ዜና

ወታደር ነኝ! “የጦርነትን አስከፊነት በሚገባ አውቀዋለው፤ ጓዶቼን አጥቻለሁ” – ጠ/ሚ ዐቢይ  አህመድ

Views: 362

ታሪካዊ የሚባል ንግግር አድርገዋል

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ በኖርዌይ ኦስሎ የኖቤል የሰላም ሽልማት ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተው፣ ሽልማታቸውን በክብር ተቀብለዋል፤ በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በቅርቡ ይፋ በተደረገው የአገሪቱን ፖለቲካዊ ፍኖተ ካርታ ‹‹መደመር››ን በጉባዔው ሰብከዋል፡፡

ዶ/ር ዐቢይ ለኖቤል ሽልማት የበቁበት የኢትዮ ኤርትራ ግጭት፣ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲፈታ ከሁለቱም ወገን የጦርነቱን ገፈት የቀመሱ ሰዎች እና የኤርትራው አቻቸው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የነበራቸው ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር አውስተው፣ ፕሬዘዳንት ኢሳያስን አመስግነዋል፡፡

ወታደር መሆናቸውን የተናገሩ ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ የጦርነትን አስከፊነት ፊት- ለፊት በቦታው ተጋፍጠው የሚያውቁ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ጉዳቱን የሚያውቁት፣ ከ20 ዓመት በፊት የሬዲዮ ኦፕሬተር በመሆን በባድመ ግንባር ጦርነት ወቅት በርካታ የሚወዷቸው ጎደኞቻቸው ከጎናቸው እንዳጡ በንግግራቸው አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለኖቤል ሽልማት አሸናፊ ያደረጓቸውን ሦስት ምክንያቶች፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረውን አለመግባባት በመፍታት ሰላም እንዲወርድ በማድረጋቸው፣ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በሀገራቸው የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲሰፍን በር ከፋች ተግባራትን በማከናወናቸው እና በምስራቅ አፍሪካ የነበሩ ግጭትና አለመግባባቶችን ለመፍታት ውጤታማ ጥረት በማድረጋቸው የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኖቤል ኢንስቲትዩት የክብር መዝገብ ላይ በአማርኛ የተጻፈ ፊርማ በማኖር የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ኢንቲትዩቱ ባወጣው መረጃ አመልክቷል።

ዶ/ር ዐቢይ፣ በኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የ2019 ዓ.ም የኖቤል የሰላም ሽልማት ባለፈው መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም አሸናፊ ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።

ዶክተር ዐቢይ ለሰላም እና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ጥረት በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀው የድንበር የይገባኛል ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ተነሳሽነትን በመውሰዳቸው የ2019 ዓ.ም የኖቤል የሰላም ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ኮሚቴው መግለፁ የሚታወስ ነው።

ኮሚቴው፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማምጣት ቃል መግባታቸውን በማስታወስ፣ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበል ሁለቱ አገራት አስመራ ላይ የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙ ማስቻላቸው ለሽልማቱ እንዳበቃቸው ጠቅሷል።

ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ስምምነት በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሻክሮ የነበረው የጅቡቲና ኤርትራ ግንኙነት እንዲስተካል ሚና እንደ ነበራቸው አስታውሷል።

የኖቤል ኮሚቴው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለረጅም ዓመታት የነበረው ውጥረት እንዲፈታ ተነሳሽነት ሲወስዱ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ሀሳቡን በበጎ መልኩ ተቀብለዋል ብሏል።

የኖቤል ሽልማት አሰጣጡ ፕሮግራም ላይ፣ ድምፃዊ ብሩክታዊት ጌታሁን (ቢቲጂ) በአማርኛ እና ኦሮምኛ ዜማዎቿ ፕሮግራሙን አድምቀዋለች፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com