“ቄሮ” በአሸባሪነት እንዲፈረጅ የሚጠይቅ ሠነድ ለተባበሩት መንግሥታት ቀረበ

Views: 77

በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ዙሪያ በኢ-መደበኛ አደረጃጀት በስፋት የሚንቀሳቀሰው “ቄሮ” የተሰኘው የወጣቶች ቡድን፤ በአሸባሪነት እንዲፈረጅ የቀረበውን ጥያቄ ታዋቂው ምሁር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ለተባበሩት መንግሥታት አቀረቡ፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በአቶ ጁሀር መሀመድ የሚመራው እና ራሱን ቄሮ ብሎ የሚጠራው ቡድን በአሸባሪነት እንዲፈረጅ የተጠየቀውን የሕዝብ ጥያቄ ዛሬ ኒውዮርክ ለሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት አቅርበዋል፡፡

ሁለት ዓይነት ቄሮ መኖሩን እና የሽብርተኝነት ፍረጃ ጥያቄው የሚመለከተው ተደራጅቶ የሰብዓዊ መብት ረገጣና ጥፋት የሚፈፅመውን የሚመለከት እንደሆነ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማብራራታቸውንም እንስክንድር ነጋ ተናግሯል፡፡

‹‹በጁሀር የሚመራው ቡድን በመንግሥት ውስጥም ተባባሪዎች እንዳሉት አሳውቀናል›› ብሏል እስክንድር ነጋ፡፡

በፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ የሚመራና ዝርዝር መረጃዎችን የሚያቀርብ ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡

ዛሬ የተደረገው ግን ጥቃት በማንኛውም ጊዜ ሊደርስ ስለሚችል ለተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ መብት ድርጅት ጉዳዩን ከማሳወቅ የዘለለ አለመሆኑንም እስክንድር ነጋ አብራርቷል፡፡

እየደረሰ ያለው ችግር ‹‹እንዳንናገር ተከለከልን፤ እንዳንፅፍ ተከለከልን፤ ከሚው የተለየ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፤ ይህ የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህንን ነው ለማሳወቅ የሄድነው›› ብለዋል ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፡፡

 

ቡድኑ በሽብርተኝነት ይፈረጅ የሚለው ጥያቄ የሕዝብ መሆኑንም ፕሮፌሰር ጌታቸው እና እስክንድር ገልፀዋል፡፡ ጉዳዩን ራሱ ተቋሙ እንዲመረምር መናገራቸውን ፕሮፌሰር ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡

‹‹ጥያቄውን ያቀረብነው የተባበሩት መንግሥታት በቀጥታ መፍትሔ እንዲሰጠን አይደለም፤ ይሄንን የዘር ፍጅት አደጋ የሚከላከለው ራሱ ሕዝቡ ነው›› ብሏል እስክንድር፡፡

‹‹እናንተ የዘር ፍጅት እየተደረገ መሆኑን እንዴት አወቃችሁ›› የሚል ጥያቄ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች እንደቀረበላቸውም ፕሮፌሰር ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ቡድኑ ለጥፋት ተግባሩ ተደራጅቶ ሲመጣ ለአባላቱ በመገናኛ ብዙሃን ጥሪ እንደሚያቀርብና ይህንንም መስማታቸውን እንዳብራሩላቸው ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በጨማሪም የተገደሉ ሰዎች አስክሬን እንደመቀጣጫ በጎዳና ላይ ሲጎተት በተንቀሳቃሽ መስሎች ማየታቸውን ብሎም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የ86 ዜጎችን ግድያ አስመልክቶ የሰጡትን መግለጫ በመተንተን እንደማስረጃ አቅርበዋል፡፡ የፎቶ እና የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃዎችንም ለተባበሩት መንግሥታት የሥራ ኃላፊዎቹ ማሳየታቸውን ተናግረዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com