ዜና

ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ ተወሰነ

Views: 209

የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች በሚቀጥለው ሳምንት በፌዴራል ጥበቃ ሥር ይሆናሉ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ በሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ፤ በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ መወሰኑን ለኢትዮ-ኦንላይን ገለጸ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ሁሉ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት መሆናቸው ታሳቢ ተደርጓል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዩንቨርስቲዎቹ ውስጥ እየተከሰተ ያለውን ግጭት በፍጥነት ለማስቆም እና ጸጥታውን አስተማማኝ ለማድረግ፣ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ ክፍተት እየፈጠረ ስላስቸገረ፣ በፌደራል ፖሊስ ለማስጠበቅ እንደተወሰነ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደጃሳ ጉርሙ ለኢትዮ-ኦንላይን ተናግረዋል፡፡

ግጭት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ፣ በፌዴራልም ሆነ በመከላከያ ኃይል እየተጠበቁ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ ያሉት አቶ ደጃሳ፣ የፌደራል ፖሊስ በየዩኒቨርሲቲዎቹ አባላቱን የሚመድብ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ፣ ይህ አሰራር መጀመር ባሉባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ተጀምሮ በሂደት ሁሉም ጋር ተግባራዊ እንደሚሆን አቶ ደጃሳ ለኢትዮ-ኦንላይን ዘጋቢ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊትም አሁን ካለው ቴክኖሎጂ፣ የተማሪ ቁጥር እና የተማሪ ደህንነት ጋር አብሮ የሚሄድ የተሻለ የተጠናከረ አካል ለመመደብ እና የግቢ ፖሊስን ለማስቀረት እየተሰራ እንደነበርም አክለው ገልጸዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com