ዜና

ጃዋር ለማን ደግፎ ጠ/ሚ ዐቢይን ተቸ

Views: 270

‹‹የጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ አሕመድን እናት ህልም እውን እንዲሆን ያደረጉት እና ዐቢይን የመረጡት ኦቦ ለማ መገርሳ እና አባዱላ ገመዳ እንጂ፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኦዲፒ) አይደለም›› ሲል አክቲቪስት ጃዋር መሀመድ ገለጸ፡፡

ባለፉት የፖለቲካ ዘመናት፣ የለማ መገርሳን ያህል የኢትዮጵያ ባለውለታ የለም፤ ህዝቡ የሚያውቀውና (የማያውቀው) ትዕግስትና ቁርጠኝነት ያለው ሀቀኛ ሰው ነው ሲል ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

አክቲቪስት ጃዋር እንደሚለው ‹‹አሁን ለማ ላይ የሚደረገው ዘመቻ ማነኛውም ሰው ኦሮሞ ከሆነና ለመርህ እና ለህዝብ የቆመ ከሆነ ሰዎች ይጠሉታል›› ሲል አወዛጋቢ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ለኦሮሞ ህዝብ መብትና እኩልነት የምትቆም ከሆነ፣ ኃይሌ ፊዳን እንደጠሉት፣ ታደሰ ብሩን እንደሰቀሉት፣ ሌንጮ ለታን እንዳብጠለጠሉት ያብጠለጥሉኃል፤ ለማም ለማ ስለሆነ ወይ ጃዋር ስለሆነ ወይም ገመዳ ስለሆነ አይደለም ብሏል፡፡

‹‹ለማን በክብር እላይ ሰቅለው ይዘውት የነበሩት ሰዎች ለመርህ ስለለቆመ ብቻ ዛሬ የሚደረግበትን ዘመቻ ሳይ፣ ለዚህ ትውልድ ምን አይነት አዲስ ትምህርት መጣ ነው ያልኩት›› ሲል አክቲቪስቱ ተናግሯል፡፡

ለማ የትግል አጋሩ የሆነውን ዐቢይን ብልጽግና ፓርቲን መመስረቱን ጠብቆ ነው እንጂ የተቃወመው፣ ቀድሞ ቢናገር ኖሮ ብልጽግና የሚባል ነገር አይኖርም ነበር፤ ሊያቆመው ይችል ነበር ሲል የገለጸው አክቲቪስት ጃዋር፣ ብልጽግና ፓርቲ የሚባለው ካለቀ በኋላ ነው ለማ አቋሙን ግልጽ ያደረገው፤ የወንድሙንና የትግል አጋሩን ፍላጎት ጠብቆ፣ የራሱን ሞራልና ህሊና ጠብቆ ነው ያደረገው፡፡

እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የለማን አይነት የሀገር ባለውለታን ምንም አያደርገውም፤ ይልቁንም ያጠነክረዋል፤ ወደፊት ከፍተኛ ድርሻ ይዞ እንደሚቀጥል ጥርጥር የለኝም፤ ለማ አሁን ባለው ፖለቲካ ትልቅ ክብር ያለውና በህይወት እያለ ሀውልት ሊቆምለት የሚገባ ሰው ነው ብሏል- ጃዋር መሀመድ፡፡

ስለ ብልጽግና ፓርቲ የተጠየቀው አክቲቪስት ጃዋር ‹‹እነ ዐብይ የመሰረቱት ብልጽግና ፓርቲ በእኔ አተያይም ቢሆን በእርግጠኝነት አይዘልቅም፤ ምክንያቱም አንድም የጋራ ስምምነት ሳይደረግ ወደ ውህደት ሲገባ፣ ጥያቄዎችን ሁሉ ይዞ ስለሚገባ መቋቋም አይችልም፡፡ በአማራና በኦሮሞ መካከል ያለውን ሁኔታ እንኳን በምን መልኩ ይዘውት እንደሚቀጥሉ ያሳስባል›› ብሏል፡፡

ሌላው በሽግግር ላይ ነው ያለነው የሚለው አክቲቪስት ጃዋር፤ ሀገሪቱ በመፍረክረክ ላይ ባለችበት ሁኔታ የሚያስፈልገው ሰላማዊ ሽግግር ማምጣት እንጂ አዲስ ክርክር መጨመር አያስፈልግም ሲል ጠቁሟል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ የኦሮሞን ጥያቄ ሳይመልስ፣ የኦሮሞ ግለሰቦችን የበላይነት ሊያመጣ ይችላል፤ ኢህአዴግ በአንድ ፓርቲ በህውሓት የበላይነት የተያዘ ነበር፤ ብልጽግና ደግሞ በዐቢይ የበላይነት የሚያዝ ፓርቲ ነው፤ ስለዚህ፣ በአንድ ግለሰብ የተያዘ ፓርቲ ስለሆነ አልቀበለውም ብሏል፡፡

እነ ዐቢይ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በጣም የተማከለ ሥልጣን ይዞ ስለነበር ነው የሚተቹት የብልጽግና ፓርቲ አሰራር ግን የበለጠ ሥልጣንን ማዕከላዊ ያደርጋል ብሏል፡፡

አሁን ላይ ህዝቡ ካስተዋለው የክልል ሰዎች ከማዕከል ነው የሚሾሙት፤ አፋርን፣ ሶማሌን ወክለው የሚመጡት የውክልና ሥልጣን የሌላቸው ናቸው በማለት አክቲቪስቱ የብልጽግና ፓርቲን መመስረት ተችቷል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ መመስረቱ የፈጠረብን ፍራቻ፣ የኦሮሞን ጥያቄ አይመልስም፣ ያድበሰብሳል፣ እንዲሁም በእኛ ስም ሌላውን ይጨፈልቃል የሚል ነው ብሏል- አክቲቪስት ጃዋር መሀመድ፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com