ዜና

“ህወሓት የራያ የማንነት ጥያቄን የሚያነሱ ወጣቶችን እያፈነ ነው” አቶ ደጀኔ አሰፋ

Views: 349

                                                    (የራያ ሕዝብ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ)

ህወሓት በክልሉ የፀጥታና የደህንነት አካላት፣ በልዩ ኃይሉ እና በአካባቢ ሚሊሻዎች የራያ ሕዝብን የማንነት ጥያቄ የሚያነሱ ወጣቶችን እያፈነ፣ እያሰረና በድብቅ እስር ቤቶች እያንገላታቸው እንደሆነ ምንጮች ለኢትዮ-ኦንላይን ገለጹ፡፡ የራያ የማንነት ጥያቄን ይደግፋሉ ያላቸውን ኃላፊዎችም ከክልሉ መንግሥት መዋቅር እያፈናቀለ ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄን አንስተው የጠየቁ ከሁለት ሺህ አንድ መቶ በላይ ወጣቶች በትግራይ ክልል ማይጨው፣ ኪኋ፣ መቀሌ፣ ተንቤን እና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በዓላማጣ እስር ቤቶች በገፍ መታሰራቸውን የራያ ኮረም ከተማ ምክር ቤት አባላት ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

የዶ/ር ዐቢይ መንግሥትን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ የፖለቲካ ምኅዳሩ ይሰፋል፣ የማንነት ጥያቄያችንም በአግባቡ ይመለሳል የሚል ተስፋ ቢኖረንም፤ በህወሓት በኩል ከቀድሞ በባሰ መልኩ ግድያው፣ ጭቆናው፣ አፈናው፣ የአንድ ለአምስት ጥርነፋ እጅግ በርትቷል በማለት ገልጸዋል፡፡

የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ጫፍ በደረሰበት በአሁኑ ጊዜ፤ የህወሓት አንጋፋ ፖለቲከኞችና ኃላፊዎች ይህን የማንነት ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችን እያፈኑ፣ እየገደሉ፣ እያሰሩና እያሰቃዩ ጥያቄውን ማዳፈን፣ ማክሰምና መቀልበስ ነው የሚፈልጉት በማለት ለዘጋቢያችን አስረድተዋል፡፡

የሕዝባችን ዋና ጭንቀት፣ ህወሓት ይሄን የሕዝብ ትግል ለመቀልበስ በምትወስደው እርምጃ፣ ሕዝባችንን ያለ አስፈላጊ ዋጋ አስከፍላ፤ ወንድማማች የሆነውን የራያ እና የትግራይ ሕዝብን እንደ ሕዝብ እንዳያጋጭ ነው ብለዋል፡፡

የራያ ሕዝብ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደጀኔ አሰፋ፣ ከ1983 – 84 ዓ.ም ጀምሮ የራያ ሕዝብ ከፍተኛ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ በደል እየደረሰበት ይገኛል ብለዋል፡፡

የራያ ተወላጆች በሰላማዊ መንገድ የማንነት ጥያቄ አንስተው ሲታገሉ ይታፈናሉ፤ ይገደላሉ፤ አካላቸው እንዲጎድል፣ ከትውልድ ሥፍራቸው እንዲፈናቀሉ፣ ከሥራ እንዲባረሩ ተደርጎ በገፍ ይታሰራሉ፡፡

ከትውልድ ሥፍራቸውም እንዲሰደዱ፣ ከዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ፣ ከሹመታቸው እንዲወርዱ፣ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጎ ንብረታቸውንና ሃብታቸውን እየተነጠቁ፣ እየደኸዩ እንዲሄዱ ነው በህወሓት ዲዛይን ተደርጎ እየተሰራ ያለው በማለት አስረድተዋል፡፡

በእርግጥ ወደ ገዢው ፓርቲ ህወሓት የተጠጉ ጥቂት ግለሰቦች ሥልጣን አግኝተው፣ ጥቅማ ጥቅም አግኝተው እየኖሩ ነው ያሉት አቶ ብሩክ አገዞም ይህ ግን የራያን ሕዝብ ሁኔታ አያመላክትም ብለዋል፡፡

በራያ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጥቅሞቻቸው ተከብሮላቸው ይኖራሉ፤ በራያ የትግራይ ብሔርን የበላይነት ለማረጋገጥ ህወሓት ተግቶ እየሰራ ነው በማለት ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

የራያ ሕዝብ ላለፉት 28 ዓመታት ለመብቱ ሲታገል የከረመ ነው፤ ህወሓት ገና ከመነሻው የራያ ሕዝብን ያለ ፍላጎቱና ፈቃደኝነቱ፣ በጉዳዩ ላይ ምንም ሳያሳትፈው ነው ወደ ትግራይ ክልል እንዲካለለ ያደረገው ብለዋል፡፡

ይሄ የህወሓት ትምክህተኝነት የራያ ሕዝብን የማንነት ጥያቄ እንዲያነሳና እንዲታገል አድርጎታል ብለዋል፡፡

በዚህ የማንነት ጥያቄ ሳቢያም በርካታ የራያ ተወላጆች መስዋዕትነትን ከፍለዋል፣ ተገድለዋል ያሉት አቶ ብሩክ፣ አካላቸው ጎድሏል፣ መሬታቸውን ተነጥቀዋል፤ ሃብት ንብረታቸውን አጥተዋል ብለዋል፡፡

ላለፉት 28 ዓመታት የራያ ሕዝብ ለመብቱ ሲታገል የከረመ ነው ያሉት አቶ ደጀኔ አሰፋ በበኩላቸው የራያ ሕዝብ ሽማግሌዎች በየአደባባዩ ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ ተግዘዋል፤ በራያ ኮረም ከተማ (ወረዳ) ብቻ ሰባት የሀገር ሽማግሌዎች በገበያ ላይ በአደባባይ ተገድለዋል፡፡

ይህም፣ የማንነት ጥያቄውን ለማዳፈን፣ በሕዝቡ ተሰሚነት ያላቸውን የሀገር ዋርካ ሽማግሌዎችን ማጥፋት፣ ሕዝቡን ለማሸማቀቅ እና ሃብቱን ለመጋራት ሌሎች የትግራይ ሰዎችን በአካባቢው ላይ አምጥቶ የማስፈር ሥራ በብዛት ተሰርቷል ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በሰሜን ወሎ አሥተዳደር ስር የነበረው የራያ ማኅበረሰብ፣ በአሁኑ ጊዜ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ እንዳለው የሚገመት ሲሆን፣ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በትግራይ ክልል ሥር እንዲካለል መደረጉ ይታወቃል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com