በቁፋሮ የተገኘች ጥንታዊት ከተማ፤ ቤተ ሰማዕቲ

Views: 919
  • የቤተክርስቲያን ሕንፃ መገኘቱን ተመራማሪዎቹ ይፋ አድርገዋል

ከሰሞኑ ከ1 ሺህ 4 መቶ ዓመታት በፊት የነበረች ጥንታዊት ከተማ በሰሜን ምሥራቅ አክሱም 30 ማይልስ ርቀት ላይ በቁፋሮ ማግኘታቸውን ዓለማቀፍ የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች አስታውቀዋል፡፡ ከተማዋ የጥንታዊ አክሱም ግዛት እንደነበችም ታውቋል፡፡ በቅድመ ሮም እንደነበረችም የምርምር ውጤቱ አመላክቷል፡፡

ከአክሱም ሥልጣኔ በፊትም ኢትዮጵያ ውስጥ ማንነታቸው በግልፅ የማይታወቅ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደነበሩ መዛግብት ይገልፃሉ፡፡ የእነኝህ የማሕበረሰብ ክፍሎችና የቅድመ አክሱም ሥልጣኔ ማሳያ ይሆናል የተባለው ግዛት መቀመጫ ከሰሀራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት መካከል የራሱ ጥንታዊ የአፃፃፍና የኪነ ሕንፃ ጥበብ የነበረው ሰሜናዊ የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሓ ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ ላይ እንደነበር መላ ምቶች ጠቁመዋል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ ነው ዓለማቀፍ የተመራማሪዎች ቡድን ጥናትና ቁፋሮ ማድረግ የጀመረው፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ ሜሪላንድ ግዛት የጆን ሆፕሊንስ ዩኒቨርሲቲ ምሁር የሆኑትና የጥናት ቡድኑ መሪ ሚካኤል ሃሮወር እንደገለፁት ቡድኑ በትግራይ ክልል በሚገኘው ሥፍራ ላይ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመነጋገር በአንድ መንደር የሚገኝ ከፍተኛ ቦታን ከልሎ ቁፋሮ የጀመረ ሲሆን፣ በውጤቱም የሕንፃ ፍርስራሽ ቅሪት የሆነ ድንጋይ አግኝቷል፡፡

በውስጡ በርካታ ትንንሽ ሕንፃዎች እና ትልቅ ባለ አራት ማዕዘን የካቴድራል ሕንፃ መገኘቱን ተመራማሪዎቹ ይፋ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም ከመዳብ የተሠራ እና የበሬ ራስ ምስል ያለው በወርቅ የተለበጠ ቀለበት ተገኝቷል፡፡ በቅሪተ አካል ጥናት ቡድኑ ሌሎች የተለያዩ የከተሜነት መገለጫ ቁሳቁሶች መገኘታቸውንም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያን አስመልክቶ ይህ ታላቅ ነገር መሆኑንም የጥናት ቡድኑ መሪ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ግሪክና ሮም ውስጥ በርካታ ቦታዎች ላይ ምርምሮች ተደርገዋል፡፡ ሆኖም፣ ከታላላቅ ጥንታዊ ከተሞች ጋር ተያይዞ አዳዲስ ግኝቶች የሉም፡፡ እዚህ ግን ይህ አስደናቂ ከተማ ተገኝቷል›› ብለዋል፡፡

በእንግሊዝ ሀገር ሎንዶን ከተማ ውስጥ የሚገኘው ሶአስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ጃኪ ፊልፕስ በበኩላቸው ‹‹ግኝቱ ከፍተኛ ዋጋ አለው፡፡ ስለአክሱምና ቅድመ አክሱም ሥፍራዎች ያለን አብዛኛው ዕውቀት ቀደም ሲል በተደረጉ ቁፋሮዎች፤ በይድረስ ይድረስ በተከናወነ እና አሁን ባለው መለኪያ መሠረት በአግባቡ ለሕትመት ባልበቁ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ነበር›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አዲስ የተገኘችው ጥንታዊት ከተማ ቤተ ሰማዕቲ በትግረኛ ቋንቋ የተሰየመች ሲሆን፣ ስያሜውም የሰሚዎች ቤት ማለት ነው፡፡ ጥናት የተደረገበት ቦታ በካርቦን ራዲየሽን ሲለካ ከ771 ዓ.ዓ እስከ 645 ዓ.ም ባሉት ዓመታት የነበረ እንደሆነም ተረጋግጧል፡፡ ይህ ቤተ ሰማዕቲ ከቅድመ አክሱም በፊት የነበረችና እስከ አክሱም ሥልጣኔ መነሳት ድረስ ሰዎች ይኖሩባት እንደነበር ያሳያል ብለዋል- አጥኝዎቹ፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ሌሎች ተጨማሪ ምርምር የሚጠይቁ መሰል ጉዳዮችም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ አጥኝዎቹ ይናገራሉ፡፡ አርክቴክት ንጉስ ቅዱስ ላሊበላ ዛሬ በወሎ ሮሃ ላስታ ላሊበላ የሚገኙትን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከማነፁ በፊት በጎጃም የተለያዩ አብያተ ክርስቲያትን እንዳነፀ ይነገራል፡፡

ከባሕር ዳር ከተማ በጥቂት ርቀት የዛሬው ምዕራብ ጎጃም ዞን አቸፈር ወረዳ ውስጥ ዋሻ ውስጥ አለት ፈልፍሎ ቤተ ክርስቲያን እንዳነፀ ይነገራል፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን የሚገኝበት የገጠር ቀበሌ አንኳ ሰግ ማርያም ይባላል፡፡ አሁንም ሰዎች ወደ ቦታው እየሄዱ ይጎበኙታል፡፡

ከዚህ ቀበሌ በቅርብ ርቀት ከፊል ከተሜ እና ከፊል ገጠሬ ቀበሌ አለ፡፡ ላሊበላ ሚካኤል ይባላል፡፡ ይህ ቦታ ሥያሜውን ያገኘው ለንጉስ ቅስዱስ ላሊበላ ማስተወሻነት በሚል እንደሆነም በአካባቢው አዛዎንቶች ይነገራል፡፡ ይህ ተጨማሪ ጥናት ይጠይቃል፡፡

በዛሬው አክሱም ከተማ ውስጥ ከመሬት ስር የተቀበረ ሌላ ከተማ እንደለም ፍንጮች አሉ፡፡ ይህም በጥልቅ ቢመረመር ነገ የሌላ ከተማ፣ የሌላ ሥልጣኔ ግኝትን የምናበስርበት ጊዜ ይሆናል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com