ኪኑዋ (Quinoa) እንጀራ ተጋገረ

Views: 260

መግቢያ

የዓለም ምርጥ እህል የተባለው አንዱ ኪኑዋ ወይም ኪኙዋ ነው፡፡  በሳይንስዊ ስሙ ቼኖፖዲየም ኪኑዋ (Chenopodium quinoa) ይባላል፡፡ የቼኖፖዲየም ዝርያ ዓይነቶች በዓለም ላይ ብዙ ናቸው፡፡  የሳር ቤተሰብ አይደለም ተቀራራቢነቱ ለቀይስር እና ለእስፒናች ነው፡፡ በዝርያ ወይም በቤተሰብ ከአማራንተስ (አሉማ) ጋር አንድ ነው፡፡  እ.ኤ.አ  2ዐ13 አመት በተባበሩት መንግስታት የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ዓለም አቀፍ የኪኑዋ አመትተብሎ ተሰይሞ ነበር፡፡  የስያሜው መታሰቢያነት ለቀደምት የኤንደን ትውልድ ነው፡፡ እነሱ ናቸው ለምግብነት አላምደው ለዛሬው እና ለወደፊቱም ትውልድ ጠቀሜታ ያቆዩት፡፡ ኪኙዋ ነቅመነሻው በላቲን አሜሪካ የኤንደን ምድር ሲሆን ፔሩ፣ ቦሊቪያ፣ ኢኳዶር እና ኮሎምቢያ ውስጥ ከዘመናት በፊት ለሰው ምግብነት የሚዘራ ነበር፡፡ ማቀጣሻ አንድ

ሀ. ኪኑዋ የዓለም ቁንጮ እህል

ኪኑዋ የዓለም ቁንጮ እህል መሆኑ ከተነገረ ከረመ፡፡ ኪኑዋን ዝና ያጎናፀፉት እና በብዙ የዓለም አገራት አውሮፓን ጨምሮ እንዲስፋፋ ያደረጉት፤

  • ግሉተን አልባ እና ለሰው ጤና ተስማሚ መሆኑ፣
  • ብዙ የተፈጥሮ ችግር ተቋቋሚነቱ፤
  • ብርድን፣ የዝናብ እጥረትን መቋቋሙ
  • የንጥረ ምግብ ይዞታው በተለይም ካልስየም፣ ፎስፈረስ እና ብረት ተመጣጣኝ እና ከሌሎች የእህል ዓይነቶች ተሽሎ መገኘቱ፣
  • የኘሮቲን እና የስብ ይዞታው ከፍተኛነት፣
  • በአበቃቀሉ ደረቅ አፈርን የሚቋቋም መሆኑ፣እና ወዘተ ናቸው፡፡

ቀደም ብሎ የዓለም ቁንጮ እህል ወይም ምግብ የተባሉት ኪኑዋ፣ አማራንዝ እና በክዊት ነበሩ፡፡ ጤፍ ከዝናው ጎራ የተደመረችው ቆይታ ነበር፡፡ ቢሆንም ከእነዚህ ውስጥ በጣም ዋነኛው ኪኑዋ እንደሆነ በብዙ ጥናት ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡ ኪኙዋ በዓለም የተሰጠው ደረጃ  ከጤፍም የበለጠ የእህል ቁንጮ ነው፡፡ ክርክሩ ሁሌም እንዳለ ነው፡፡ በሌላም በኩል ታላቁ የጤፍ ተመራማሪ ዶ/ር ታረቀ በረሔ “ዝም ብለው ነው ኪኑዋ ይበልጣል የሚሉት ጤፍ ትበልጣለች፤ ከሁሉ የምድር እህል የዓለም የተስፋ ምግብ፣ የጤና ምግብ ጤፍ ናት፡፡”  በማለት ተጨባጭ መስፈርት ያስቀምጣሉ፡፡

ለ. የኪኑዋ የዓለም የገበያ ዋጋ

በዓለም ዋጋ አማካይ  የ ጥቅምት 2ዐ18 እ.ኤ.አ የአንድ ኪሎ የጥሬ ኪኑዋ ዋጋ 2.32 ዶላር  ነው፡፡ ማቀጣሻ ሁለት   ከአውሮፓ አገራት ፈረንሳይ ከፍተኛ ገዢ ስትሆን ቀዳሚ አምራችም ናት፡፡ አሁን የምርት መጠኗ ግን ከእስፔን ቀጥሎ ሁለተኛ ናት፡፡  በሌሎች የአውሮፓ አገራትም እንደ  ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ፖላንድ፣ ቡልጋሪያ፣ ፖርቹጋል እና ቼክ ሪፓብሊክ ባሉት ይታረሳል፡፡

ሐ. ኪኑዋ በኢትዮጵያ

የኪኑዋን ዘር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት፣ በምርምር እንዲፈተሽ እና በኢትዮጵያ ለማስመዝገብ እንዲቻል የዳን ቸርች ኤድ (Dan Church Aid) የገንዘብ እና የሙያ እርዳታ አድርጎ ነው፡፡  ዳን ቸርች ኤድ (Dan Church Aid)   ለዚህ መልካም ውለታቸው የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

የመልካሳ እርሻ ምርምር ማዕከል የመጣውን የኪኑዋ ዘር  ለሁለት አመት በመፈተሽ  መስፈርቱን አሟልቶ በኢትዮጵያ እንዲመዘገብ ታላቅ የሙያ አበርክቶ አድርገዋል፡፡ እነሱም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ከፍተሻው እና ምዝገባው በኋላም ዳን ቸርች ኤድ ድጋፉን በመቀጠል፣ በ2ዐዐ7 ዓ.ም  ወሎ ውስጥ ወረኢሉአምባሰል፣ ለጋምቦ እና ለጋሂዳ ወረዳዎች ውስጥ በአርሶ አደር ማሳ ላይ እና በገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከል ጊቢ ውስጥ የማላመድ ሥራ ተከናውኖ የአመርራረት መመሪያም በአቶ ልደት ስጦታው ሊዘጋጅ ተችሏል፡፡ በአመራረት መመሪያው ላይ ስለ አስተራረሱ፡ የአዝመራ አሰባሰብ ስልቱ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተገልጿል፡፡ ማጣቀሻ ሶስት

ከዚያም በኋላ በቀጣይ አመታት በተለያዩ ቦታዎች ተዘርቶ ይሆናል፡፡ በተለይም ዋግምራ አካባቢ በአውሮፓ ህብረት የሚደገፈው ሪሴት 2 ፕሮጀክት በአክሽን አጌነስት ሃንገር (ACTION AGAINST HUNGER) ድርጅት  ጥሩ ሙከራ ተደርጓል፡፡ አክሽን አጌነስት ሃንገር ከወራት በፊት በዞማ ፓርክ ውስጥ በአንድ ልዩ ዝግጅት ላይ የኪኑዋን  ውጤታማነት በፖስተር አስደግፎ፣ በአቶ አቦምሳ ከበደ ኡማ ሲያስተዋውቅ ነበር፡፡

ምስል አንድ የኪኑዋ ተክል በማሳ ላይ

ከአክሽን አጌነስት ሃንገር ፖስተር ላይ የተነሳ ምስል

እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ ኪኑዋ ኢትዮጵያ ውስጥ መታረሱን ሰማሁ፣ ወድያውም እህሉንም አየሁ፡፡ ከዶ/ር ባዩሽ ፀጋዬ  እና ከሌሎችም ጋር ሆነን ከመስኩ ላይ ተቀምጠን እንዴት ደስ እንዳለን አልረሳውም፡፡ እኔ “ጤፍ የኛ በረካ ከአጃቢዎቹ ጋር”  መጽሐፍ ላይ ስለ ኪኑዋ የጠቀስኩት፣ የእኛ ተመራማሪዎች ዱር በቀል የሆነውን ስኒንግ ወይም አመድማዶን በመረጣ ስልት ወደ አዝመራ ያመጣሉ የሚል ተስፋ ነበረኝ እንጂ፤ ዋናው  ኪኑዋ ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርብ አመታት ደርሶ፣ ተመዝግቦ ይታረሳል የሚል ሐሳብ አልነበረኝም፡፡

ምስል ሁለት የኪኑዋ ዘር

መ. የኪኑዋ እንጀራ

የኪኑዋ በአገራችን መታረስ ዜና ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ከታረሰማ  እንጀራ መጋገር ነው እንጂ ምን እንጠብቃለን፡፡ በብዙ ፍለጋ አንድ ኪሎ ኪኑዋ አገኘሁ፡፡ ከሁለት ኪሎ ጤፍ ጋር ግማሽ ኪሎ ኪኑዋ (4፡1) ተመጥኖ ተፈጨ፡፡ ከዚህ ላይ ጥቂት ዱቄት 2 ቀን ተኩል ወይም 6ዐ ሰዓት ተቦክቶ ቆየ፡፡ ልክ እንደ ጤፍ አብሲት ሠራንለት፡፡ አብሲቱ እጅግ ስለወፈረ ብዙ ውሃ አነሳ፡፡ አብሲቱ ሲቀዘቅዝ ለብ ባለው ውሃ እና ትንሽ ከዱቄቱ አጎባጉበን ሊጡ ቀጠነ፡፡ ሊጡም ብዙ ውሃ አነሳ፡፡ በአንድ ሰዓት ውስጥ ኩፍ አለ እናም ተጋገረ፡፡ እየበላንለት ሁለት ቀን አደረ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ፎቶ ያነሳሁት፡፡ ከሁለት ቀን በኋላም የእንጀራው ዓይኑ፣ ሰበከቱ ያምራል፡፡ ቃናው ምንም የተለየ አይደለም፡፡ እጅግ ግሩም ነው፡፡

ምስል ሶስት ጤፍ እና ኪኑዋ (4፡1) ምጥን እንጀራ

ማጠቃለያ

በዓለም የተጨበጨበላቸው ጤፍ እና ኪኑዋ ተመጥነው እንዲህ ያለ እንጀራ ከሆኑ ምን እንጠብቃለን?  እንደ ጥቂቶች የነገር ጉንጉን ትተን እንደ ብዙሃኑ አርሶ አደር ትኩረታችንን ወደ እርሻ አድርገን በምግብ ሰብል እራሳችንን እንቻል፡፡ ይህ ማለት እርሻ ብዙ ሥራ አሉት፤ ሁሉም ሰው ሁለት በሬ ጠምዶ ማረስ አይደለም፡፡  ኪኑዋ የዓለም ዋና እህል በመሆኑ እንዲሁም በብዙ የተጎዱ ቦታዎች መልማት በመቻሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ እንጀራ በተለይም በከተሞች ዋና ምግብ ስለሆነ፣ ኪኑዋ ለእንጀራ ተስማሚ በመሆኑ ምርቱ ላይ ትጋት ማድረግ እንደሚገባን ያመለክታል፡፡ ኪኑዋ ቅጠሉም እንደ ሰላጣ ወይም በስሎ ይበላል፡፡ ቅጠሉ እና ዘንጎቹ ለእንስሳት መኖ ይሆናሉ፡፡

ኪኑዋ እንኳን ወደ ኢትዮጵያ እርሻ በሠላም መጣሽ፡፡

 

ማጣቀሻ

 ማቀጣሻ አንድ በቀለች ቶላ 2ዐዐ8 ዓ.ም ጤፍ የኛ በረካ ከአጃቢዎቹ ጋር፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት አዲስ አበባ፤

ማቀጣሻ ሁለት  https://www.statista.com/statistics/520974/average-price-of-quinoa-worldwide/

ማጣቀሻ ሶስት Lidet Sitotaw, May 2017, Quinoa Production Manual, Quinoa: Possible Solution for Multiple

Agricultural Problems, Preliminary Information Source for Agricultural Experts, USAID and DCA

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com