ዜና

ተማሪዎች ኮማንድ ፖስት እንዲቋቋም ጠየቁ

Views: 234

ስምንት ተማሪዎች በቁጥር ሥር ውለዋል

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ከሰሞኑን የተነሳውን አለመረጋጋት ተከትሎ በዛው ዕለት  አንጻራዊ መረጋጋት የሚታይ ቢመስልም፣ ሙሉ በሙሉ ከስጋት አልወጣንም ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለኢትዮ-ኦንላይን ገለጹ፡፡

ተማሪዎቹም ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው በመስጋት ወደ መጡበት እየተመለሱ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ቁጥራቸው አንድ ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች በሐረር ሥላሴ ቤተክርስቲያን የተጠለሉ ሲሆን፣ አሁን ግን ወደ 400 ገደማ ተማሪዎች ብቻ በደብሩ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች ከግቢው ወጥተን ‹‹እንሂድ- አንሂድ›› በሚሉ ሃሳቦች ለሁለት መከፈላቸውን የነገሩን የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች፤ በጊቢው ውስጥ ኮማንድ ፖስት እንዲቋቋም ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር ጠይቀናል ብለዋል፡፡

አመራሮቹም እኛ ጊዜያዊ ነን፣ በቂ መልስ መስጠጥ አንችልም፤ ቢሆንም ግን ወደ ትምህርታችሁ ተመለሱ፤ ጥበቃ እናደርግላቸኋለን ብለዋል ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡

ከኮማንድ ፖስት ይቋቋም ጥያቄ በተጨማሪ፣  አጥፊዎች ይጠየቁልን፣ ዩኒቨርሲቲው በፌደራል መንግሥት የሚተዳደር በመሆኑ፣ በአንድ ወገን ብቻ የተሞላ በመሆኑ አስተዳደራዊ መዋቅር ይስተካከልን የሚለውን ጨምሮ ሌሎች ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

አንዳንድ ተማሪዎች ለመማር ፍላጎት እንኳን ቢኖራቸው፣ የግጭቱ አቀጣጣዮች  ግን ‹‹ከአማራ ጋር አብረን መማር አንፈልግም›› ማለታቸውን ሰምተናል ሲሉ ምንጫችን ለዘጋቢያችን አስረድተዋል፡፡

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ተጀምሯል ይበል እንጂ፣ ተማሪዎቹ ግን እንዳልተጀመረ እና የኦሮምኛ ተናጋሪ ተማሪዎችም አንገባም እያሉ ናቸው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ የተወሰኑ ኮሌጆች ላይ ትምህርት ተጀምሯል፤ አሁን ላይ ይህን ያህል ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ተገኝተዋል ለማለት አዳጋች መሆኑን ገልጿል፡፡

የኮማንድ ፖስቱን ጉዳይ በተመለከተም የዩኒቨርስቲው የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር  አቶ የዓለምእሸት ተሾመ ለኢትዮኦንላይን  እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው ይህን የማድረግ ሥልጣን የለውም፤ ይህንን ማድረግም አይችልም ብለዋል፡፡

የእኛ አቅም የጸጥታ ጉዳዩን አጠናክሮ መስራት ነው፤ ይህንንም እያደረግን ነው የመከላከለያ፣ የፌደራል  እና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል አድማ ብተና  በመመደብ ተማሪዎቹ ከሥጋት ነጻ እንዲሆኑ እየሠራን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም እስካሁንም ስምንት ተማሪዎች በቁጥር ሥር መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሕይወቱ ያለፈ ተማሪ የለም ያሉት አቶ የዓለምእሸት በንብረት ላይ ግን አንድ ክፍል የወንዶች ማረፊያ ወይም ዶርም መቃጠሉን ገልጸዋል፡፡

ጥቃቱ ዘር እና ሀይማኖትን ያማከለ ነው ወይ ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄ በዩኒቨርሲቲ  የተከሰተው ግጭት  ከወልዲያ ከተከሰተው ክስተት ጋር ብዙ ግንኙነት የለውም ሲሉ ተደምጠዋል ፡፡

ምክንያቱ ደግሞ  ከዚህ ጥቃት በፊት በወለጋ የተጣለው አስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ይነሳ የሚል ነበር፤ በኋላም የብሔር ግጭት የሚመስል ድርጊት ተፈጸመ እንጂ፣ እዚህ ያለ ተማሪ ብሔር ለይቶ የታገጨ የለም  ነው ያሉት አቶ የዓለምእሸት፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com