ዓብዮታዊ ዴሞክራሲ አግላይና አርብቶ አደሩን የገፋ ነው ተባለ

Views: 49

የኢሕአዴግ መርህ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በነበረበት ወቅት፣ አጋር የተባሉት ድርጅቶች አጋርነትን እራሳቸው ፈልገው ሳይሆን፣ ከድርጅቱ ተሰጥቷቸው ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል ም/ል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ተናገሩ፡፡

እነዚህ አጋር የተባሉት ድርጅቶች በወቅቱ የሕብረተሰብ መሠረታቸው አብዮታዊ ዴሞክራሲን መሸከም ስለማይችሉ አጋር ድርጅቶች ይሁኑ ተብሎ ነው የተወሰነው፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲን ለመሸከም ሳይንሳዊ ምክንያት አልቀረበም፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ውስጡ ልማታዊ መንግስት ለመፍጠር፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ለማስከበር፣ ፍትሕ ለማስፈን እና በኢኮኖሚ ላይ የመንግስት ሚና መኖር አለበት የሚል ነው፡፡

ስለዚህ አርብቶ አደር ማህበረሰብ የተባለ ሁሉ ምኑን ነው የማይሸከመው አርብቶ አደር ማህበረሰቦች እንዴት አብዮታዊ ዴሞክራሲን መሸከም እንደማይችሉ የተብራራ ነገር ሳይኖር፣ በደፈናው ነው መሸከም አይችሉም ተብለን ለ27 ዓመታት የኖርነው ብለዋል፡፡

ከሶማሌ ክልል አኳያ እንኳን ብናይ፣ ህዝቡ እራሱን እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንዲያይ አድርጎታል፤ ስለ ኢትዮጵያ ሲወሰን የሶማሌ ህዝብ ምንም አስተዋጽዎ የለውም ነበር፤ የተወሰነው ነገር የሚደርሰን በኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት በኩል ነው፡፡

ስለዚህ አመራሮችም ሆኑ ህዝቡ በውህደቱ ላይ ግፊት ሲያደርግ ነው የቆየው በማለት አቶ ሙስጠፌ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል፡፡

የሱማሌ ህዝብ ውህደቱ እንዴት ይፈጸም የሚለውን ሳይሆን ሲጠይቅ የነበረው፣ እኛ ወደ መሐል መምጣት አለብን፤ ለምንድነው ከእኛ ውጪ ሀገራዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑት፤ እኛ ኢትዮጵያውያን አይደለንም ወይ የሚለውን ስሜቱ በተለያዩ መልኮችም ገልጿል ብለዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com