ  አስተላልፈዋል፡፡

ይህ አሰራር ስኬታማ እንዲሆንም አመራሩ ድጋፍና ክትትሉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ማለታቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

እስከ ታህሳስ መጨረሻ 10 ሺህ የፌደራል ግብር ከፋዮችን ወደ ዘመናዊ የታክስ (e-filing) እና (e-payment) ሥርዓት ለማስገባት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም የኦንላይን ግብር ከፋዮች ብዛት 15 ሺህ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com