ዜና

ኮሸሽላ ለጉበት ጤና (Milk thistle)

Views: 809

ምስል አንድ ኮሸሽላ Milk thistle ገና ለጋ ሳለ

መነሻ፡-

ኮሸሽሌ በተለምዶ መጠሪያ ስሙ ብዙ ነው፡፡ የአህያ እሾህ ወይም ነጭ ኮሸሽሌ ተብሎም ይጠራል፡፡ በሳይንሳዊ ስም ሲላይማሪን ማሪያኑም (Silymarin Marianum) ይባላል፡፡

መገኛ አገሩ ሜደትራንያን ዙሪያ ባሉት አገራት ነው ይባላል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በጣሊያን ወረራ ጊዜ ነው ብለው ያሙታል፡፡ ዋና ሥራው ኢትዮጵያ ውስጥ ደጋ አካባቢ መንገድ ዳር ይበቅልና መንገድን ያደምቃል፡፡ ወይም ዱር በቀል ነው፡፡ በጣም ጥቂት የተፈጥሮ መድኃኒት ወዳጆች ጥቂት ሰብስበው ጥቅም ላይ ያውሉታል፡፡

በሌሎች አገራት ግልጋሎቱ ታውቆ በብዙ አምርተው፤ በማቀናበር አዘጋጅተው ተጨማሪ መድኃኒት “ሰፕሊመንት” በማለት ወይም የተፈጥሮ መድኃኒት ብለው ይሸጡታል፡፡  ይህ በሌላ አገር የሚሸጠውን ወደ እኛ አገር እንደሌላው መድኃኒት ስለማይመጣ ገበያ ላይ ማግኘት አይቻልም፡፡ እንግዲያውስ “ያስፈልገኛል” ያለ ወቅቱን ጠብቆ ከመንገድ ዳር መልቀም ይችላል፡፡ አለዚያም ከውጪ አገራት በሰው ማስገዛት ነው፡፡ ዋጋው ግን ቀላል አይደለም፡፡

ሀ. ዋና መድኃኒትነቱ ለጉበት ነው፡-

ጉበት በብዙ ህመም ሊጎዳ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የተለያየ ሄፐታይተስ፣ ሲሮሲስ፣ ወይቦ፣ የጉበት በቅባት መታፈን እና የመሳሰሉት ህመሞች ጉበትን ሊያጠቁ ይችላሉ፡፡

በተለይም ሲሮሲስ በዘመናዊ መድኃኒት ለማዳን በጣም አዳጋች ነው፡፡ ብዙ የሚረዳ መድኃኒት የለም፡፡ ታማሚው የመጀመሪያውን የሲሮሲስ ምልክት እንዳየ፣

 • አልኮል መጠጣትን ፈጽሞ መተው፣
 • በቂ እና ተስማሚ አትክልት እና ፍራፍሬ መመገብ፣
 • ብዙ ፕሮቲን ያላቸውን እንደ ሥጋ፣ እንቁላል፣ አሳ አለመመገብ፣
 • ሰውነት እብጠት ከጀመረ ጨው አለመመገብ፣

ለእነዚህ የጉበት በሽታዎች በመደበኛው የሕክምና ዘርፍ የሚሰጠው መድኃኒት እና ምክር እንዳለ ሆኖ ኮሸሽላን ዘር መጠቀም በብዙ ይረዳል፡፡ ማጣቀሻ አንድ  ላይ ባለው ሊንክ በሰፊው ማንበብ ይቻላል፡፡

ለ. ዘሩን በወቅቱ መልቀም፡-

ነጭ ኮሸሽሌ ዘሩ የሚለቀመው ከመስከረም እስከ ኅዳር ባሉት ወራት ነው፡፡ መጀመሪያ አያያዙ እሾሃም ሆኖ መሬት ላይ ይስፋፋል፡፡ መስከረም ላይ ከመሐሉ ዘንግ መስሎ ያድጋል፤ ከጥሎም አናቱ ላይ ወይንጠጅ መልክ አበባ ያብባል፡፡ ባፈራ ጊዜ አበባው ይደርቅና ብናኝ ነገር ወይም ልጆች “እፉዬ ገላ” የሚሉት ይኖረዋል፡፡

ከዚህ ብናኝ ሥር ትንሽ ኳስ መሳይ በሾህ የተከበበ ክፍል አለው፡፡ እዚህ ክፍል ውስጥ ጠቆር ያለ ሱፍ የሚመስል ምርት አለው፡፡ በወቅቱ ካልተለቀመ ሱፍ መሳይ ፍሬው ይበተናል፡፡ ምንም ዘር ከውስጡ አይቀርም፡፡ ከመበተኑ በፊት እንዝርት መሳይ አናቱን እየቆረጡ፤ ዘሩን ከውስጥ እያፈሰሱ መልቀም ነው፡፡

መልቀሙ ግን ትንሽ ያስቸግራል፡፡ ሆኖም ለጉበት ያለው የጤና በረከት ሲታሰብ ቀላል ነው፡፡ ደግሞስ ሳያርሱ፣ ሳያርሙ ወቅቱን ጠብቀው አንድ ቀን መሰብሰብ ከባድ አይደለም፡፡ በዚህ በኅዳር ወር ላይ ተበትኖ ወደ መጠናቀቁ ነው፡፡ የደረሳችሁበትን ያህል ሰብስቡ፡፡

በጣም በአነስተኛ መጠን አስለቅመው የሚሸጡም አሉ፡፡ እሱም ቢገኝ መቶ ግራም ከ 6ዐ እስከ 8ዐ ብር ይሸጣል፡፡ ነገር ግን ከጥቂት ወራት በኋላ እንኳን በዚህ ዋጋ ቀርቶ፤ ከዚህ 5 እጥፍ እከፍላለሁ የሚል ገዥ ቢመጣ አይገኝም፡፡ መግዛቱ ግን አስተማማኝ መጠን ስላልሆነ በርትቶ መሰብሰቡ መልካም ነው፡፡

ምስል ሁለት ማፍራት የጀመረ የአህያ እሾህ

ሐ. የኮሸሽላ ዘር ለመድኃኒት አጠቃቀም

. 1. ከዱር የሚለቀመው ከሆነ

አንድ ስኒ ሱፍ መሳይ ዘሩን ለሰስ ባለ የሸክላ ምጣድ ላይ ማመስ፣ ከዚያም

 • ከገብስ ቆሎ ጋር ቀይጦ በመጠን አድርጎ መብላት ይቻላል፡፡ ወይም
 • መፍጨት (መለንቀጥ) እና ለብ ባለ አንድ ሊትር ውሃ በጥብጦ ማር አክሎ መጠጣት

በየቀኑ መመገብ ወይም መጠጣት ይቻላል፡፡ ለወራት ያህል እንዲሁ መቀጠል፡፡ ይህ ዘዴ ባጠቃላይ ለጉበት ጤና ይረዳል፡፡ በተለይ ግን ለሲሮሲስ እጅግ የተሻለ ነው፡፡ ማጣቀሻ ሁለት

. 2. ከውጪ አገር የሚገዛው ከሆነ

ከውጪ አገር የሚገዛው እንደ ዱር በቀል በጥሬው አይደለም፡፡ ተጨምቆ፤ ተጣርቶ፣ በአነስተኛ መጠን ነው፡፡ የአጠቃቀም መመሪያው አብሮት አለ፡፡ ስለዚህ በተነገረው መሠረት መጠቀም ነው፡፡ ከታች ምስሉ ላይ ያለው ምሳሌ ለማሳየት ያህል ነው፡፡ በአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ በህንድ በተለያየ ዓይነት ይዘጋጃል፡፡

This image is courtesy to Jamieson.ro

መ. ለሌሎች ህመሞችም ይረዳል

የአህያ እሾህ ዘሩ ከላይ ለጉበት ከተነገረው ሌላ ለብዙ ሕመሞች እንደሚረዳ በጥናቶች ላይ ይነበባል፡፡ ማጣቀሻ አንድ ላይ ሜዲካል ኒውስ ቱደይ እንደሚለው/

 • ከዘሩ የሚዘጋጀው ዘይት በሰውነት ቆዳ ላይ ሲቀባ ለብዙ የቆዳ በሽታ ይረዳል፣
 • ለጤና መልካም ያልሆነውን ኮልስትሮል በመቀነስ፣ ለልብ ጭምር ይረዳል፣
 • ልክ አለፍ ውፋሬ እና ክብደት ለመቀነስ ይረዳል፣
 • ለዓይነት 2 የስኳር በሽተኞች ሰውነት ኢንሱሊንን በአግባብ እንዲጠቀም ያደርጋል፣
 • በአለርጂ እና አስም ለሚታመሙት ስቃዩን ይቀንሳል፣
 • በነቀርሳ (ካንሰር) ለተያዙት የነቀርሳ ሴሎች ወደ ብዙ አካል እንዳይስፋፉ ያግዳቸዋል፡
 • የአጥንት ጤናን በእጅጉ ይረዳል፣
 • የአልዛይመር (በጣም ዝንጉ መሆን) በሽታን ይከላከላል፣
 • ለሰውነት የበሽታ መከላከል አቅምን ያጎለብታል፡፡

 ማጠቃለያ

የአህያ እሾህን በሚበቅልበት ደጋ አካባቢ አሁን በወቅቱ ተበትኖ ሳያልቅ መሰብሰብ ብልጠት ነው፡፡ ነገር ግን ትልቁ ጉዳይ ይህንን ዘር በብዙ መጠን ለማምረት የሚያቅድ ሰው በብዙ መጠን እራሱን እና አገርን ይጠቅማል፡፡ ደጋ አካባቢ ባሉ ከተሞች መንገድ ዳር እና በአገር አቋራጭ መንገድ ዳርቻ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ኮተቤ፤ አያት፣ ከአያት ወደ ቱሉ ዲምቱ በሚወስደው መንገድ ዳርቻ አለላችሁ፡፡ ወደፊት ለማልማት የሚያቅድ ሰውም ቢሆን ለዘር የሚሆነውን ቢሰበስብ እጅግ ጥሩ ነው፡፡

ማጣቀሻ

ማጣቀሻ አንድ https://www.medicalnewstoday.com/articles/320362.php#ten-health-benefits-of-milk-thistle

ማጣቀሻ ሁለት፣ በቀለች ቶላ፣ 2ዐዐ9 ዓ.ም፣ ሕክምና በቤታችን፣ የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና

በተፈጥቶ መድኃኒት፣ አልፋ አታሚዎች፡ አዲስ አበባ፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com