ዜና

ራያ ኮረም አዲስ ከንቲባዋን አልቀበልም አለች

Views: 276
  • በሹመቱ የከተማው ምክር ቤት እና ህወሓት ተፋጠዋል

ራያ-ኮረም ከተማን በሕግ ያልተወከለ ከንቲባ እያስተዳደራት እንደሆነ የከተማው ምክር ቤት አባላት ለኢትዮ-ኦንላይን አሳወቁ፡፡

ህወሓት በቀላጤ ከትግራይ ሰው መልምሎ ለራያ-ኮረም ከተማ ከንቲባ የሾመ ቢሆንም፣ የኮረም ከተማ ምክር ቤት ሹመቱን ባለማጽደቁ፣ ህወሓትና የከተማው ምክር ቤት ተፋጠዋል ብለዋል፡፡

በቀድሞው አሥተዳደራዊ መዋቅር የሰሜን ወሎ ክፍለ ሃገር፣ በአሁኑ የትግራይ ክልል ውስጥ የተካተተችው የኮረም ከተማ፤ በህወሓት ባለስልጣናት ተመርጦ የተሾመው ከንቲባ፣ ሹመቱ በከተማው ምክር ቤት ባለመጽደቁ በሕግ ያልተወከለ ከንቲባ አድርጎታል ሲሉ የምክር ቤት ምንጮች ለኢትዮ-ኦንላይን ገልጸዋል፡፡

ለሁለቱ የአመራር አካላት መፋጠጥ ምክንያት የሆነው፣ ህወሓት ለኮረም ከተማ በቀጥታ ሾሞ የላከላቸውን የከንቲባ ሹመት፣ የከተማው ምክር ቤት አባላት በአንድ ድምጽ አላጸድቅም ማለቱ ነው፡፡

የራያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደጀኔ አሰፋ ለኢትዮ-ኦንላይን እንደገለጹት፣ በህወሓት ለራያ ኮረም ከተማ ከንቲባነት የተመለመለው ግለሰብ በመጀመሪያ በከተማው የአነስተኛና ጥቃቅን ብድር ተቋም ኃላፊ ሆኖ ተመድቦ ሲሰራ፣ በሙሰኝነቱ የታወቀ፣ ብድርና የሥራ ድጋፍ በብዛት በከተማው ለሚኖሩ የትግራይ ሰዎች ብቻ ሲፈቅድ የነበረ ነው ብለዋል፡፡

በአንፃሩ፣ የራያ ወጣቶች ተደራጅተው ለሥራ ብድር ሲጠይቁ ግን መሰናከል የሚያበዛ፣ ለሚፈቀድላቸው ጥቂቶችም ከሚፈቀድላቸው ብድር ላይ በመቶኛ ተደራድሮ ገንዘብ የሚቀበል ሙሰኛ ሰው ስለነበረ፣ የከተማው ሰው ተማሮ ከፍተኛ ተቃውሞ በመከሰቱ ከኃላፊነት እንዲነሳ የተደረገ የትግራይ ተወላጅ ነው፤ የራያ ተወላጅ አይደለም ብለዋል፡፡

ህወሓት፣ አሁን በዚህ ወቅት ይህን ግለሰብ የራያ ኮረም ከተማ ከንቲባ ለማድረግ የፈለገው፣ የተጠናከረበትን የራያ የማንነት ጥያቄ ለመቀልበስና ግለሰቡ ቀደም ሲል በሰራበት ተቋም ሳቢያ፣ የራያ ወጣቶችን ያውቃል ተብሎ ስለሚታሰብ፤ የማንነት ጥያቄ የሚያነሱ ወጣቶችን አስለቅሞ ለማሳሰር ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል ጀምሮ ህወሓት በከተማው እንደፈለገው ሹመት ሲያወርድ እንደነበር የጠቀሱት የመረጃ ምንጮቻችን፣ በድርጅታዊ አሰራር ከአንድ የህወሓት የዕዝ ሠንሠለት የሚወርድን ትዕዛዝ ወደ ታች ያለው አካል ያለ ጥያቄ መፈጸም የሚገደድበት ነበር፤ የምክር ቤቶቹም ሚና የተባሉትን ከማጽደቅ የዘለለ አልነበረም፤ አሁን ነገሮች ተቀይረዋል፤ ራያ ማንነቱን ሊያስከብር ቆርጦ ተነስቷል ብለዋል፡፡

በዚህ ምክንያትም የራያ ኮረም ከተማ ምክር ቤቱ በአንድ ድምጽ ከላይ የተሰየመውን የከንቲባውን ሹመት እንደማያጸድቅና እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡

የህወሓት የበላይ አካላትም የተወሰኑ የምክር ቤት አባላትን ነጥለው በማስፈራራት፣ የተወሰኑትን ደግሞ በጥቅማ ጥቅም ለማግባባትና ሹመቱን ለማስጸደቅ ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ ምክር ቤቱ በአቋሙ በመጽናቱ ሊሳካ አልቻለም ብለዋልል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከተማዋ ያለ ሕጋዊ ከንቲባ እየተዳደረች ሲሆን፣ የከተማው ድባብ ህወሓት ልዩ ኃይሉን ልኮ ማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ስጋት አለ እየተባለ ነው፡፡

የከተማው ምክር ቤት የከንቲባውን ሹመት ያልተቀበለው ለምንድን ነው በሚል ከኢትዮ-ኦንላይን ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ከተማዋ ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብቷን ለመጠቀም የወሰደችው ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው፤ ይህ የዓመታት የራያ የማንነት ጥያቄ አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com