ዜና

ለፊት ቆዳ ውበት እና ጤና

Views: 9524

(ካሌንዱላ /ፖት ሜሪጐልድ)

 መነሻ፡-

የሰው ፊት በተለያየ ጉዳት የተነሳ ጉስቁልና ሊደርስበት፣ ውበቱ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ለእዚህ ጥቂት ይረዳችሁ ዘንድ በቤት ውስጥ፣ ተፈጥሯዊ በሆነ ዘዴ፣ በቀላል ወጪ ምን ምን ነገሮችን ማድረግ እንደምትችሉ በጥቂቱ ተመልከቱ፡፡

 1. የፊት ቆዳ ችግርን መለየት

የሁሉም ሰው ፊት አንድ ዓይነት ችግር አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ችግሩን መለየት እና እንደ ኹኔታው የተገኘውን አማራጭ ምክር መጠቀም ነው፡፡ (ማጣቀሻ አንድ)

ሀ. ለሰፋፊ የፊት ቆዳ ቀዳዳዎች

 • የቲማቲም ጭማቂ መቀባት፣ ጥቂት ሲቆይ እና ፊት ላይ ሲደርቅ መታጠብ፣
 • አንድ የሻይ ማንኪያ የቲማቲም ጭማቂ እና የሎሚ ጭማቂ ቀይጦ መቀባት፣ ጥቂት ቆይቶ መታጠብ፤

ለ. ለፊት መጨማደድ

 • ማታ የለውዝ ዘይት ፊት እና አንገትን ላይ ማሸትና ማሳደር፤ እና ማለዳ አብሽ ቀብቶ መታጠብ፣
 • ጧት በባዶ ሆድ አንድ ማንኪያ ኮምጣጤን በአንድ ኩባያ ውሃ ላይ ጨምሮ ትንሽ ስኳር አክሎ መጠጣት፣

ሐ. በፊት ላይ ወዝ ሲበዛ

 • ለፊት የሚበቃ ማር፣ የሎሚ ጭማቂ እና ለብ ያለ ውሃ አደባልቆ ፊትን መቀባት፤ (ይህ የፊትን ቅባት ይመጠዋል)፤ አቆይቶ መታጠብ፤
 • ሙዝ ቆዳ የሚፈልጋጀው ቫይታሚን የያዘ ስለሆነ፤ የበሰለ ሙዝ መጨፍለቅ እና ከ2 ማንኪያ ወይራ ዘይት ጋር መምታት፣ ከዓይን ራቅ አድርጎ ፊትን መቀባት እና ከ 25 ደቂቃ በኋላ መታጠብ፣

መ. ለፊት ቆዳ ድርቀት

 • ሁለት የሻይ ማንኪያ የሽንብራ ዱቄት እና አራት የሻይ ማንኪያ የላም ወተት ማዋሃድ፤ ዓይን እና ከንፈር ዙሪያ አስቀርቶ ፊትን በሙሉ መቀባት፣ ከ 2ዐ ደቂቃ በኋላ መታጠብ፤
 • የእንቁላል አስኳል፣ አንድ የሻይ ማንኪያ የለውዝ ዘይት፣ የሻይ ማንኪያ የወተት ስልባቦት አደባልቆ መቀባት፣ አምስት ደቂቃ ካቆዩ በኋላ መታጠብ፣
 • የበሰለ ሙዝ፣ ማር፣ የወተት ስልባቦት በአንድ ላይ መምታት እና ማታ መቀባት፣ ጠዋት መታጠብ፣
 • ኦትስ (ሲናር አጃ) ጥሬው ዱቄት ከማር ወይም ከወተት ጋር ይመታል፤ ይህን ፊት መቀባት እና ከ 15 ደቂቃ በኋላ መታጠብ፡፡

ሠ. ለማድያት እና ለፀሐይ ቃጠሎ

 • አደይ አበባ (ቢገኝ እርጥቡን) መጨፍለቅ ወይም መፍጨት እና ከለጋ ቅቤ ጋር መቀባት፡፡ አደይ አበባን በወቅቱ ሰብስቦ ማቆየት፣ ወይም ዘሩን በማልማት መጠቀም ነው፡፡
 • የአብሽ ዱቄት በለጋ ቅቤ ለውሶ ማታ ተቀብቶ አድሮ ጠዋት መታጠብ፡፡
 • ጥቂት የኦቾሎኒ ፍሬዎች መፍጨት፣ በአንድ የሻይ ማንኪያ እርጎ ወተት ደባልቆ፣ በስሱ መጠፍጠፍ፣ በተጎዳው ቦታ ላይ መለጠፍ፣ ከ 15 ደቂቃ በኋላ አንስቶ መታጠብ፤

የቀጋ አበባ እና የቀጠጥና አበባ ለቅሞ በአንድነት መደቆስና በለጋ ቅቤ ማታ መቀበት ጠዋት መታጠብ፡፡

(ቀጠጥና ተክል)

 1. ሁለገብ የፊት ቆዳ አብነት

አንዳንድ የተፈጥሮ መድኃኒቶች ሁለገብ ጥቅም አላቸው፡፡ ለምሳሌ ካለንዱላ እንደዚህ ነው፡፡

ካሌንዱላ አበባ

ካሌንዱላ ተክልን በቀላሉ ፍሬውን በመዝራት ማልማት ይቻላል፡፡ አመቱን ሙሉ ያብባል፡፡ ይህ ተክል አበባው ተለቅሞ አድርቆ ማቆየት ይቻላል፡፡ አንድ ማንኪያ የደረቀውን አበባ በአንድ ማንኪያ ወይራ ዘይት ጨምሮ ዘፍዝፎ ማቆየት፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ፊትን መቀባት ይቻላል፡፡ በተለያየ ምክንያት ለተጎዳ ፊት ጥሩ አብነት ነው፡፡

(የካሌንዱላ ተክል)

ማጠቃለያ፡-  

የፊት ውበት ለመጠበቅ እነዚህን ምክሮች አስተውሉ፡፡

 • በቂ ንፁህ ውሃ በአግባብ መጠጣት፣ የውሃ እጥረት የቆዳ ድርቀት ያስከትላልና፣
 • የአንድ ሎሚ ጭማቂ ውሃ ላይ ጨምሮ ጧት አዘውትሮ መጠጣት፤
 • ተስማሚ የፍራፍሬ ጁስ መጠጣት፣
 • የቲማቲም ጁስ መጠጣት፣
 • ተልባ ታምሶ ተውቅጦ፣ እንደ ጁስ መጠጣት፣
 • የጥጥ ፍሬ (ቢገኝ የአበሻ ጥጥ ፍሬ) መውቀጥ እና መፍጨት፣ ይህንን ማታ በለጋ ቅቤ ለውሶ መቀባት ለፊት ቆዳ ውበት ይረዳል፣
 • የእርድ ዱቄት በለጋ ቅቤ ለውሶ መቀባት ከአራት ሰዓት በኋላ ለብ ባለ ውሃ መታጠብ፣
 • አንድ ካሮት ልጦ መፍጨት፣ ጥቂት የላም ወተት መጨመር፣ ወይም የእንቁላል አስኳል አብሮ መምታት፣ ተቀብቶ ማደር እና ጧት መታጠብ፣
 • የእንቁላል አስኳል በማር ለውሶ ቀብቶ፣ ጥቂት አቆይቶ መታጠብ፤ በቆዳ ላይ የሚገኙ መልክ አጥፊ ምልክቶችን ያስወግዳል፣
 • ማር ተቀብቶ ቆይቶ መታጠብ፣ ከዚያም የወይራ ዘይት መቀባት፣ ይህንንም ማዘውተር፤
 • በተቻለ መጠን ፊትን ከሐይለኛ የፀሐይ ጨረር መጠበቅ፣

(ዘወትር የፊታችሁን ጤና ተንከባከቡ፡፡)

ማጣቀሻ አንድ፣   በቀለች ቶላ፣ 2ዐዐ9 ዓ.ም፣ ሕክምና በቤታችን፣ የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና በተፈጥሮ መድኃኒት፤ 5ተኛ እትም፣ አልፋ አታሚዎች፣ አዲስ አበባ

በተጨማሪ ከፊት ቆዳ ጋር በተገናኘ በዚሁ አምድ ላይ በሚከተሉት ሊንክ ላይ አንብቡ

 1. https://ethio-online.com/archives/4415

  የቆዳን በሽታ (Skin disease) በአብሽ፣እሬት፣ቁልቋል፣ቁርቁራ፣ግራዋ፣እንዶድ እና እርድ ታከሙት

2. https://ethio-online.com/archives/2402  ፀጉርን እንዲህ ተንከባከቡ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com