ዜና

የአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ 3 መቶ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ማስመለሱን ገለጸ

Views: 244

በአዲስ አበባ ከተማ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ ሦስት መቶ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታን ማስመለሱን የከተማዋ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የሠላምና ፀጥታ ቢሮ የ2012 ዓ.ም የሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለከተማ አስተዳድሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡

ቢሮው በሥሩ በሚመራው የአዲስ አበባ የደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽሕፈት ቤት በኩል ሕገ- ወጥ ግንባታዎችን፣ ሕገ-ወጥ የጎዳና ላይ ንግድን እና ሕገ-ወጥ እርድን ሲከላከልና ሲቆጣጠር መቆየቱን አስታውቋል፡፡

በሩብ ዓመቱ ውስጥ በሕገ-ወጥ ሂደት ተይዞ የቆየ ሦስት መቶ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ማስመለሱንም በሪፖርቱ መገለፁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የሕዝብ ተወካች ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አዲስዓለም እንቻለው በተለይ ለኢትዮ ኦንላይን ያብራሩ ሲሆን፣ ተነሺዎቹ የት እንደተወሰዱ ግን አልገለፁም፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የከተማዋን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑንንም የሠላምና ፀጥታ አስተዳድር ቢሮው ለምክር ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት አመላክቷል፡፡

ሕዝብ በአደባባይ በሚሰበሰብባቸው ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት ላይ ፀጥታን በአግባቡ ማስከበሩንም ጠቁሟል፡፡

ቢሮው በሥሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን፣ የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲን እና የአዲስ አበባ የደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽሕፈት ቤትን ይመራል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com