የዓለም የቱሪዝም ግብይት ተቋም በአዲስ አበባ የምስራቅ አፍሪካ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱን ሊከፍት ነው

Views: 237

ታዋቂው የዓለም የቱሪዝም ግብይት ተቋም (World Travel Market) በአዲስ አበባ ማዕከሉን ሊገነባ መሆኑን የባሕልና ቱሪዝም ሚንስቴር አስታውቋል፡፡ የባሕልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳው የዓለም ቱሪዝም ግብት ተቋም እና የሪድ አውደርዕይ ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን ሚስካፎል ዌቪንግን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገነባው ማዕከል የምስራቅ አፍሪካ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እንዲሆን ታስቧል፡፡ ከዚህ በፊት በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ማስተባበሪያ ከፍቶ እየሠራ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ የሚከፈተው በአፍሪካ ሁለተኛ ማዕከሉ ይሆናል፡፡ የማዕከሉ መከፈት ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ በሚካሄዱ ጉባዔዎችና አውደርዕዮች ባሕሏንና ቅርሶቿን ለማስተዋወቅ እንደሚያግዛትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገብረ መስቀል ካሳ በተለይ ለኢትዮ ኦንላይን ገልፀዋል፡፡

የፊታችን ሚያዚያ ማዕከሉ በአዲስ አበባ ይከፈታል ብለው እንደሚጠብቁም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

በዓለም የቱሪዝም ግብይት ሥር በቋሚነት በኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ የኢትዮጵያ የጉብኝት ግብይት እና የምስራቅ አፍሪካን ዓለማቀፍ የቱሪዝም ጉባዔ ብሎም አውደ ርዕይ ለመክፈት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

የኢትዮጵያን የጉብኝት መስህቦች ይበልጥ ለማስተዋወቅና የገንዘብ ምንጭ እንዲሆኑ ለማስቻልም የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ዶክተር ሒሩት ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክር አቶ ስለሺ ግርማ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተገኝተዋል፡፡

የማዕከሉ መገንባት በመስተንግዶ እና ቱሪዝም ዘርፎች ኢትዮጵያ የምትሠራቸውን ሥራዎች የተሻለ ለማድረግ እንደሚያግዝም ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሥራ ሁለት የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የባህልና የትምህርት ተቋም አስመዝግብለች፡፡ ሆኖም ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ አነስተኛ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በቱርክ አንድ ቅርስ የሚበላሸው በጎብኝዎች ብዛት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግን ቅርሶች የሚበላሹት በፀሃይ፣ በውርጭ፣ በነፋስና እና መሰል ከእንክብካቤ ጉድለት የሚመጡ አደጋዎች ነው፡፡ በመሆኑም የማዕከሉ መገንባት ይህንን ልማድ ለመቀየር ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com